1 ሳሙኤል 23 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምዳዊት የቀዒላን ከተማ ከጥፋት እንደ አዳነ 1 ፍልስጥኤማውያን በቀዒላ ከተማ ላይ አደጋ መጣላቸውንና በቅርቡ የተሰበሰበውንም የአዲሱን መከር እህል ዘርፈው መውሰዳቸውን ዳዊት ሰማ፤ 2 ስለዚህም ዳዊት “ሄጄ በፍልስጥኤማውያን ላይ አደጋ ልጣልባቸውን?” ሲል የእግዚአብሔርን ፈቃድ ጠየቀ። እግዚአብሔርም “አዎ! በፍልስጥኤማውያን ላይ አደጋ በመጣል ቀዒላን ከጥፋት አድን” ሲል መለሰለት። 3 ነገር ግን የዳዊት ተከታዮች “በዚህ በይሁዳ ስንኖር የምንፈራው ብዙ ነገር አለ፤ አሁን ደግሞ ወደ ቀዒላ ሄደን በፍልስጥኤማውያን ሠራዊት ላይ አደጋ ብንጥል ችግራችን የባሰ ችግር ይገጥመናል!” አሉት። 4 ከዚህም የተነሣ ዳዊት እንደገና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም “እኔ በፍልስጥኤማውያን ላይ ድልን ስለማቀዳጅህ ሄደህ በቀዒላ ላይ አደጋ ጣል” አለው። 5 ስለዚህም ዳዊትና ተከታዮቹ ወደ ቀዒላ ሄደው በፍልስጥኤማውያን ላይ አደጋ ጣሉባቸው፤ ከእነርሱም ብዙዎቹን ገድለው የከብትና የበግ መንጋዎቻቸውን ዘርፈው ወሰዱ፤ በዚህም ዐይነት ዳዊት ከተማይቱን ከጥፋት አዳናት። 6 የአቤሜሌክ ልጅ አብያታር አምልጦ በቀዒላ ከዳዊት ጋር በተባበረ ጊዜ ወደዚያ የመጣው ኤፉዱን እንደ ያዘ ነበር። 7 ለሳኦልም ዳዊት ወደ ቀዒላ መምጣቱ በተነገረው ጊዜ “እግዚአብሔር እርሱን በእጄ ሊጥልልኝ ነው፤ ዳዊት የግንብ ቅጽርና የተመሸጉ የቅጽር በሮች ወዳሉአት ከተማ በመዝለቁ ራሱን በወጥመድ ውስጥ አስገብቶአል” አለ። 8 ስለዚህም ሳኦል ወታደሮቹን ለጦርነት ጠርቶ ወደ ቀዒላ በመዝመት ዳዊትንና ተከታዮቹን እንዲከቡ አዘዘ። 9 ዳዊትም ሳኦል አደጋ ሊጥልበት ማቀዱን በሰማ ጊዜ ካህኑን አብያታርን “ኤፉዱን ይዘህ ና!” አለው። 10 ከዚህም በኋላ ዳዊት እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! በአገልጋይህ በእኔ ሰበብ ሳኦል መጥቶ ቀዒላን ለመደምሰስ ማቀዱን ሰምቻለሁ። 11 ታዲያ፥ የቀዒላ ከተማ ነዋሪዎች እኔን ለሳኦል አሳልፈው ይሰጡኝ ይሆን? ሳኦልስ እኔ እንደ ሰማሁት ወደዚህ መምጣቱ እውነት ነውን? የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! መልስ እንድትሰጠኝ እለምንሃለሁ!” እግዚአብሔርም “አዎ፥ ሳኦል በእርግጥ ይመጣል” ሲል መለሰለት። 12 ዳዊትም “የቀዒላ ከተማ ነዋሪዎችስ ተከታዮቼንና እኔን ለሳኦል አሳልፈው ይሰጡን ይሆን?” ሲል እንደገና ጠየቀ። እግዚአብሔርም “አዎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል” ሲል መለሰ። 13 ስለዚህም ዳዊትና ስድስት መቶ የሚሆኑ ተከታዮቹ በሙሉ ወዲያውኑ ቀዒላን ለቀው ለመሄድ ተንቀሳቀሱ፤ ሳኦልም ዳዊት ከቀዒላ አምልጦ መሄዱን በሰማ ጊዜ የነበረውን ዕቅድ ተወ። ዳዊት በኮረብታማው አገር የነበረበት ሁኔታ 14 ዳዊት በዚፍ አጠገብ ባለው ምድረ በዳ ውስጥ በኮረብታማው አገር ተሸሽጎ ኖረ፤ ሳኦልም እርሱን ለማግኘት ዘወትር ይፈልገው ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ዳዊትን ለሳኦል አሳልፎ አልሰጠውም፤ 15 ዳዊትም ሳኦል ሊገድለው መምጣቱን ተመለከተ። ዳዊት በዚፍ አጠገብ ባለው ምድረ በዳ ውስጥ በሖሬሽ ይገኝ ነበር፤ 16 የሳኦል ልጅ ዮናታንም እዚያው ድረስ ወደ ዳዊት ሄዶ እግዚአብሔር በአስተማማኝ ሁኔታ የሚጠብቀው መሆኑን በመግለጥ እንዲህ እያለ አበረታታው፤ 17 “አይዞህ አትፍራ፤ አባቴ ሳኦል በአንተ ላይ ጒዳት ማድረስ ከቶ አይችልም፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ እንደምትሆንና እኔም ከአንተ የምቀጥል ሁለተኛ ማዕርግ እንደሚኖረኝ አባቴ በደንብ ያውቃል።” 18 ስለዚህ ሁለቱም እርስ በርሳቸው የወዳጅነት ቃል ኪዳን አደረጉ፤ ከዚህም በኋላ ዳዊት በሖሬሽ መኖሩን ቀጠለ፤ ዮናታንም ወደ ቤቱ ተመልሶ ሄደ። 19 ከዚፍ ነዋሪዎች አንዳንዶቹ በጊብዓ ወደሚገኘው ወደ ሳኦል ሄደው እንዲህ አሉ፥ “ዳዊት በእኛ ግዛት ውስጥ ከይሁዳ ምድረ በዳ በስተ ደቡብ ባለው በሐኪላ ተራራ ላይ በምትገኘው በሖሬሽ ተሸሽጎ ይገኛል። 20 ንጉሥ ሆይ፥ አንተ እርሱን በምትፈልግበት ጊዜ ወደ እኛ ና፤ እኛም እርሱን ለአንተ ለንጉሡ አሳልፈን ለመስጠት ኀላፊነትን እንወስዳለን።” 21 ሳኦልም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “ለእኔ ይህን ያኽል ቸርነት ስላደረጋችሁልኝ እግዚአብሔር ይባርካችሁ! 22 አሁንም እንደገና ሄዳችሁ አረጋግጡ፤ ያለበትን ስፍራ ያየውም ማን እንደ ሆነ መርምራችሁ አግኙ፤ እኔ እርሱ ዘዴኛ መሆኑን ሰምቻለሁ፤ 23 የሚሸሸግባቸውን ስፍራዎች በትክክል አግኙ፤ ያገኛችሁትንም ማስረጃ ወዲያው ይዛችሁልኝ ኑ፤ ከዚያም በኋላ እኔ አብሬአችሁ እሄዳለሁ፤ አሁንም በዚያው ግዛት ውስጥ የሚኖር ከሆነ መላውን የይሁዳ ግዛት ማሰስ ቢያስፈልገኝም እንኳ እርሱን በማደን እይዘዋለሁ።” 24 ስለዚህም እነርሱ ሳኦል ከመሄዱ በፊት ወደ ዚፍ ተመለሱ፤ በዚህን ጊዜ ዳዊትና ተከታዮቹ ከይሁዳ ምድረ በዳ በስተ ደቡብ በኩል በሚገኘው በማዖን በረሓ ነበሩ፤ 25 ሳኦልና ወታደሮቹም ዳዊትን ለማሳደድ ወጥተው ሄዱ፤ ዳዊትም ይህን ስላወቀ በማዖን ምድረ በዳ አለት ወደበዛበት አንድ ኮረብታ አልፎ በዚያ ተቀመጠ፤ ሳኦልም ይህን በሰማ ጊዜ ዳዊትን የመከታተል ተግባሩን ቀጠለ፤ 26 ሳኦልና ወታደሮቹ ከኮረብታው በአንድ በኩል ሲሆኑ፥ ዳዊትና ተከታዮቹም ከኮረብታው በሌላ በኩል ነበሩ፤ ዳዊትና ተከታዮቹም ሊማርኩአቸው ከተቃረቡት ከሳኦልና ከወታደሮቹ ለማምለጥ በመጣደፍ ላይ ነበሩ። 27 ይህ በዚህ እንዳለ ወዲያውኑ አንድ መልእክተኛ ደርሶ ሳኦልን “ፍልስጥኤማውያን አገሪቱን በመውረር ላይ ናቸውና አሁኑኑ ፈጥነህ ተመልሰህ ና!” አለው። 28 ስለዚህም ሳኦል ዳዊትን የማሳደድ ተግባሩን አቁሞ ፍልስጥኤማውያንን ለመውጋት ሄደ፤ ያም ቦታ “የማምለጥ አለት” ተብሎ የተጠራበት ምክንያት ይኸው ነው። 29 ዳዊትም ከዚያ በመነሣት ተሸሽጎ ወደቈየበት ዔንገዲ ተብሎ ወደሚጠራው ስፍራ ሄደ። |