Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


1 ሳሙኤል 22 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ዳዊት በዓላምና በምጽጳ

1 ዳዊት ከጋት ከተማ ሸሽቶ በዐዱላም ከተማ አጠገብ ወደሚገኝው ወደ አንድ ዋሻ ሄደ፤ ወንድሞቹና ሌሎቹም ቤተሰቦቹ ይህን በሰሙ ጊዜ ወደዚያ ሄደው ከእርሱ ጋር ተቀላቀሉ፤

2 የተጨነቁ፥ ዕዳ ያለባቸው፥ እንዲሁም ሆድ የባሳቸው አንዳንድ ሰዎች ወደ እርሱ ስለ ሄዱ ብዛታቸው በድምሩ እስከ አራት መቶ ደረሰ፤ ዳዊትም የእነርሱ መሪ ሆነ።

3 ዳዊትም ከዚያ ተነሥቶ በሞአብ ወደምትገኘው ወደ ምጽጳ ሄደ፤ የሞአብንም ንጉሥ “እግዚአብሔር ለእኔ የሚያደርግልኝን ነገር እስካውቅ ድረስ እባክህ አባቴና እናቴ መጥተው በአንተ ዘንድ እንዲቈዩ ፍቀድላቸው” ሲል ጠየቀው።

4 በዚህም ዐይነት ወላጆቹን በሞአብ ንጉሥ ዘንድ ተዋቸው፤ እነርሱም ዳዊት እየተደበቀ በሚኖርበት ዘመን ሁሉ በዚያው ቈዩ።

5 ከዚህ በኋላ ነቢዩ ጋድ ወደ ዳዊት መጥቶ “በዚህ አትቈይ፤ አሁኑኑ ፈጥነህ ወደ ይሁዳ ሂድ” ሲል ነገረው፤ ስለዚህም ዳዊት ከዚያ ተነሥቶ ወደ ሔሬት ጫካ ገባ።


የካህናት መገደል

6 ከዕለታት አንድ ቀን ሳኦል ጦሩን በእጁ እንደ ያዘ በጊብዓ በሚገኝ ኮረብታ ላይ ታማሪስክ ተብሎ በሚጠራ ዛፍ ሥር ተቀምጦ ነበር፤ ባለሟሎቹ የሆኑ ባለሥልጣኖችም በዙሪያው ቆመው ነበር፤ በዚህን ጊዜ ዳዊትና ተከታዮቹ በአንድ ስፍራ መኖራቸው ለሳኦል ተነገረው፤

7 ሳኦልም ባለሟሎችን እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የብንያም ሰዎች አድምጡኝ! በውኑ የእሴይ ልጅ ዳዊት ለሁላችሁም ለእያንዳንዳችሁ የእርሻ መሬትና የወይን ተክል ቦታ የሚሰጣችሁና በሠራዊቱም ውስጥ ሻለቆችና የመቶ አለቆች አድርጎ የሚሾማችሁ ይመስላችኋልን?

8 በእኔስ ላይ ሤራ የምታካሄዱት ስለዚህ ነውን? የገዛ ልጄ ከእሴይ ልጅ ጋር መተባበሩን የነገረኝ ከእናንተ አንድ እንኳ የለም፤ ስለ እኔ የሚያስብ ከቶ ማንም የለም፤ ወይም ዛሬ እንደሚያደርገው ሁሉ አገልጋዬ በእኔ ላይ እንዲሸምቅ ልጄ ያነሣሣው መሆኑን ከእናንተ ማንም የነገረኝ የለም።”

9 በዚህን ጊዜ ከባለሥልጣኖቹ ጋር ኤዶማዊው ዶይቅ እዚያ ቆሞ ስለ ነበር “እኔ የእሴይን ልጅ በኖብ ወደሚገኘው የአሒጡብ ልጅ ወደ ሆነው ወደ አቤሜሌክ በመጣ ጊዜ አይቼዋለሁ፤

10 ዳዊትም ምን ማድረግ እንደሚገባው አቤሜሌክ እግዚአብሔርን ጠይቆለታል፤ ከዚያም በኋላ ለዳዊት ጥቂት ምግብና የፍልስጥኤማዊውን የጎልያድን ሰይፍ ሰጥቶታል” ሲል ተናገረ።

11 ስለዚህም ንጉሥ ሳኦል ወደ ካህኑ የአሒጡብ ልጅ ወደ ሆነው ወደ አቤሜሌክና በኖብ ወደሚገኙት ዘመዶቹ ወደሆኑት ካህናት ሁሉ መልእክት ላከ፤ እነርሱም መጡ፤

12 ሳኦልም፥ “የአሒጡብ ልጅ ሆይ! እንግዲህ ስማ” አለው። አቤሜሌክም “እነሆኝ ጌታ ሆይ!” ብሎ መለሰ።

13 ሳኦልም “አንተና የእሴይ ልጅ በእኔ ላይ ያሤራችሁት ስለምንድን ነው? ለእርሱ ምግብና ሰይፍ ሰጥተኸዋል እግዚአብሔርንም ጠይቀህለታል፤ እነሆ፥ እርሱ አሁን በእኔ ላይ በጠላትነት ተነሥቶ እኔን ለመግደል አጋጣሚ ጊዜ በመፈለግ ላይ ነው” ሲል ጠየቀው።

14 አቤሜሌክም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ዳዊት ለአንተ የታመነ የጦር መኰንን ነው፤ የአንተው የራስህ ዐማች ከመሆኑም ሌላ የክብር ዘብህ አዛዥ ነው፤ በቤተ መንግሥትህም አደባባይ እንደ እርሱ የሚከበር ማን አለ?

15 በውኑ እግዚአብሔርን ስለ እርሱ መጠየቅ ይህ ዛሬ የመጀመሪያ ጊዜዬ ነውን? አይደለም! ንጉሥ ሆይ! እኔን አገልጋይህንም ሆነ ቤተሰቤን በዚህ ጉዳይ ላይ አትውቀስ፤ ስለዚህ ጉዳይ ይብዛም ይነስም እኔ የማውቀው ነገር የለም።”

16 ንጉሡም “አቤሜሌክ ሆይ! አንተና መላው ዘመዶችህ ሞት ይገባችኋል!” አለው።

17 ከዚህም በኋላ ሳኦል በአጠገቡ ወደቆሙት ዘብ ጠባቂዎች መለስ ብሎ “እነዚህን የእግዚአብሔርን ካህናት ግደሉ! እነርሱ ከዳዊት ጋር በእኔ ላይ ዐምፀውብኛል፤ እንዲሁም ሁሉን ነገር እያወቁ ዳዊት መኰብለሉን እንኳ አልነገሩኝም” አላቸው፤ ዘብ ጠባቂዎቹ ግን “የእግዚአብሔርን ካህናት አንገድልም” አሉ።

18 ስለዚህም ሳኦል ዶይቅን “አንተው ግደላቸው!” አለው፤ ኤዶማዊው ዶይቅም ተነሥቶ ሁሉንም ገደለ፤ በዚያኑ ቀን የፈጃቸው ኤፉድ የሚለብሱ ካህናት ብዛት ሰማኒያ አምስት ነበር፤

19 ከዚህም በኋላ ሳኦል የካህናት ከተማ በሆነችው በኖብ የሚኖሩት ሁሉ ወንዶችና ሴቶች፥ ልጆችና ሕፃናት፥ የቀንድ ከብቶችና አህዮች፥ እንዲሁም የበግ መንጋዎች ሁሉ እንዲገደሉ አደረገ።

20 ነገር ግን አብያታር የሚባል ከአቤሜሌክ ወንዶች ልጆች አንዱ ብቻ አምልጦ በመሄድ ከዳዊት ጋር ተቀላቀለ፤

21 ሳኦል የእግዚአብሔርን ካህናት እንዴት እንደ ፈጀም ለዳዊት ነገረው፤

22 ዳዊትም አብያታርን “እኔ በዚያ ቀን ኤዶማዊውን ዶይቅን እዚያ ባየሁት ጊዜ ሁሉን ነገር ለሳኦል እንደሚነግረው ዐውቄ ነበር፤ ከዚህም የተነሣ ስለ ዘመዶችህ ሁሉ እልቂት እኔ ተጠያቂነት አለብኝ፤

23 አንተ ግን ከእኔ ጋር ኑር፤ አይዞህ አትፍራ፤ በእርግጥ ሳኦል አንተንም እኔንም ለመግደል ይፈልጋል፤ ነገር ግን አንተ ከእኔ ጋር በሰላም ትኖራለህ” አለው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos