Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


1 ሳሙኤል 24 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ዳዊት የሳኦልን ሕይወት ማትረፉ

1 ሳኦል ፍልስጥኤማውያንን ወግቶ ከተመለሰ በኋላ ዳዊት በዔንገዲ አጠገብ በሚገኘው ምድረ በዳ የሚገኝ መሆኑን ሰማ፤

2 ስለዚህም ሳኦል በእስራኤል ምርጥ የሆኑትን ሦስት ሺህ ወታደሮች በማስከተል “የሜዳ ፍየሎች አለት” ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በስተ ምሥራቅ በኩል ዳዊትን አሳዶ ለመያዝ ሄደ፤

3 በመንገድ ዳር ባሉት የበጎች ማደሪያዎች አቅራቢያ ወደሚገኘው ወደ አንድ ዋሻ ወገቡን ሊሞክር ወደ ውስጥ ገባ፤ በዚያም እርሱ ከተቀመጠበት ወደ ውስጥ ገባ ብሎ ዳዊትና ተከታዮቹ ተደብቀው የሚኖሩበት ክፍል ነበር፤

4 ተከታዮቹም ዳዊትን “እነሆ፥ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖልሃል! እግዚአብሔር ጠላትህን በእጅህ እንደሚጥልልህ ነግሮሃል፤ እነሆ፥ አሁን በጠላትህ ላይ የፈለግኸውን ማድረግ ትችላለህ!” አሉት፤ ዳዊትም በልቡ እየተሳበ በመቅረብ ሳኦል ሳያውቅ ከልብሱ ጫፍ ላይ ቈርጦ ወሰደ፤

5 ነገር ግን ዳዊትን የኅሊና ወቀሳ አስጨነቀው፤

6 ስለዚህም ተከታዮቹን “እግዚአብሔር ቀብቶ ባነገሠው በጌታዬ ላይ እጄን ከማንሣት እግዚአብሔር ይጠብቀኝ! እርሱ እግዚአብሔር የመረጠው ንጉሥ ስለ ሆነ እኔ በእርሱ ላይ ምንም ዐይነት ጒዳት ላደርስበት አይገባኝም!” አላቸው።

7 በዚህም አባባሉ በሳኦል ላይ አደጋ እንዳይጥሉበት ዳዊት ተከታዮቹን ከለከላቸው። ሳኦልም ከዚያ በመነሣት ከዋሻው ወጥቶ ሄደ፤

8 ዳዊትም ከዚያ ወጥቶ ሳኦልን በመከተል “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ!” አለው፤ ሳኦልም መለስ ብሎ ዙሪያውን ሲመለከት ዳዊት በመሬት ላይ ለጥ ብሎ እጅ ነሣውና እንዲህ አለው፤

9 “እኔ አንተን ጒዳት እንደማደርስብህ አስመስለው የሚነግሩህን ሰዎች ቃል ስለምን ትሰማለህ?

10 ዛሬ በዚህ ሰዓት በዋሻው ውስጥ ሳለህ እግዚአብሔር በእጄ ጥሎህ እንደ ነበር አንተ ራስህ ማየት ትችላለህ፤ አንዳንድ ሰዎችም እንድገድልህ መክረውኝ ነበር፤ ነገር ግን አንተ ‘እግዚአብሔር የቀባህ ንጉሥ ነህና እኔ በጌታዬ ላይ እጄን አላነሣም’ ብዬ ራራሁልህ፤

11 አባቴ ሆይ! እነሆ፥ ከካባህ ላይ ቈርጬ የያዝኩትን ጨርቅ ተመልከት! ታዲያ እኮ ልገድልህ እችል ነበር፤ ነገር ግን ይህን በማድረግ ፈንታ የልብስህን ጫፍ ቈረጥሁ፤ በአንተ ላይ ለማመፅም ሆነ ወይም በአንተ ላይ ጒዳት ላደርስብህ አለመፈለጌን በዚህ መረዳት ትችላለህ፤ አንተ ግን ምንም ነገር ሳላደርግና ሳልበድልህ እኔን ለመግደል ትከታተለኛለህ።

12 እንግዲህ ስሕተተኛው ማንኛችን እንደ ሆንን በመለየት እግዚአብሔር ፍርዱን ይስጥ! እኔ በአንተ ላይ ምንም ዐይነት ጒዳት ላደርስብህ ስለማልፈልግ በእኔ ላይ ስለምታደርገው ክፉ ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ራሱ ይበቀል።

13 ‘ክፉ ነገርን የሚያደርጉ ክፉ ሰዎች ብቻ ናቸው’ የተባለውን ጥንታዊ አነጋገር ታውቃለህ፤ ስለዚህም እኔ በአንተ ላይ ጒዳት ላደርስብህ አልፈልግም።

14 እነሆ፥ የእስራኤል ንጉሥ ማንን ለመግደል እንደሚጥር ተመልከት! ማንንም እንደሚያሳድድ አስተውል! የሞተ ውሻን ወይስ ቁንጫን? ማንን እንደሚያሳድድ ተመልከት!

15 እግዚአብሔር ይፍረድ፤ ከሁለታችንም ስሕተተኛው ማን እንደ ሆነ እርሱ ይወስን፤ እግዚአብሔር ይህን ጉዳይ ተመልክቶ ይከላከልልኝ፤ ከአንተም እጅ ያድነኝ።”

16 ዳዊትም ይህን ተናግሮ እንደ ጨረሰ ሳኦል “ልጄ ዳዊት ሆይ! በእውነት ይህ የአንተ ድምፅ ነውን?” ብሎ ማልቀስ ጀመረ፤

17 ከዚያም በኋላ ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “አንተ እውነተኛ ሰው ነህ! እኔ ግን ስሕተተኛ ነኝ፤ ይህን የመሰለ በደል ስፈጽምብህ አንተ ለእኔ ቸርነት አድርገህልኛል!

18 እግዚአብሔር በእጅህ ቢጥለኝም እንኳ አንተ አልገደልከኝምና ለእኔ በጎ አድራጊ መሆንህንም ዛሬ አስመስክረሃል።

19 ጠላት በእጁ ገብቶለት ጒዳት ሳያደርስበት የሚለቀው ሰው ከቶ የት ይገኛል? ዛሬ ለእኔ ስላደረግኸው መልካም ነገር እግዚአብሔር ይባርክህ!

20 እነሆ፥ አንተ የእስራኤል ንጉሥ እንደምትሆንና የእስራኤልም መንግሥት በአንተ አገዛዝ ሥር ጸንቶ እንደሚኖር ዛሬ አረጋግጫለሁ።

21 እንግዲህ ስሜና የቤተሰቤ ስም ተደምስሶ እንዳይረሳ ለማድረግና የዘሮቼንም ሕይወት ከጥፋት ለማትረፍ በእግዚአብሔር ስም ማልልኝ።”

22 ዳዊትም ይህን እንደሚያደርግ ማለለት። ከዚህ በኋላም ሳኦል ወደ ቤቱ ተመልሶ ሄደ፤ ዳዊትና ተከታዮቹም ወደሚሸሸጉበት ስፍራ ተመለሱ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos