Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


1 ሳሙኤል 21 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ዳዊት ከሳኦል ፊት ሸሽቶ መሄዱ

1 ዳዊት በኖብ ወደሚገኘው ወደ ካህኑ አቤሜሌክ ዘንድ ሄደ፤ አቤሜሌክም በፍርሃት እየተንቀጠቀጠ ሊቀበለው ወጥቶ “ማንም ሰው ሳይከተልህ ብቻህን ስለምን ወደዚህ መጣህ?” ሲል ጠየቀው።

2 ዳዊትም ለካህኑ ለአቢሜሌክ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔ እዚህ የመጣሁት የንጉሥ ሳኦልን ተልእኮ ለመፈጸም ነው፤ እኔ ወደዚህ የተላክሁበትን ጉዳይ ለማንም ሰው እንዳልገልጥ ንጉሡ አዞኛል፤ ተከታዮቼንም በአንድ ቦታ እንድንገናኝ አዝዣቸዋለሁ፤

3 ታዲያ አሁን ምን ምግብ ትሰጠኛለህ? አምስት እንጀራ ወይም ያለህን ሌላ ነገር ስጠኝ።”

4 ካህኑም “ከተቀደሰው ኅብስት በቀር ሕዝብ የሚመገበው እንጀራ የለኝም፤ ተከታዮችህ በቅርቡ ከሴቶች ጋር ሳይገናኙ ተቈጥበው በንጽሕና የቈዩ ከሆኑ፥ ይህን ኅብስት መብላት ይችላሉ” ሲል መለሰለት።

5 ዳዊትም ለካህኑ መልሶ “ከብላቴኖቼ ጋር ወደ ተልእኮ በምሄድበት ጊዜ ሁሉ ከሴቶች እንርቃለን፤ ተራ ተልእኮ እንኳ በምናደርግበት ጊዜ ብላቴኖቼ ንጽሕናቸውን ይጠብቃሉ። ዛሬማ ምንኛ የበለጠ ቅዱሳን መሆን ይገባቸዋል?”

6 ስለዚህም ካህኑ የተቀደሰውን ኅብስት አንሥቶ ለዳዊት ሰጠው፤ ካህኑ ያለው ምግብ ለእግዚአብሔር መባ ሆኖ የቀረበው ኅብስት ብቻ ነበር፤ ይህም ኅብስት ከተቀደሰው ጠረጴዛ ላይ ተነሥቶ በሌላ አዲስ ኅብስት የተተካ ነበር።

7 የሳኦል እረኞች አለቃ የሆነው ኤዶማዊው ዶይቅ በዚያኑ ቀን ሃይማኖታዊ ሥርዓትን ለመፈጸም በዚያ ተገኝቶ ነበር።

8 ዳዊትም አቤሜሌክን “የምትሰጠኝ ጦር ወይም ሰይፍ በአንተ ዘንድ ይገኛልን? የንጉሡ ትእዛዝ አስቸኳይ ስለ ሆነ ጦሬንም ሆነ ሌላውንም መሣሪያዬን ለመያዝ ጊዜ አላገኘሁም ነበር” አለው።

9 አቤሜሌክም “በኤላ ሸለቆ የገደልከው የፍልስጥኤማዊው የጎልያድ ሰይፍ በእኔ ዘንድ አለ፤ እርሱም ከኤፉዱ በስተኋላ በጨርቅ ተጠቅሎ ተቀምጦአል፤ የምትፈልገው ከሆነ ውሰደው፤ በዚህ የሚገኝ የጦር መሣሪያ እርሱ ብቻ ነው” አለው። ዳዊትም “እርሱኑ ስጠኝ! ከእርሱ የተሻለ ሰይፍ የትም አይገኝም” አለው።

10 ዳዊትም ከሳኦል በመሸሽ አኪሽ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ጋት ንጉሥ ሄደ፤

11 የንጉሡ ባለሟሎች የሆኑት ባለሥልጣኖች “ይህ በአገሩ የነገሠው ዳዊት አይደለምን? ‘ሳኦል ሺህ ገዳይ! ዳዊት ዐሥር ሺህ ገዳይ!’ እያሉ ሴቶች በጭፍራ የዘፈኑለት እርሱ አይደለምን?” ሲሉ አኪሽን ጠየቁት።

12 በእነርሱም አነጋገር የዳዊት ልብ በብርቱ ተነካ፤ ንጉሥ አኪሽንም በብርቱ ፈራ።

13 በፊታቸው ጠባዩን ለወጠ፤ ከእነርሱ ጋር እያለም ራሱን እብድ አስመሰለ፤ በበሩ መዝጊያ ላይ ቧጠጠ፤ ለሐጩንም በጺሙ ላይ እንዲዝረከረክ አደረገ።

14 አኪሽም ባለሟሎቹ ለሆኑት ባለሥልጣኖች “እነሆ! ይህ ሰው እብድ ነው! ታዲያ፥ ስለምን ወደ እኔ አመጣችሁት?

15 በእኔ ዘንድ እንዲያብድ ወደ እኔ ይህን ሰው ያመጣችሁት፥ እኔ እብድ አጥቼ ነውን? ይህ ሰው ወደ ቤቴ መግባት አለበትን?” አላቸው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos