1 ሳሙኤል 20 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምዮናታን ዳዊትን እንደ ረዳ 1 ከዚህ በኋላ ዳዊት በራማ ከምትገኘው ከናዮት በመሸሽ ወደ ዮናታን ሄዶ “ከቶ ምን አደረግሁ? ምንስ ወንጀል ፈጸምኩ? አባትህ ለመግደል የሚፈልገኝስ ምን በድየው ነው?” ሲል ጠየቀው። 2 ዮናታንም “ይህንንስ ከአንተ ያርቀው! አትሞትም፤ ትልቅም ሆነ ትንሽ አባቴ ከእኔ የሚሰውረው ነገር የለም፤ ይህንንም ነገር ቢሆን አባቴ ከእኔ አይሰውርም በፍጹም አይደረግም!” አለው። 3 ዳዊት ግን “አባትህ አንተ እኔን ምን ያኽል እንደምትወደኝ በደንብ ያውቃል፤ ስለዚህም ዕቅዱን አንተ እንድታውቅበት ላለማድረግ ወስኖአል፤ ይህንንም የሚያደርገው አንተ ይህን ብታውቅ በብርቱ እንደምታዝን ስለሚያውቅ ነው፤ በሕያው እግዚአብሔር ስምና በነፍስህ እምላለሁ፤ ከአሁን ወዲያ ወደ ሞት ለመድረስ የቀረችን አንዲት ዕርምጃ ብቻ ናት!” አለው። 4 ዮናታንም “አንተ የምትፈልገውን ሁሉ አደርግልሃለሁ” አለው። 5 ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ነገ አዲስ ጨረቃ የምትታይበት በዓል ነው፤ እኔም ከንጉሡ ጋር መብላት ይኖርብኛል፤ እስከ ነገ ወዲያ ምሽት ድረስ እንድደበቅ ፍቀድልኝ” አለው። 6 “ምናልባት አባትህ ቢፈልገኝ በቤተሰቡ ዓመታዊ በዓል የሚከበር ስለ ሆነ ወደ ቤተልሔም እንዲሄድ እፈቅድለት ዘንድ ዳዊት እኔን አጥብቆ ለምኖኛል ብለህ ንገረው። 7 ንጉሡም ‘እሺ’ ቢል፥ እኔ አገልጋይህ በሰላም እንደምኖር ዐውቃለሁ፤ ንጉሡ ከተቈጣ ግን ጒዳት ሊያደርስብኝ የወሰነ መሆኑን ታውቃለህ፤ 8 በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ስለ ተማመንን የሰጠኸኝን የተቀደሰ ተስፋ በመጠበቅ እባክህ ለእኔ ለአገልጋይህ መልካም ነገር አድርግልኝ፤ ወንጀለኛ ሆኜ ከተገኘሁ ግን አንተው ራስህ ግደለኝ እንጂ እንዲገድለኝ ወደ አባትህ ለምን ትወስደኛለህ?” 9 ዮናታን ግን “እንዲህ ያለውን ነገር ፈጽሞ አታስብ! በአንተ ክፉ ነገር አስቦ ቢሆን ኖሮ፥ እነግርህ አልነበረም?” አለው። 10 ዳዊትም “ታዲያ አባትህ ስለ እኔ ክፉ ቃል ቢናገር ማን ያስረዳኛል?” ሲል ጠየቀ። 11 ዮናታንም “ና! ወደ ሜዳ እንሂድ!” ሲል መለሰለት፤ ሁለቱም ወደ ሜዳ ወጡ። 12 ዮናታን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ነገ በዚህ ሰዓት ወይም በሦስተኛው ቀን ስለ አንተ መልካም አስተሳሰብ ያለው መሆኑን አባቴን ጠይቄ ከተረዳሁ በኋላ ስለዚሁ ጉዳይ የሚገልጥልህ መልእክተኛ እልክብሃለሁ፤ ለዚህም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ምስክር ይሁን! 13 አንተን ለመጒዳት የሚፈልግ ከሆነ ግን፥ ስለ እርሱ ባልገልጥልህና አንተም በሰላም እንድታመልጥ ባላደርግ አባቴ በአንተ ላይ ሊያደርግ ያሰበውን ክፉ ነገር እግዚአብሔር በእኔ ላይ ያድርሰው። እግዚአብሔር ከአባቴ ጋር እንደ ነበር ከአንተም ጋር ይሁን፤ 14-15 በሕይወት ብኖር እግዚአብሔር የሚወድደውን ታማኝ ፍቅር አሳየኝ፤ ብሞት ግን እግዚአብሔር የአንተን የዳዊትን ጠላቶች ሁሉ ከገጸ ምድር በሚያጠፋበት ጊዜ ታማኝ የሆነውን ፍቅርህን ከቤተሰቤም አታቋርጥ፥ 16 ይህ የገባነው ቃል ኪዳን ለዘለቄታው እንደ ተጠበቀ ይኑር፤ ይህን ቃል ኪዳን ብታፈርስ ግን እግዚአብሔር ይፈርድብሃል።” 17 ዮናታን ዳዊትን እንደ ራሱ አድርጎ ይወደው ስለ ነበር “በእርግጥ እንደምትወደኝ ለመግለጥ እንደገና ማልልኝ” አለው። 18 ከዚህ በኋላ ዮናታን እንዲህ አለው “ነገ አዲስ ጨረቃ የምትታይበት በዐል ነው፤ መቀመጫህ ባዶ ስለሚሆን በማእድ ላይ አለመኖርህ ይታወቃል፤ 19 ከነገ ወዲያ ወደ ማታ ጊዜ ከዚህ በፊት ይህ ችግር ሲጀመር ወደ ተደበቅህበት ቦታ ሄደህ ከኤጼል ድንጋይ በስተጀርባ ተሸሸግ፤ 20 እኔም ወደ ጎኑ ዒላማ በማስመሰል ሦስት ፍላጻዎችን እወረውራለሁ፤ 21 ከዚያም በኋላ ፍላጻዎቹን እንዲያመጣ ልጁን እልካለሁ፤ ‘ፍላጻዎቹ ከአንተ ወደዚህ ናቸውና አምጣቸው!’ ካልሁት አንተ ከተደበቅኽበት ቦታ ልትወጣ ትችላለህ፤ ስለዚህ ምንም ችግር እንደማይደርስብህና ምንም አደጋ እንደሌለ በእግዚአብሔር ስም እምልልሃለሁ። 22 ነገር ግን ልጁን እነሆ! ‘ፍላጻዎቹ ከአንተ ወዲያ ናቸው!’ ያልኩት እንደ ሆነ እግዚአብሔር አሰናብቶሃልና መንገድህን ሂድ። 23 እርስ በርሳችን የገባነውን ቃል ኪዳን ለዘለዓለም እንደምንጠብቀው እግዚአብሔር ምስክራችን ነው። ” 24 ስለዚህም ዳዊት በዱር ተደብቆ ቈየ፤ አዲስ ጨረቃ በምትታይበት በዓል ሳኦል ግብሩን ለማብላት ተቀመጠ፤ 25 ከግድግዳው ጥግ በተለመደው የክብር ስፍራ ሲቀመጥ፥ አበኔር ከእርሱ ቀጥሎ ተቀመጠ፤ ዮናታንም በንጉሡ ፊት ለፊት ተቀምጦ ነበር፤ በዚህ ጊዜ የዳዊት ወንበር ባዶ ነበር፤ 26 ይሁን እንጂ ሳኦል በዚያን ቀን ምንም ቃል አልተናገረም፤ ሳኦል ስለ ዳዊት ሲያስብ “ምናልባት አንድ ነገር ገጥሞት ይሆናል፤ ወይም በሕጉ መሠረት በሥርዓት አልነጻም ይሆናል” በማለት ያሰላስል ነበር፤ 27 አዲስ ጨረቃ የታየችበት በዓል ካለፈ በኋላም በተከታዩ ቀን የዳዊት ወንበር ባዶ ነበር፤ ስለዚህ ሳኦል ልጁን ዮናታንን “የእሴይ ልጅ ትናንትም፥ ዛሬም ወደዚህ ግብዣ ያልመጣው ስለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። 28 ዮናታንም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ዳዊት ወደ ቤተልሔም ይሄድ ዘንድ እንድፈቅድለት አጥብቆ ለመነኝ፤ 29 ‘የእኛ ቤተሰብ በከተማው ውስጥ መሥዋዕት ስለሚያቀርብና ወንድሜም በዚያ እንድገኝ ስላዘዘኝ በአንተ ዘንድ ሞገስን አግኝቼ ከሆነ እባክህ ፍቀድልኝና ወንድሞቼን ለማየት ልሂድ’ ብሎ ጠይቆኝ ነበር፤ በዚህ ምክንያት በንጉሡ ግብር ላይ አልተገኘም።” 30 የሳኦልም ቊጣ በዮናታን ላይ ነድዶ እንዲህ አለ፤ “አንተ የጠማማና የዐመፀኛ ሴት ልጅ! በራስህ ላይ ኀፍረትንና በእናትህም ላይ ውርደትን ለማምጣት ከእሴይ ልጅ ጋር መወዳጀትህን ደኅና አድርጌ ዐውቃለሁ! 31 የእሴይ ልጅ በሕይወት እስካለ ድረስ አንተና መንግሥትህ ጸንታችሁ ለመኖር እንደማትችሉ አታውቅምን? አሁን ሄደህ አምጣው! እርሱ በሞት መቀጣት አለበት!” 32 ዮናታንም ለአባቱ ለሳኦል “ስለምን ይሞታል? ምንስ አደረገ?” ሲል መለሰ። 33 ከዚህም የተነሣ ዮናታንን ለመግደል የያዘውን ጦር ወረወረበት፤ ስለዚህም ዮናታን አባቱ ሳኦል ዳዊትን ለመግደል ቊርጥ ውሳኔ ማድረጉን አረጋገጠ፤ 34 ዮናታንም በቊጣ ከማእዱ ላይ ተነሣ፤ በዚያ ቀን ማለትም አዲስ ጨረቃ በታየችበት በዓል በሁለተኛ ቀን ምንም ምግብ አልበላም፤ ሳኦል ዳዊትን በማዋረዱ ምክንያት ስለ ዳዊት ሁኔታ ዮናታን በብርቱ አዝኖ ነበር። 35 በማግስቱ ጠዋት በቀጠሮአቸው መሠረት ዮናታን ዳዊትን ለማግኘት ወደ ሜዳ ሄደ፤ ሲሄድም አንድ ትንሽ ልጅ አስከትሎ ነበር፤ 36 ልጁንም “ፈጥነህ ሂድና የምወረውራቸውን ፍላጻዎች ፈልገህ አምጣልኝ” አለው፤ ልጁም ሲሮጥ ዮናታን ከዚያ ልጅ ፊት አሳልፎ አንድ ፍላጻ ወረወረ፤ 37 ያም ልጅ ፍላጻው ባረፈበት ቦታ በደረሰ ጊዜ ዮናታን “ፍላጻው አልፎህ ሄዶአል! 38 እዚያ ዝም ብለህ አትቁም! ፈጠን በል!” ሲል ጮኸበት፤ ልጁም ፍላጻውን አንሥቶ ወደ ጌታው ተመለሰ፤ 39 ይህን ምሥጢር የሚያውቁት ዮናታንና ዳዊት ብቻ ነበሩ እንጂ ልጁ ምንም አያውቅም ነበር። 40 ዮናታንም ያንን ልጅ “መሣሪያዎቼን ይዘህ ወደ ከተማ ተመለስ” አለው። 41 ልጁም ከሄደ በኋላ ዳዊት ከድንጋዩ ቊልል በስተኋላ ከተደበቀበት ስፍራ ወጥቶ በጒልበቱ በመንበርከክ ሦስት ጊዜ ወደ መሬት ሰገደ፤ እርሱና ዮናታን በሚሳሳሙበት ጊዜ ሁለቱም ያለቅሱ ነበር፤ ከዮናታንም ይልቅ የዳዊት ሐዘን የበረታ ነበር። 42 ከዚህ በኋላ ዮናታን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “በሰላም ሂድ፤ እኔና አንተ በዘሬና በዘርህ መካከል እግዚአብሔር ለዘለዓለም ይሁን ብለን በእግዚአብሔር ስም ተማምለናል።” ዳዊት ተነሥቶ ሄደ፤ ዮናታንም ወደ ከተማ ተመለሰ። |