Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


1 ሳሙኤል 31 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የሳኦልና የልጆቹ አሟሟት
( 1ዜ.መ. 10፥1-12 )

1 ፍልስጥኤማውያን በጊልቦዓ ተራራ ከእስራኤላውያን ጋር ጦርነት ገጠሙ፤ ብዙ እስራኤላውያንም ሸሹ፤ ብዙዎችም ተገደሉ።

2 ፍልስጥኤማውያን ግን ተከታትለው ስለ ደረሱባቸው ሦስቱን የሳኦልን ልጆች ዮናታንን፥ አቢናዳብንና ማልኪሹዓን ገደሉአቸው።

3 ጦርነቱ በሳኦል ዙሪያ ስለ በረታ ቀስተኞች ሳኦልን አገኙት፤ ወግተውም በጣም አቈሰሉት፤

4 ጋሻጃግሬው የነበረውንም ወጣት “እነዚህ ያልተገረዙ እኔን ወግተው በመሳለቅ መጫወቻ እንዳያደርጉኝ አንተ ራስህ ሰይፍህን መዘህ ግደለኝ” አለው፤ ወጣቱ ግን ፈርቶ አልገደለውም፤ ስለዚህም ሳኦል ራሱ የገዛ ሰይፉን ወስዶ በስለቱ ላይ ወደቀበት።

5 ወጣቱም ሳኦል እንደ ሞተ ባየ ጊዜ እርሱም በበኩሉ በራሱ ሰይፍ ስለት ላይ ወድቆ ከሳኦል ጋር ሞተ።

6 እንግዲህ ሳኦልና ሦስቱ ወንዶች ልጆቹ እንዲሁም ጋሻጃግሬው የሞቱት በዚህ ዐይነት ሲሆን፥ የሳኦልም ተከታዮች በዚያን ቀን አብረዋቸው ሞቱ።

7 ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅና በኢይዝራኤል ሸለቆ ማዶ የነበሩ እስራኤላውያንም የእስራኤል ሠራዊት መሸሹን፥ ሳኦልና ልጆቹም መገደላቸውን ሰምተው ከተሞቻቸውን እየጣሉ ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ከተሞቹን ያዙ።

8 ከጦርነቱ ቀጥሎ ባለው ቀን ፍልስጥኤማውያን የሟቾቹን ሬሳ ትጥቅ ለመግፈፍ ሄደው ሳኦልንና ሦስቱን ልጆቹን በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወድቀው አገኙአቸው።

9 የሳኦልንም ራስ ቈርጠው የጦር ልብሱንም ገፈው በማስያዝ ለአማልክቶቻቸው መቅደስና ለሕዝባቸው የድሉን ዜና ያበሥሩ ዘንድ መልእክተኞቻቸውን ላኩ።

10 ከዚህ በኋላ ፍልስጥኤማውያን የሳኦልን የጦር መሣሪያዎች ዐስታሮት ተብላ በምትጠራው ሴት አምላካቸው ቤተ መቅደስ ውስጥ አኖሩ። የሳኦልንም ሬሳ ቤትሻን ተብላ በምትጠራው ከተማ ቅጽር ግንብ ላይ በምስማር ቸነከሩት።

11 በገለዓድ የሚኖሩ የያቤሽ ሰዎችም ፍልስጥኤማውያን በሳኦል ላይ ያደረጉበትን ነገር በሰሙ ጊዜ፥

12 ጀግኖቻቸው በድንገት ተነሥተው በመገሥገሥ በሌሊት ወደ ቤትሻን ሄዱ፤ የሳኦልንና የልጆቹን አስከሬን ከከተማይቱ ቅጽር ግንብ ላይ አውርደው ወደ ያቤሽ በማምጣት አቃጠሉአቸው።

13 አጥንቶቻቸውንም በከተማው ውስጥ ታማሪስክ ተብሎ በሚጠራ ዛፍ ሥር ቀብረው ሰባት ቀን ጾሙ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos