2 ነገሥት 10 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየአክዓብ ዘሮች ሁሉ መገደል 1 ብዛታቸው ሰባ የሚሆን የአክዓብ ልጆች በሰማርያ ከተማ ይኖሩ ነበር፤ ኢዩ ደብዳቤ ጽፎ የደብዳቤውን አንዳንድ ቅጂ ለከተማይቱ ገዢዎች፥ ለታወቁ የአገር ሽማግሌዎችና የአክዓብን ተወላጆች ለሚያሳድጉ ሞግዚቶች ሁሉ ላከ፤ የደብዳቤውም ቃል፥ 2 “እናንተ ለንጉሡ ተወላጆች ኀላፊዎች ናችሁ፤ ፈረሶችና ሠረገሎች የጦር መሣሪያዎችና የተመሸጉ ከተሞች ሁሉ በእናንተ እጅ ይገኛሉ፤ እንግዲህ ይህ ደብዳቤ እንደ ደረሳችሁ ወዲያውኑ፥ 3 ከንጉሡ ተወላጆች የተሻለውን አንዱን መርጣችሁ አንግሡት፤ ለእርሱም በመከላከል ተዋጉለት!” የሚል ነበር። 4 ከዚህም የተነሣ የሰማርያ ገዢዎች በፍርሃት ተሸብረው፥ “ንጉሥ ኢዮራምና ንጉሥ አካዝያስ ሊቋቋሙ ያልቻሉትን እኛ እንዴት ኢዩን ልንቋቋመው እንችላለን?” አሉ። 5 ስለዚህም የቤተ መንግሥቱ ኀላፊና የከተማይቱ ገዢ ከታወቁ የአገር ሽማግሌዎችና ከአሳዳጊ ሞግዚቶች ጋር በመተባበር ለኢዩ “እኛ አገልጋዮችህ ነን፤ አንተ የምታዘንን ሁሉ ለመፈጸም ዝግጁዎች ነን፤ እኛ ማንንም አናነግሥም፤ አንተ መልካም መስሎ የታየህን አድርግ” ሲሉ መልእክት ላኩ። 6 ኢዩም “እናንተ ከእኔ ጋር ከተባበራችሁና ትእዛዜንም ለመፈጸም ዝግጁዎች ከሆናችሁ፥ ነገ በዚህ ጊዜ የንጉሥ አክዓብን ዘሮች ሁሉ ራሶቻቸውን ቈርጣችሁ ይዛችሁልኝ ኑ” ሲል ሌላ ደብዳቤ ጻፈላቸው። ሰባው የንጉሥ አክዓብ ተወላጆች በሰማርያ አሳዳጊዎቻቸው በሆኑ በታወቁ የአገር ሽማግሌዎች ጥበቃ ሥር ነበሩ፤ 7 የኢዩ ደብዳቤ እንደ ደረሳቸው የሰማርያ መሪዎች ሰባውንም የአክዓብ ተወላጆች በሙሉ ገደሉ፤ ራሶቻቸውንም በመቊረጥ በቅርጫት ሞልተው በኢይዝራኤል ወደ ነበረው ወደ ኢዩ ላኩለት። 8 ኢዩ የአክዓብ ትውልድ ራሶች ተቈርጠው መምጣታቸውን በሰማ ጊዜ በከተማይቱ ቅጽር በር በሁለት ረድፍ ተከምረው እስከ ተከታዩ ቀን ጧት ድረስ እንዲቈዩ ትእዛዝ ሰጠ፤ 9 በማግስቱም ማለዳ ወደ ከተማይቱ ቅጽር በር ሄዶ በዚያ ለተሰበሰቡት ሕዝብ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “በንጉሥ ኢዮራም ላይ በማሤር የገደልኩት እኔ ነበርኩ፤ ስለዚህም እናንተ በዚያ ጉዳይ አትጠየቁበትም፤ ነገር ግን እነዚህን ሁሉ የገደለ ማን ነው? 10 ይህም ሁሉ እግዚአብሔር ስለ አክዓብ ትውልድ የተናገረው ቃል እውነት መሆኑን ያስረዳል፤ እግዚአብሔር በአገልጋዩ በነቢዩ ኤልያስ አማካይነት የተናገረውን ቃል ፈጽሞታል።” 11 ከዚህም በኋላ ኢዩ በኢይዝራኤል የሚኖሩትን ሌሎቹን የአክዓብን ዘመዶች፥ ባለሟሎቹ የነበሩትን ባለሥልጣኖች እንዲሁም የቅርብ ወዳጆቹንና ካህናቱን አንድም ሳይቀር ሁሉንም ገደለ። የንጉሥ አካዝያስ ዘመዶች በሙሉ መገደል 12 ኢዩ ከኢይዝራኤል ተነሥቶ ወደ ሰማርያ ሄደ፤ በመንገድ ሳለም “የእረኞች ሰፈር” ተብሎ በሚጠራው ቦታ ሲደርስ፥ 13 ከሟቹ የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ ዘመዶች መካከል ጥቂቶቹን አግኝቶ “እናንተ እነማን ናችሁ?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም “እኛ የአካዝያስ ዘመዶች ነን፤ አሁንም የንግሥት ኤልዛቤልን ልጆችና የቀሩትንም ንጉሣውያን ቤተሰብ እጅ ለመንሣት ወደ ኢይዝራኤል መሄዳችን ነው” ሲሉ መለሱለት። 14 ኢዩም “እነዚህን ሰዎች ከነሕይወታቸው ያዙአቸው!” ሲል ለጭፍሮቹ ትእዛዝ ሰጠ፤ ጭፍሮቹም ያዙአቸውና ኢዩ በዚያው በውሃ ጒድጓድ አጠገብ ገደላቸው። ብዛታቸውም በሙሉ አርባ ሁለት ሲሆን፥ ከእነርሱ አንድ እንኳ በሕይወት አልተረፈም። የቀሩት የአክዓብ ዘመዶች በሙሉ መገደል 15 ኢዩ ተነሥቶ እንደገና ጒዞ ቀጠለ፤ በመንገድ ሳለም የሬካብን ልጅ ኢዮናዳብን አገኘ፤ ኢዩም ሰላምታ ከሰጠው በኋላ “እኔና አንተ በሐሳብ አንድ ነን፤ ታዲያ ከእኔ ጋር ትተባበራለህን?” ሲል ጠየቀው። ኢዮናዳብም “አዎ እተባበርሃለሁ” ሲል መለሰ። ኢዩም “እንግዲያውስ ጨብጠኝ” ሲል መለሰለት፤ እጅ ለእጅ ተያይዘው ኢዩ ደግፎት በሠረገላው ላይ አስቀመጠውና፥ 16 “ከእኔ ጋር ሆነህ እኔ ለእግዚአብሔር ምን ያኽል ታማኝ እንደ ሆንኩ ራስህ ተመልከት” አለው፤ አብረውም እየጋለቡ ወደ ሰማርያ ሄዱ። 17 እዚያም በደረሱ ጊዜ ኢዩ አንድም ሳያስቀር የአክዓብን ዘመዶች በሙሉ ፈጀ፤ ይህም ሁሉ የሆነው እግዚአብሔር በነቢዩ ኤልያስ አማካይነት በተናገረው ቃል መሠረት ነበር። ባዓል ተብሎ የሚጠራውን ጣዖት የሚያመልኩ መገደል 18 ኢዩ የሰማርያን ሕዝብ በአንድነት ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ንጉሥ አክዓብ ባዓልን ያገለገለው በመጠኑ ነበር፤ እኔ ግን ከእርሱ ይበልጥ ላገለግለው እፈልጋለሁ፤ 19 ስለዚህም የባዓልን ነቢያት በሙሉ፥ ባዓልን የሚያመልኩትንና ካህናቱን ጭምር በአንድነት ጠርታችሁ ሰብስቡልኝ፤ በምንም ምክንያት የሚቀር አይኑር፤ እኔ ለባዓል ታላቅ መሥዋዕት ስለማቀርብ በዚያ የማይገኝ ማንም ሰው ቢኖር በሞት ይቀጣል።” ይህም ሁሉ ባዓልን የሚያመልኩትን ሁሉ ለመግደል ኢዩ ያቀደው የተንኰል ዘዴ ነበር። 20 ከዚህም በኋላ ኢዩ “ባዓል ተብሎ ለሚጠራው ጣዖት ክብረ በዓል ይደረግ!” ሲል ትእዛዝ ሰጠ፤ ይህም በዐዋጅ ተነገረ። 21 ኢዩም በእስራኤል ምድር ሁሉ መልእክት አስተላለፈ፤ ባዓልን የሚያመልኩ ሁሉ ተሰበሰቡ፤ አንድም እንኳ የቀረ ሰው አልነበረም፤ ሁሉም ወደ ባዓል ቤተ መቅደስ ገብተው ዳር እስከ ዳር ሞሉት፤ 22 ከዚህም በኋላ ኢዩ የተቀደሱ አባላት ኀላፊ የሆነውን ካህን አልባሳቱን ሁሉ አውጥቶ ለባዓል አምላኪዎች ያጐናጽፋቸው ዘንድ አዘዘ። 23 ከዚህም በኋላ ኢዩ ራሱ የሬካብ ልጅ ከሆነው ከኢዮናዳብ ጋር አብሮ ወደ ቤተ መቅደሱ ገባ፤ በዚያም ለሕዝቡ “እንግዲህ በዚህ የሚገኙት የባዓል አምላኪዎች ብቻ መሆናቸውንና እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንድም አለመኖሩን በሚገባ አረጋግጡ” ሲል ተናገረ፤ 24 ወዲያውም እርሱና ኢዮናዳብ ለባዓል የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላም ልዩ ልዩ መሥዋዕት ለማቅረብ ገቡ፤ ከዚህም ቀደም ብሎ ኢዩ በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ሰማኒያ ወታደሮች በማሰለፍ “እነዚህን ሁሉ ሰዎች እንድትገድሉ ከእነርሱ አንድ ሰው እንኳ እንዲያመልጥ የሚያደርግ ማንም ሰው ቢኖር በዚያ ሰው ምትክ እርሱ ራሱ ይገደላል!” ሲል መመሪያ ሰጥቶአቸው ነበር። 25 ኢዩ መሥዋዕቱን አቅርቦ እንዳበቃ ወዲያውኑ ለዘብ ጠባቂዎችና ለጦር መኰንኖች “ገብታችሁ እነዚህን ሁሉ ግደሉ፤ አንድም ሰው እንዳያመልጥ!” ሲል አዘዛቸው፤ እነርሱም ሰይፍ ሰይፋቸውን በመምዘዝ ገብተው ሁሉንም ገደሉ፤ ሬሳቸውንም ሁሉ እየጐተቱ ወደ ውጪ አወጡት፤ ከዚህም በኋላ ወደ ቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል ገብተው፥ 26 በዚያ ያመልኩት የነበረውን የድንጋይ ዐምድ ወደ ውጪ አውጥተው በእሳት አቃጠሉት፤ 27 በዚህም ዐይነት ጣዖት አምላኪዎቹ የተቀደሰ ነው ብለው የሚያምኑበትን የድንጋይ ዐምድና ቤተ መቅደሱን አፈራረሱ፤ ቤተ መቅደሱንም መጸዳጃ አደረጉት፤ ዛሬም በዚሁ ዐይነት ይገኛል። 28 ኢዩ በእስራኤል የነበረውን የባዓልን ጣዖታዊ አምልኮ ያስወገደው በዚህ ዐይነት ዘዴ ነበር፤ 29 ነገር ግን ኢዩ እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራውን የንጉሥ ኢዮርብዓምን የኃጢአት መንገድ ከመከተል አልተገታም፤ ኢዩ ራሱ ቀደም ሲል የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በቤትኤልና በዳን ላቆማቸው የወርቅ ጥጃ ምስሎች መስገዱ አልቀረም። 30 ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ኢዩን “በአክዓብ ተወላጆች ሁሉ ላይ ልታደርግ የሚገባህን ባዘዝኩህ መሠረት ፈጽመሃል፤ ከዚህም የተነሣ የአንተ ትውልድ እስከ አራት ትውልድ ድረስ በእስራኤል ላይ እንደሚነግሡ የተስፋ ቃል እሰጥሃለሁ” አለው። 31 ኢዩ ግን ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ሕግ በፍጹም ልቡ ታዛዥ ሆኖ አልተገኘም፤ ይህን በማድረግ ፈንታ እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራቸውን የኢዮርብዓምን ክፉ አርአያነት ተከተለ። የኢዩ መሞት 32 በዚያም ዘመን እግዚአብሔር የእስራኤል ግዛት ስፋቱ እንዲቀነስ ማድረግ ጀመረ፤ የሶርያ ንጉሥ አዛሄል እስራኤልን ድል ነሥቶ የእስራኤልን ግዛት ሁሉ ያዘ። 33 እርሱም የያዘው ግዛት፥ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ፥ በስተ ደቡብ በኩል ከአርኖን ወንዝ በላይ እስከምትገኘው እስከ ዓሮዔር ከተማ የሚደርስ ሲሆን ይህም የጋድ፥ የሮቤልና በምሥራቅ የሚገኘው የምናሴ ነገድ እኩሌታ ይኖሩባቸው የነበሩትን የገለዓድንና የባሳንን ግዛቶች ያጠቃልላል። 34 ኢዩ ያደረገው ሌላው ነገርና የጀግንነት ሥራውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፤ 35 ከዚህም በኋላ ኢዩ ሞተ፤ በሰማርያም ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢዮአካዝ ነገሠ፤ 36 ኢዩ መኖሪያውን በሰማርያ በማድረግ በእስራኤል ላይ የነገሠበት ዘመን ኻያ ስምንት ዓመት ነበር። |