1 ሳሙኤል 29 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምፍልስጥኤማውያን ዳዊትን መቃወማቸው 1 እስራኤላውያን በኢይዝራኤል ሸለቆ ውስጥ በሚገኘው ምንጭ አጠገብ ሰፍረው ሳሉ፥ ፍልስጥኤማውያን ወታደሮቻቸውን በአንድነት ሰብስበው በማምጣት በአፌቅ አሰለፉ፤ 2 አምስቱም የፍልስጥኤም ነገሥታት በመቶና በሺህ ከተመደቡ ሰልፈኞቻቸው ጋር ዘመቱ፤ ዳዊትና ተከታዮቹም የአኪሽ ደጀን ጦር ሆነው ዘመቱ፤ 3 የፍልስጥኤም ጦር አዛዦችም እነርሱን ባዩ ጊዜ “እነዚህ ዕብራውያን እዚህ ምን ይሠራሉ?” ሲሉ ጠየቁ። አኪሽም “ይህማ የእስራኤል ንጉሥ ባለሟል የነበረው ዳዊት አይደለምን? እነሆ እርሱ ከእኔ ጋር ሲኖር ብዙ ጊዜው ነው፤ ሳኦልን ከድቶ ወደ እኔ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ሊያሳዝነኝ የሚችል ምንም ዐይነት በደል ሠርቶ አልተገኘም” ሲል መለሰ። 4 ነገር ግን የፍልስጥኤም ጦር አዛዦች በአኪሽ ላይ ተቈጥተው እንዲህ አሉት፤ “ይህን ሰው ቀድሞ ወደ ሰጠኸው ከተማ መልሰው፤ ከእኛ ጋር አብሮ እንዲዘምት አታድርግ፤ ጦርነቱ በሚፋፋምበት ወቅት በእኛ ላይ ሊነሣ ይችላል፤ እርሱ ከጌታው ጋር ለመስማማት የእኛን ሰዎች ከመግደል ሌላ ምን አማራጭ ይኖረዋል? 5 ከዚህስ በቀር ቀደም ሲል ሴቶች ‘ሳኦል ሺህ ገዳይ! ዳዊት ዐሥር ሺህ ገዳይ!’ ብለው እየጨፈሩ የዘፈኑለት ይኸው ዳዊት አይደለምን?” 6 ስለዚህም አኪሽ ዳዊትን ጠርቶ እንዲህ አለው፤ “አንተ ለእኔ ታማኝ ስለ መሆንህ በሕያው አምላክ ስም እምላለሁ፤ ወደዚህም ጦርነት ዘምተህ ብትዋጋ ደስ ባለኝ ነበር፤ ወደ እኔ ከመጣህበት ጊዜ ጀምሮ እኔን ማሳዘን የሚችል በደል ሠርተህ አላገኘሁህም፤ ነገር ግን ሌሎቹ ገዢዎች የአንተን አብሮ መዝመት አልፈቀዱም፤ 7 አሁን እንግዲህ ወደ ኋላ ተመለስ፤ በሰላም ሂድ፤ የፍልስጥኤማውያን ገዢዎች ቅር የሚያሰኝ ምንም ነገር አታድርግ።” 8 ዳዊትም “ጌታዬ ምን በደል ሠራሁ? አንተን ማገልገል ከጀመርኩበት ጊዜ አንሥቶ በደል ካልተገኘብኝ ጌታዬና ንጉሤ የሆንከውን አንተን ተከትዬ በመዝመት ጠላቶችህን መውጋት የማልችለው ስለምንድን ነው?” አለው። 9 አኪሽም ዳዊትን መልሶ እንዲህ አለው፦ “አንተ በእኔ አስተያየት እንደ እግዚአብሔር መልአክ ምንም እንከን የሌለብህ መሆኑን ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን የፍልስጥኤማውያን ገዢዎች ‘ከእኛ ጋር ወደ ጦርነት መዝመት አይችልም’ አሉ። 10 ስለዚህ አንተና ከአንተ ጋር የመጡ የጌታህ አገልጋዮች ነገ ጠዋት ሲነጋጋ በመነሣት ወደ ሰፈራችሁ ተመለሱ” ሲል መለሰለት። 11 ስለዚህም ዳዊትና ተከታዮቹ በማግስቱ ማለዳ ወደ ፍልስጥኤም ተመልሰው ለመሄድ ተነሡ፤ ፍልስጥኤማውያንም ወደ ኢይዝራኤል ዘመቱ። |