Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


2 ነገሥት 9 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የኢዩ በእስራኤል ላይ ተቀብቶ መንገሥ

1 በዚያን ጊዜ ነቢዩ ኤልሳዕ ደቀ መዛሙርቱ ከሆኑት ነቢያት አንዱን ጠርቶ እንዲህ አለ፤ “በገለዓድ ወደምትገኘው ወደ ራሞት ለመሄድ ተዘጋጅ፤ ይህንንም የዘይት ማሰሮ ያዝ፤

2 እዚያም በደረስህ ጊዜ የኢዮሣፍጥ ልጅ፥ የኒምሺ የልጅ ልጅ የሆነውን ኢዩን ፈልግ፤ እርሱንም ከጓደኞቹ በማስገለል ወደ ጓዳ አስገባው፤

3 ይህን የወይራ ዘይት በራሱ ላይ አፍስስበት፤ ‘አንተ ተቀብተህ በእስራኤል ላይ እንድትነግሥ እግዚአብሔር አዞአል’ ብለህም ንገረው፤ ከዚህም በኋላ በሩን በመክፈት በተቻለ ፍጥነት ከዚያ ስፍራ ተነሥተህ ሽሽ።”

4 ስለዚህም ወጣቱ ነቢይ ወደ ራሞት ሄደ፤

5 እዚያም እንደ ደረሰ የጦር መኰንኖች ተቀምጠው ሲወያዩ አግኝቶ “ጌታዬ ለአንተ የምሰጥህ መልእክት አለኝ” አለው። ኢዩም “ከእኛ መካከል ለማንኛችን ነው የምትናገረው?” ሲል ጠየቀው። ነቢዩም “የምናገረው ለአንተው ነው” ሲል መለሰ።

6 ከዚህ በኋላ ሁለቱ ወደ ቤት ውስጥ ገብተው ወጣቱ ነቢይ የወይራውን ዘይት በኢዩ ራስ ላይ አፈሰሰበትና እንዲህ አለው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚናገረው ይህ ነው፤ ‘በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ተቀብተህ እንድትነግሥ አድርጌሃለሁ፤

7 አንተም የአክዓብ ልጅ የሆነውን ጌታህን ንጉሡን መግደል አለብህ፤ በዚህም ዐይነት የእኔን ነቢያትና ሌሎችንም አገልጋዮቼን የገደለችውን ኤልዛቤልን እበቀላታለሁ፤

8 መላው የአክዓብ ቤተሰብና ትውልዱ ሁሉ መሞት አለባቸው፤ እኔ ከእርሱ ቤተሰብ ወንድ የሆነውን ማንኛውንም ባሪያም ሆነ ነጻ ሰው አስወግዳለሁ።

9 የእስራኤል ነገሥታት በነበሩት በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓምና በአኪያል ልጅ በበዕሻ ቤተሰቦች ላይ ያደረግኹትን፥ ሁሉ በአክዓብ ቤተሰብ ላይ እፈጽማለሁ።

10 ኤልዛቤል የመቀበር ዕድል እንኳ አታገኝም፤ የእርስዋም ሬሳ በኢይዝራኤል ግዛት ውሾች ይበሉታል፤’ ” ይህን ሁሉ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ ወጣቱ ነቢይ በሩን በመክፈት ከዚያ ክፍል ወጥቶ ሸሸ።

11 ኢዩም፦ ጓደኞቹ ወደሆኑት ወደ ጦር መኰንኖቹ በመጣ ጊዜ “ሁሉ ነገር ሰላም ነውን? ለመሆኑ ይህ እብድ ከአንተ ምን ይፈልጋል?” ሲሉ ጠየቁት። ኢዩም “ሰውየውንም ሆነ እርሱ የሚናገረውን እናንተ ታውቁታላችሁ” አላቸው።

12 እነርሱም “ኧረ እኛ አናውቅም፤ ምን እንደ ተናገረ አስረዳን!” ሲሉ መለሱለት። ኢዩም፦ “ ‘በእስራኤል ላይ ተቀብተህ እንድትነግሥ እግዚአብሔር አዞአል’ አለኝ” ሲል አስረዳቸው።

13 ወዲያውኑ የኢዩ ጓደኞች የነበሩት የጦር መኰንኖች ልብሳቸውን እያወለቁ ኢዩ በሚራመድበት ደረጃ ላይ አነጠፉ፤ በዚያም ላይ እንዲቆም አድርገው እምቢልታ ነፉ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው “ኢዩ ነግሦአል!” ሲሉ ጮኹ።


የእስራኤል ንጉሥ ኢዮራም መገደል

14-15 ከዚያም በኋላ የኢዮሣፍጥ ልጅ የኒምሺ ልጅ ኢዩ በንጉሥ ኢዮራም ላይ ሤራ ማካሄድ ጀመረ፤ ኢዮራም ከሶርያ ንጉሥ አዛሄል ጋር በራሞት በተደረገው ጦርነት ላይ ስለ ቈሰለ በዚያን ጊዜ በኢይዝራኤል ውስጥ በማገገም ላይ ነበር፤ ስለዚህም ኢዩ ጓደኞቹ የሆኑትን የጦር መኰንኖች “እናንተ በእርግጥ ከእኔ ጋር ከሆናችሁ በኢይዝራኤል የሚኖረውን ሕዝብ ለማስጠንቀቅ አንድ ወሬ ነጋሪ እንኳ ከራሞት ወጥቶ እንዳያመልጥ አድርጉ” አላቸው።

16 ከዚህም በኋላ ኢዩ በሠረገላው ላይ ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ገሠገሠ፤ በዚህ ጊዜ ኢዮራም ገና ከቊስሉ አልዳነም ነበር፤ የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስም ሊጠይቀው መጥቶ በዚያ ይገኝ ነበር።

17 በኢይዝራኤል ከተማ መጠበቂያ ግንብ ላይ የነበረው ቃፊር ኢዩና ተከታዩ ጭፍራ ሲመጡ መቃረባቸውን አይቶ፥ “ሰዎች እየጋለቡ ሲመጡ አያለሁ!” ሲል የጥሪ ድምፅ አሰማ። ኢዮራምም “አንድ ፈረሰኛ ልከህ የሚመጡትን ሰዎች ሰላም ነውን? ብሎ እንዲጠይቅ አድርግ” አለው።

18 መልእክተኛውም ጋልቦ ሄዶ ኢዩን “ንጉሡ አመጣጥህ በወዳጅነት እንደ ሆነ ማወቅ ይፈልጋል” ሲል ጠየቀው። ኢዩም “አንተ ከሰላም ጋር ምን ግንኙነት አለህ? ይልቅስ ወደ ኋላ አልፈህ ተከተለኝ!” ሲል መለሰለት። በከተማይቱም መጠበቂያ ግንብ ላይ የነበረው ዘብ “መልእክተኛው በመምጣት ላይ ወዳለው ጭፍራ ደርሶአል፤ ነገር ግን ተመልሶ አልመጣም” ሲል አስረዳ፤

19 ሌላም መልእክተኛ ተልኮ ያንኑ ተመሳሳይ ጥያቄ ለኢዩ አቀረበለት፤ ኢዩም “አንተ ከሰላም ጋር ምን ግንኙነት አለህ? ይልቅስ ወደ ኋላ አልፈህ ተከተለኝ!” ሲል መለሰለት።

20 “ዘበኛውም እንደገና መልእክተኛው በመምጣት ላይ ወዳለው ጭፍራ ደርሶአል፤ ነገር ግን ተመልሶ አልመጣም” ካለ በኋላ “የጭፍራው መሪ ሠረገላ አነዳዱ እንደ እብድ ሰው ነው! እንዲያውም ልክ ኢዩን ይመስላል!” ሲል ተናገረ።

21 ከዚህ በኋላ ንጉሥ ኢዮራም “ሠረገላዬን አዘጋጅልኝ” ሲል ትእዛዝ ሰጠ፤ ሠረገላውም ተዘጋጅቶለት እርሱና ንጉሥ አካዝያስ በየግል ሠረገላቸው እየጋለቡ ኢዩን ሊገናኙት ወጡ፤ እነርሱም ኢዩን ቀድሞ የናቡቴ ርስት በነበረው እርሻ ላይ አገኙት።

22 ኢዮራምም “ኢዩ ሆይ፥ አመጣጥህ በሰላም ነውን?” ሲል ጠየቀ። ኢዩም፦ “እናትህ ኤልዛቤል ባመጣችው አስማትና የጣዖት አምልኮ ውስጥ ተነክረን እስካለን ድረስ ምን ሰላም አለ?” ሲል መለሰለት።

23 ኢዮራምም ድምፁን ከፍ በማድረግ “አካዝያስ ሆይ! ይህ እኮ ክሕደት ነው!” እያለ ሠረገላውን መልሶ ሸሸ።

24 ኢዩ ቀስቱን ስቦ ባለው ኀይል በመጠቀም ፍላጻውን ባስፈነጠረ ጊዜ ኢዮራምን ወግቶ በትከሻዎቹ መካከል እስከ ልቡ ዘለቀ፤ ኢዮራምም ሞቶ በሠረገላው ውስጥ ወደቀ።

25 ኢዩ ቢድቃር ተብሎ የሚጠራውን የቅርብ ረዳቱን “ሬሳውን አንሥተህ የናቡቴ ርስት በነበረው እርሻ ላይ ወርውረህ ጣለው፤ እኔና አንተ የንጉሥ ኢዮራም አባት ከነበረው ከአክዓብ በስተኋላ እየጋለብን ስንሄድ እግዚአብሔር በአክዓብ ላይ የተናገረውን ቃል አስታውስ፤

26 ‘ትናንትና የናቡቴንና የልጆቹን መገደል አየሁ፤ በዚሁ እርሻ ላይ እንደምቀጣህ እምላለሁ’ የሚል ነበር።” ስለዚህ ኢዩ “እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ የኢዮራምን ሬሳ አንሥተህ የናቡቴ ርስት በነበረው እርሻ ላይ በመወርወር ጣለው” ሲል የቅርብ ረዳቱን አዘዘ።


የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ መገደል

27 ንጉሥ አካዝያስ የሆነውን ነገር ሁሉ በተመለከተ ጊዜ በሠረገላው ላይ ተቀምጦ ወደ ቤትሀጋን ከተማ ሸሽቶ ሄደ፤ ኢዩ ተከታትሎ እያሳደደው “እርሱንም ግደሉት!” ሲል ለወታደሮቹ ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም አካዝያስን ተከታትለው በዪብለዓም ከተማ አጠገብ በምትገኘው በጉር የአቀበት መንገድ ላይ በሠረገላው ሲበር መትተው አቈሰሉት፤ እርሱ ግን እንደምንም ጨክኖ መጊዶ ከተማ እስኪደርስ ተጓዘ፤ በዚያም ሞተ፤

28 ባለሟሎቹ የሆኑ ባለሥልጣኖችም ሬሳውን በሠረገላ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰደው በዳዊት ከተማ በሚገኘው የነገሥታት መካነ መቃብር ቀበሩት።

29 አካዝያስ የይሁዳ ንጉሥ የሆነው የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በዐሥራ አንደኛው ዓመት ነበር።


የንግሥት ኤልዛቤል መገደል

30 በዚህም ጊዜ ኢዩ ወደ ኢይዝራኤል ደረሰ፤ ኤልዛቤልም ይህን የሆነውን ነገር ሰምታ ዐይንዋን ተኳለች፤ ጠጒርዋንም ተሠርታ በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ በመስኮት አዘንብላ ቊልቊል መንገዱን ትመለከት ነበር።

31 ኢዩ የቅጽሩን በር አልፎ ሲገባ “አንተ ዚምሪ! አንተ የጌታህ ገዳይ ደግሞ እዚህ ምን አመጣህ?” ስትል ጮኸችበት።

32 ኢዩ ቀና ብሎ ወደ ላይ በመመልከት ድምፁን ከፍ አድርጎ “ከእኔ ጋር የሚተባበር ማን ነው?” ሲል ጮኸ፤ ቊጥራቸው ከሁለት እስከ ሦስት የሆነ የቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣኖች በመስኮት ብቅ ብለው ወደ እርሱ ተመለከቱ፤

33 ኢዩም “ኤልዛቤልን ወደታች ወርውሩአት!” አላቸው፤ እነርሱም አንሥተው በወረወሩአት ጊዜ ደምዋ በግንቡና በፈረሶች ላይ ተረጨ፤ ኢዩም በሬሳዋ ላይ ፈረሶቹንና ሠረገላውን ነዳበት፤

34 ወደ ቤተ መንግሥቱም ገብቶ ተመገበ፤ ከዚህም በኋላ “ምንም ቢሆን የንጉሥ ልጅ ነችና፥ ያችን የተረገመች ሴት ወስዳችሁ ቅበሩ” አለ።

35 ሊቀብሩአት የሄዱ ሰዎች ግን ከራስ ቅልዋ፥ ከእግሮችዋና ከእጆችዋ አጥንት በቀር ምንም አላገኙም፤

36 ይህንንም ሁሉ ለኢዩ በነገሩት ጊዜ ኢዩ እንዲህ አለ፤ “ይህ ሁሉ የተፈጸመው እግዚአብሔር በአገልጋዩ ቴስቢያዊው በኤልያስ አማካይነት አስቀድሞ በተናገረው መሠረት ነው፤ ይኸውም ‘የኤልዛቤልም ሬሳ በኢይዝራኤል ግዛት ውሾች ይበሉታል፤

37 ከሬሳውም የሚተርፈው እንደ ፍግ በዚያ ይበተናል፤ ስለዚህም ማንም እርስዋነትዋን ለይቶ በማወቅ፦ ይህች ኤልዛቤል ናት፥ ሊል አይችልም’ ያለው ነው።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos