Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


1 ሳሙኤል 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የቃል ኪዳኑ ታቦት መማረክ

1 እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያንን ለመውጋት ወጡ፤ ስለዚህም እስራኤላውያን አቤንዔዜር ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ሰፈሩ፤ ፍልስጥኤማውያንም አፌቅ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ሰፈሩ፤

2 ፍልስጥኤማውያንም አደጋ መጣል ጀመሩ፤ ከከባድ ጦርነት በኋላ እስራኤላውያንን ድል በመንሣት በጦር ሜዳ አራት ሺህ ሰው ገደሉባቸው፤

3 ከጦርነት የተረፉት ወደ ሰፈራቸው በተመለሱ ጊዜ የእስራኤል መሪዎች እንዲህ አሉ፤ “ዛሬ ፍልስጥኤማውያን እኛን ድል ያደርጉ ዘንድ እግዚአብሔር ስለምን ፈቀደላቸው? ከእኛ ጋር በመሄድ ከጠላቶቻችን እጅ ያድነን ዘንድ እንግዲህ እንሂድና የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ከሴሎ እናምጣ።”

4 ስለዚህም ወደ ሴሎ መልእክተኞች ልከው በታቦቱ ላይ ባሉ ኪሩቤል ዙፋኑን ያደረገ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ግርማውን የሚገልጥበትን የቃል ኪዳኑን ታቦት አስመጡ፤ ሁለቱ የዔሊ ልጆች ሖፍኒና ፊንሐስም የቃል ኪዳኑን ታቦት አጅበው መጡ።

5 የቃል ኪዳኑም ታቦት በዚያ ቦታ በደረሰ ጊዜ እስራኤላውያን ምድር እስክትናወጥ ድረስ ታላቅ የእልልታና የሆታ ድምፅ አሰሙ።

6 ፍልስጥኤማውያንም ያንን የእልልታ ድምፅ ሰምተው “በዕብራውያን ሰፈር የምንሰማው ይህ ታላቅ የእልልታ ድምፅ ምን ይሆን?” ተባባሉ፤ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ዕብራውያን ሰፈር መምጣቱንም ባወቁ ጊዜ፥

7 ፈርተው እንዲህ አሉ፦ “ከአማልክት አንዱ ወደ እነርሱ ሰፈር መጥቶአል፤ እንግዲህ ወዮልን! ከዚህ በፊት እንዲህ ያለ ሁኔታ ደርሶብን አያውቅም፤

8 ወዮልን! ከእነዚህ ኀያላን አማልክት እጅ ማን ያድነናል? እነርሱ ግብጻውያንን በበረሓ በተለያዩ መቅሠፍቶች የመቱ ናቸው።

9 ፍልስጥኤማውያን ሆይ! እንግዲህ በርቱ! ጠንክሩ! ይህ ካልሆነ ቀድሞ እነርሱ የእኛ ባሪያዎች እንደ ነበሩ ሁሉ እኛም ደግሞ የዕብራውያን ባርያዎች ሆነን መቅረታችን ነው፤ ስለዚህ በወንድነት ጠንክራችሁ ተዋጉ!”

10 ፍልስጥኤማውያንም በብርቱ ተዋግተው እስራኤላውያንን ድል ነሡ፤ እስራኤላውያንም ወደየድንኳናቸው ሸሹ፤ ታላቅ እልቂት ሆኖ ሠላሳ ሺህ እስራኤላውያን ወታደሮች ተገደሉ፤

11 የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦትም ተማረከ፤ ሁለቱ የዔሊ ልጆች ሖፍኒና ፊንሐስም ተገደሉ።


የዔሊ መሞት

12 ነገዱ ከብንያም ወገን የሆነ አንድ ሰው ከጦር ሜዳ ተነሥቶ በመገሥገሥ በዚያኑ ዕለት ሴሎ ደረሰ፤ ሐዘኑንም ለማሳወቅ ልብሱን ቀዶ በራሱ ላይ ትቢያ ነስንሶ ነበር፤

13 ሰውዬው በደረሰ ጊዜ ልቡ ለእግዚአብሔር ታቦት ተጨንቆ የነበረው ዔሊ በመንገድ ዳር በወንበር ተቀምጦ ይመለከት ነበር። ሰውዬውም ወደ ከተማ መጥቶ ወሬውን በተናገረ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ከፍተኛ ጩኸት አስተጋቡ።

14 ዔሊም የጩኸቱን ድምፅ ሰምቶ “ይህ ሁሉ ጩኸት ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀ፤ ያም ሰው ወሬውን ለዔሊ ለመንገር ቸኲሎ ሄደና ነገረው፤

15 በዚያን ዘመን ዔሊ የዘጠና ስምንት ዓመት ሽማግሌ ነበር፤ ዐይኑም ፈዞ ነበር።

16 ሰውየውም ቀርቦ “እኔ ከጦርነቱ አምልጬ መጣሁ፤ ዛሬም እዚህ የደረስኩት በብርቱ ሩጫ ነው” አለ። ዔሊም “ልጄ ሆይ! ታዲያ እንዴት ሆነ?” አለው።

17 ወሬ ነጋሪውም “እስራኤላውያን ድል ሆነው ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ ይህም ሽንፈት በእኛ ላይ መድረሱ እጅግ አሠቃቂ ነው፤ ከዚህም ሁሉ ጋር ልጆችህ ሖፍኒና ፊንሐስ ተገደሉ፤ የእግዚአብሔርም የቃል ኪዳን ታቦት ተማረከች” ሲል መለሰለት።

18 ወሬ ነጋሪው የቃል ኪዳኑን ታቦት መማረክ ባወሳ ጊዜ ዔሊ በቅጽሩ በር አጠገብ ከተቀመጠበት ወንበር ላይ ተገልብጦ ወደ ኋላው ወደቀ፤ እርሱም ሽማግሌ ከመሆኑም በላይ በውፍረቱ ግዙፍ ስለ ነበር ከአወዳደቁ የተነሣ አንገቱ ተሰብሮ ሞተ፤ ዔሊም በእስራኤል መሪ ሆኖ የቈየበት ዘመን አርባ ዓመት ነበር።


የሟቹ ፊንሐስ ሚስት አሟሟት

19 የፊንሐስ ሚስት የነበረችው የዔሊ ምራት ነፍሰ ጡር ነበረች፤ የምትወልድበትም ጊዜ ተቃርቦ ነበር፤ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት መማረኩን፤ ዐማትዋና ባልዋ መሞታቸውን በሰማች ጊዜ በድንገተኛ ምጥ ተይዛ ወለደች፤ ምጡም ጸንቶባት ነበር፤

20 እርስዋም ለመሞት በምታጣጥርበት ጊዜ በማዋለድ የምትረዳት ሴት “አይዞሽ በርቺ! ወንድ ልጅ ወልደሻል!” አለቻት፤ ነገር ግን አዳምጣ መልስ አልሰጠቻትም፤ አላተኰረችበትምም።

21 እርስዋም በእግዚአብሔር ታቦት መማረክ፥ በዐማትዋና በባልዋ መሞት ምክንያት ክብር ከእስራኤል ተለየ ስትል ልጅዋን ኢካቦድ ብላ ሰየመችው።

22 ቀጥላም “የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት በመማረኩ ምክንያት የእግዚአብሔር ክብር ከእስራኤል ተለየ” አለች።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos