1 ሳሙኤል 14 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምዮናታን በፍልስጥኤማውያን ላይ በቈራጥነት የጣለው አደጋ 1 አንድ ቀን የሳኦል ልጅ ዮናታን የጦር መሣሪያ የሚሸከምለትን ወጣት ጋሻ ጃግሬውን “ወደ ፍልስጥኤማውያን የጦር ሰፈር እንሻገር” አለው። ነገር ግን ዮናታን ይህን ጉዳይ ለአባቱ እንኳ አልነገረውም፤ 2 በዚህ ጊዜ ሳኦል ከጊብዓ በጣም ሳይርቅ በሚግሮን በአንድ የሮማን ዛፍ ሥር ሰፍሮ ነበር፤ ከእርሱም ጋር ስድስት መቶ ያኽል ጭፍሮች ነበሩ፤ 3 በሴሎ የእግዚአብሔር ካህን የነበረው የዔሊ ልጅ ካህኑ ፊንሐስ የወለደው የኢካቦድ ወንድም የአሒጡብ ልጅ አኪያ ኤፉድ ለብሶ ከእርሱ ጋር አብሮ ነበር። እነርሱም ዮናታን ወዴት እንደ ሄደ አላወቁም ነበር። 4 ዮናታን ወደ ፍልስጥኤማውያን ሰፈር ለመድረስ በሚክማስ መተላለፊያ መውጣት ነበረበት፤ በመተላለፊያውም ከግራና ከቀኝ ሁለት ሾጣጣ አለቶች ሲኖሩ የአንደኛው አለት ስም ቦጼጽ፥ የሁለተኛውም ስም ሴኔ ተብሎ ይጠራል፤ 5 ከአለቶቹም አንዱ ከመተላለፊያው በስተ ሰሜን በኩል በሚክማስ ፊት ለፊት የሚገኘው ሲሆን፥ ሁለተኛውም በስተደቡብ በኩል በጌባዕ ፊት ለፊት ይገኝ ነበር። 6 ዮናታን ጋሻ ጃግሬ የሆነውን ወጣት “ና ወደ እነዚያ ወደ አልተገረዙት ወገኖች የጦር ሰፈር እንሻገር እግዚአብሔር ይረዳን ይሆናል፤ በብዙም ሆነ በጥቂት እግዚአብሔር ማዳን አይሳነውም” አለው። 7 ወጣቱም ጋሻጃግሬ “የምትፈቅደውን ነገር ሁሉ አድርግ፤ እኔ ከአንተ አልለይም፤ በሙሉ ልቤም ከአንተ ጋር ነኝ” አለው። 8 ዮናታንም እንዲህ አለው፤ “እሺ እንግዲያውስ ወደ ማዶ እንሻገርና ለፍልስጥኤማውያን ፊት ለፊት እንታያቸው፤ 9 እነርሱም ‘ወደ እናንተ እስክንመጣ ድረስ በዚያ ጠብቁን’ ቢሉን፥ ባለንበት እንቈያለን፤ 10 ነገር ግን ‘ወደ እኛ ኑ’ ቢሉን፥ ወደ እነርሱ እንሄዳለን፤ ይህም እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ላይ ድልን የሚያቀዳጀን ለመሆኑ ምልክት ይሆንልናል።” 11 እነርሱም ወጣ ብለው ለፍልስጥኤማውያን ታዩአቸው፤ ፍልስጥኤማውያንም “እነሆ! አንዳንድ ዕብራውያን ከተሸሸጉበት ጒድጓድ በመውጣት ላይ ናቸው!” ተባባሉ፤ 12 ከዚህ በኋላ ፍልስጥኤማውያን ዮናታንንና ጋሻጃግሬውን ጠርተው “የምንነግራችሁ ጉዳይ ስላለን ወደዚህ እኛ ወዳለንበት ኑ!” አሉአቸው። ዮናታንም ጋሻጃግሬውን “እንግዲህ ተከተለኝ፤ እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ላይ ድልን ለእስራኤል ይሰጣል” አለው፤ 13 ዮናታንም በእጁና በጒልበቱ እየዳኸ ወደ አፋፉ ወጣ፤ ጋሻጃግሬውም ተከተለው፤ ዮናታንም በፍልስጥኤማውያን ላይ ድንገተኛ አደጋ በመጣል መታቸው፤ ጋሻጃግሬውም ገደላቸው። 14 በመጀመሪያውም ግድያ በአንድ የእርሻ ክልል ላይ ኻያ ያኽል ሰዎችን ገደሉ፤ 15 በገጠር የነበሩ ፍልስጥኤማውያንም ሁሉ ተሸበሩ፤ አደጋ ጣዮችና በሰፈር የነበሩ ወታደሮችም ሁሉ በፍርሃት ተንቀጠቀጡ፤ እግዚአብሔር በላከባቸውም አስጨናቂ ሽብር መሬት ተንቀጠቀጠች። የፍልስጥኤማውያን መሸነፍ 16 የሳኦል ወታደሮች የብንያም ግዛት በሆነችው በጊብዓ መሽገው ሁኔታውን ሁሉ በመጠባበቅ ላይ ሳሉ በመታወክ የሚሸሹትን ፍልስጥኤማውያን አዩ። 17 ስለዚህም ሳኦል “እስቲ ወታደሮችን ቊጠሩና ከእኛ መካከል የጐደሉ እንዳሉ አረጋግጡ” ብሎ አዘዘ፤ በትእዛዙም መሠረት ሠራዊቱን በቈጠሩ ጊዜ ዮናታንና ጋሻጃግሬው አለመኖራቸው ታወቀ። 18 ሳኦልም ካህኑን አኪያን “ኤፉዱን ይዘህ ና” አለው። በዚያን ቀን ካህኑ አኪያ ኤፉድ ለብሶ በእስራኤል ሕዝብ ፊት ነበር፤ 19 ሳኦል ከካህኑ ጋር በመነጋገር ላይ ሳለ፥ በፍልስጥኤማውያን ሰፈር የተነሣው ሁከትና ሽብር እየባሰበት ሄደ፤ ሳኦልም ካህኑን “እግዚአብሔርን ለመጠየቅ አሁን ጊዜ የለንም” አለው። 20 ከዚህ በኋላ ሳኦልና ወታደሮቹ ካሉበት በመንቀሳቀስ ወደ ውጊያው ሄዱ፦ እዚያም ፍልስጥኤማውያን ግራ በመጋባት እርስ በርሳቸው በሰይፍ ይጋደሉ ነበር። 21 ከፍልስጥኤማውያን ጋር በመተባበር ወደ ጦሩ ሰፈር ሄደው የነበሩ አንዳንድ ዕብራውያንም ፍልስጥኤማውያንን ከድተው ከሳኦልና ከዮናታን ጋር ተባበሩ። 22 በኤፍሬም ኮረብታዎች ተደብቀው የነበሩ ሌሎች እስራኤላውያንም ፍልስጥኤማውያን በሽሽት ላይ መሆናቸውን ሰሙ፤ ስለዚህም ከወገን ጦር ጋር ተባብረው ፍልስጥኤማውያንን ማሳደድ ጀመሩ፤ 23 እስከ ቤትአዌን ከተማ ማዶ ባለው መንገድ ሁሉ ተከታትለው ወጉአቸው፤ እግዚአብሔርም በዚያን ቀን እስራኤልን በመታደግ አዳነ። ከጦርነቱ በኋላ የተፈጸሙ ድርጊቶች 24 በዚያን ቀን እስራኤላውያን በራብ ደከሙ፤ ምክንያቱም ሳኦል “ጠላቶቼን እስክበቀል ድረስ ዛሬ እህል ውሃ የሚቀምስ ማናቸውም ሰው የተረገመ ይሁን!” ብሎ ሕዝቡን በማስማል ማንም ሰው እህል ውሃ እንዳይቀምስ ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር። ከዚህም የተነሣ ሁሉም ምንም ነገር ሳይቀምሱ ቀኑን ሙሉ ዋሉ። 25 ጫካ ወደበዛበትም ቦታ በመጡም ጊዜ በየስፍራው ማር. አግኝተው ነበር፤ 26 ዛፉ ሁሉ ማር. የሞላበት ቢሆንም የሳኦልን ርግማን በመፍራት ከማሩ የቀመሰ ማንም አልነበረም፤ 27 ዮናታን ግን አባቱ ሕዝቡን ማስማሉን ስላልሰማ፥ የያዘውን በትር በመዘርጋት ወለላውን እየሳበ ጥቂት ማር. በላ፤ ወዲያውኑ ብርታት አግኝቶ ዐይኑ በራ፤ 28 ነገር ግን ከወታደሮቹ አንዱ “እኛ ሁላችን በራብ ደክመን ዝለናል፤ አባትህ ግን ‘በዛሬው ዕለት ምንም ዐይነት ምግብ የሚመገብ ሰው የተረገመ ይሁን’ ሲል በብርቱ አስጠንቅቆናል” አለው። 29 ዮናታንም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አባቴ በሕዝባችን ላይ የፈጠረው ችግር ምን ያኽል ከባድ ነው! ትንሽ ማር. አግኝቼ በመብላት ብርታት አግኝቼ ዐይኔ እንደ በራ ተመልከት! 30 ታዲያ ዛሬ ሕዝባችን ጠላትን ድል መትቶ ከምርኮ የሚያገኘውን ምግብ ቢመገብ ኖሮ እንዴት በተሻለው ነበር? የሚገድሉአቸው ፍልስጥኤማውያን ቊጥር ምን ያኽል ይበዛ እንደ ነበር እስቲ ገምት።” 31 በዚያን ቀን እስራኤላውያን ከሚክማስ እስከ አያሎን ባለው መንገድ ሁሉ እያሳደዱ በመውጋት ፍልስጥኤማውያንን ድል መቱ፤ በዚህም ጊዜ እስራኤላውያንም በራብ እጅግ ዝለው ነበር። 32 ስለዚህም ከጠላት ባገኙት ምርኮ ላይ እየተረባረቡ በጎችን፥ የቀንድ ከብቶችንና ጥጆችን ባገኙበት ቦታ እያረዱ ሥጋውን ከነደሙ መብላት ጀመሩ፤ 33 ለሳኦልም “ተመልከት ሕዝቡ ደም ያለበትን ሥጋ በመብላታቸው በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአት ሠርተዋል” የሚል ወሬ ደረሰው። ሳኦልም “ይህ የክሕደት ተግባር ነው! አንድ ትልቅ ድንጋይ አንከባላችሁ ወደዚህ አምጡልኝ” ሲል ጮኸባቸው። 34 ከዚህም በኋላ ሌላ ትእዛዝ እንዲህ ሲል አስተላለፈ፤ “ወደ ሕዝቡ ሄዳችሁ ‘የቀንድ ከብቶቻችሁንና በጎቻችሁን ሁሉ አምጡ፤ እነርሱንም ዐርዳችሁ በዚህ ስፍራ መመገብ አለባችሁ፤ ደም ያለበትንም እርጥብ ሥጋ በመብላት በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአት አትሥሩ’ ብላችሁ ንገሩአቸው።” ስለዚህም ሕዝቡ ሁሉ በዚያን ሌሊት የቀንድ ከብቶቻቸውንና በጎቻቸውን ሁሉ አምጥተው በዚያ ዐረዱ፤ 35 ሳኦልም በዚያ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤ ይህም እርሱ የሠራው መሠዊያ የመጀመሪያው ነበር። 36 ሳኦልም ወታደሮቹን “እንግዲህ እንውረድና በፍልስጥኤማውያን ላይ በሌሊት አደጋ እንጣልባቸው፤ እስኪነጋም ድረስ ሀብታቸውን ዘርፈን ሁሉንም እንፍጃቸው” አለ። እነርሱም “መልካም መስሎ የታየህን ሁሉ አድርግ” አሉት። ካህኑ ግን “በመጀመሪያ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንጠይቅ” አለ። 37 ሳኦልም “በፍልስጥኤማውያን ላይ አደጋ እንጣልባቸውን? ድልንስ ለእኛ ትሰጣለህን?” ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በዚያን ቀን ምንም መልስ አልሰጠም። 38 ከዚህ በኋላ ሳኦል ለሕዝቡ መሪዎች እንዲህ አለ፤ “ወደዚህ ቀርባችሁ ዛሬ ምን ዐይነት ኃጢአት እንደ ተሠራ መርምራችሁ ዕወቁ፤ 39 በደል ሠርቶ የተገኘው ሰው ልጄ ዮናታን እንኳ ቢሆን በሞት እንደሚቀጣ ለእስራኤል ድልን በሰጠው በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ።” ነገር ግን አንዳች መልስ የሰጠው ሰው አልተገኘም። 40 ከዚያም በኋላ ሳኦል “እናንተ ሁላችሁም በዚያ በኩል ቁሙ፤ እኔና ልጄ ዮናታን ደግሞ በዚህ በኩል እንቆማለን” አላቸው። እነርሱም “መልካም መስሎ የታየህን አድርግ” አሉት። 41 ሳኦልም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “እግዚአብሔር ሆይ! ዛሬ ስለምን መልስ አልሰጠኸኝም? የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! በእነዚህ በተቀደሱ ድንጋዮች አማካይነት መልስ ስጠኝ፤ ይህን በደል የሠራነው ዮናታን ወይም እኔ ከሆንን በኡሪም አማካይነት፥ ይህን በደል የፈጸሙ ሕዝብህ እስራኤል ከሆኑ በቱሚም አማካይነት መልስ ስጠኝ።” መልሱም ዮናታንንና ሳኦልን ስላመለከተ ሕዝቡ ነጻ ሆኑ፤ 42 ከዚህም በኋላ ሳኦል “በእኔና በልጄ በዮናታን መካከል ዕጣ ጣሉ” አለ፤ ዕጣውም በዮናታን ላይ መጣ፤ 43 ከዚህም በኋላ ሳኦል ዮናታንን “ያደረግኸው ነገር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ። ዮናታንም “በበትሬ ጫፍ አስነክቼ ጥቂት ማር. ቀምሻለሁ እነሆ በዚህ እገኛለሁ፤ ለመሞትም ዝግጁ ነኝ” አለ። 44 ሳኦልም “እግዚአብሔር ይፍረድብኝ፤ አንተ ከሞት ቅጣት አታመልጥም!” አለው። 45 ሕዝቡ ግን ሳኦልን “ይህን ታላቅ ድል ለእስራኤል ያስገኘ ዮናታን ይሞታልን? ከቶ አይደረግም! መሞቱ ይቅርና ከራስ ጠጒሩ አንዲቱ እንደማትወድቅ በሕያው እግዚአብሔር ስም እንምላለን፤ ዛሬ እርሱ ያደረገው ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ረዳትነት የተፈጸመ ነው” አሉ፤ በዚህም ዐይነት ሕዝቡ ዮናታንን ከሞት ቅጣት አዳኑት። 46 ከዚያም በኋላ ሳኦል ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ተገታ፤ እነርሱም ተመልሰው ወደ አገራቸው ሄዱ። የሳኦል ዘመነ መንግሥትና የቤተሰቡ ሁኔታ 47 ሳኦል በእስራኤል ከነገሠ በኋላ፥ በሁሉም ስፍራ የሚገኙ ጠላቶቹን ወጋ፤ እነርሱም የሞአብ፥ የዐሞንና የኤዶም ሕዝቦች፥ የጾባ ነገሥታትና ፍልስጥኤማውያን ናቸው፤ በተዋጋበት ስፍራ ሁሉ ድል አድራጊ ሆነ፤ 48 በጀግንነትም ተዋግቶ የዐማሌቅን ሕዝብ እንኳ ሳይቀር ድል መታ፤ እርሱም እስራኤላውያንን ከጠላቶቻቸው እጅ አዳነ። 49 የሳኦልም ወንዶች ልጆች ዮናታን፥ ይሽዊና ማልኪሹዓ ተብለው ይጠሩ ነበር፤ ታላቋ ሴት ልጁም ሜራብ ስትሆን፥ ታናሽዋ ሜልኮል ትባል ነበር፤ 50 ሚስቱም አሒኖዓም ተብላ የምትጠራ የአሒማዓጽ ልጅ ነበረች፤ የሠራዊቱም አዛዥ አበኔር ተብሎ የሚጠራው የአጐቱ የኔር ልጅ ነበር። 51 ስለዚህም የሳኦል አባት ቂስና የአበኔር አባት ኔር የአቢኤል ልጆች ነበሩ። 52 ሳኦል በነበረበት ዘመን ሁሉ ከፍልስጥኤማውያን ጋር በብርቱ ጠላትነት ሲዋጋ ኖረ፤ ስለዚህም ብርቱ ወይም ጀግና የሆነ ሰው ሲያገኝ እየመለመለ በጦር ሠራዊቱ ውስጥ ያስመዘግበው ነበር። |