Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


1 ነገሥት 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ንጉሥ ዳዊት በሽምግልና ዕድሜው

1 ንጉሥ ዳዊት እጅግ ሸምግሎ ስለ ነበር አገልጋዮቹ የብርድ መከላከያ የሚሆን ልብስ ደራርበው ቢያለብሱትም ሙቀት ሊሰጠው አልቻለም ነበር።

2 ስለዚህ ባለሟሎቹ “ንጉሥ ሆይ! ከአንተ ጋር ሆና የምትንከባከብህ ወጣት ልጃገረድ ፈልገን እናምጣልህ፤ ከአንተ ጋር ዐቅፋህ በመተኛት ታሞቅሃለች” አሉት።

3 አንዲት ቈንጆ ልጃገረድ ለማግኘት በመላው እስራኤል ፍለጋ ተደረገ፤ ሹኔም ተብላ ከምትጠራው ስፍራ አቢሻግ የምትባል አንዲት ልጃገረድ አግኝተው ለንጉሡ አመጡለት፤

4 እርስዋም እጅግ ውብ ነበረች፤ ከንጉሡም ጋር ሆና በማገልገል ትንከባከበው ነበር፤ ይሁን እንጂ እርሱ ከእርስዋ ጋር አልተገናኘም።


አዶንያስ ለመንገሥ የነበረው ፍላጎት

5-6 ከአቤሴሎም በኋላ ከዳዊትና ከሐጊት የተወለደ በሕይወት ያለ ተከታይ ልጅ አዶንያስ ነበር፤ እርሱም እጅግ መልከ ቀና ነበር፤ ዳዊት ስለማናቸውም ነገር ምክርና ተግሣጽ ሰጥቶት አያውቅም ነበር፤ ከዚህም የተነሣ አዶንያስ ለመንገሥ ፈለገ፤ ይህንንም ፍላጎቱን ለማሟላት ሠረገሎችን፥ ፈረሶችንና ኀምሳ ጋሻ ጃግሬዎችን አዘጋጀ።

7 ስለዚህም ጉዳይ ከጸሩያ ልጅ ከኢዮአብና ከካህኑ ከአብያታር ጋር ተመካከረ፤ እነርሱም ዓላማውን ደገፉ፤

8 ነገር ግን ካህኑ ሳዶቅ፥ የዮዳሄ ልጅ በናያ፥ ነቢዩ ናታን፥ ሺምዒ፥ ሬዒና የዳዊት የክብር ዘበኞች አዶንያስን አልደገፉም።

9 አንድ ቀን አዶንያስ “ዔንሮጌል” ተብሎ በሚጠራው የውሃ ምንጭ አጠገብ የዞሔሌት አለት በሚባለው ስፍራ በጎችን፥ በሬዎችንና የሰቡ ወይፈኖችን ዐርዶ መሥዋዕት አቀረበ፤ የንጉሥ ዳዊትን ልጆችና በይሁዳ የሚገኙትን የመንግሥት ባለሥልጣኖች ሁሉ ወደዚህ ወደ መሥዋዕቱ በዓል መጥተው ተካፋዮች እንዲሆኑ ጋበዛቸው፤

10 ነገር ግን ነቢዩን ናታንን፥ በናያን፥ የንጉሡን የክብር ዘበኞችና ወንድሙን ሰሎሞንን አልጠራቸውም።


የሰሎሞን መንገሥ

11 ከዚህ በኋላ ናታን ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ ሄዶ “ጌታችን ዳዊት ሳያውቅ የሐጊት ልጅ አዶንያስ መንገሡን አልሰማሽምን?” አላት።

12 “የራስሽንና የልጅሽን የሰሎሞንን ሕይወት ለማትረፍ እንድትችይ ልምከርሽ።

13 ወደ ንጉሥ ዳዊት ገብተሽ ‘ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ነግሦ በዙፋኔ ይቀመጣል’ ብለህ ለአገልጋይህ በመሐላ ቃል ገብተህልኝ አልነበረምን? ታዲያ፥ አሁን አዶንያስ እንዴት ሊነግሥ ቻለ? ብለሽ ንገሪው”።

14 “ከንጉሥ ዳዊት ጋር በምትነጋገሪበት ጊዜ እኔም ወዲያውኑ ገብቼ አንቺ የተናገርሺው ሁሉ እውነት መሆኑን አረጋግጣለሁ” አላት።

15 ስለዚህ ቤርሳቤህ ንጉሡን ለማነጋገር ወዳለበት እልፍኝ ገባች፤ ንጉሡ እጅግ ስለ ሸመገለ ሹኔማይቱ ልጃገረድ አቢሻግ በጥንቃቄ ትንከባከበው ነበር፤

16 ቤርሳቤህም ወደ መሬት ለጥ ብላ እጅ ነሣች፤ ንጉሡም “ምን ትፈልጊያለሽ?” አላት።

17 ቤርሳቤህም እንዲህ ስትል መለሰች፤ “ጌታዬ ሆይ! ልጄ ሰሎሞን የዙፋንህ ወራሽ ሆኖ እንደሚነግሥና በዙፋንህ እንደሚቀመጥ በአምላክህ በእግዚአብሔር ስም ምለህ ቃል ገብተህልኝ ነበር፤

18 አሁን ግን ጌታዬ ንጉሡ ሳታውቅ አዶንያስ ነግሦአል።

19 ስለዚህ ብዙ ኰርማዎችን፥ የሰቡ ወይፈኖችንና በጎችን መሥዋዕት አቅርቦአል፤ በበዓሉም ላይ እንዲገኙለት የንጉሡን ልጆች ካህኑን አብያታርንና የሠራዊትህን አዛዥ ኢዮአብን ጋብዞአቸዋል፤ አገልጋይህን ሰሎሞንን ግን አልጋበዘውም።

20 ጌታዬ ንጉሥ ሆይ! የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ከአንተ በኋላ የሚነግሠው ማን መሆኑን እንድታስታውቀው በመጠባበቅ ላይ ነው፤

21 ይህን ባታደርግ ግን አንተ ከሞትህ በኋላ ወዲያውኑ ልጄ ሰሎሞንና እኔ እንደ በደለኞች እንቈጠራለን።”

22 ቤርሳቤህ ገና ንግግርዋን ሳትጨርስ ነቢዩ ናታን ደረሰ፤

23 የነቢዩም መምጣት ለንጉሡ ተነገረው፤ ናታንም ወደ ውስጥ በመግባት ለጥ ብሎ እጅ ነሣ፤

24 ናታንም፦ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ! አዶንያስ ከአንተ በኋላ ነግሦ በዙፋንህ እንዲቀመጥ አስታውቀሃልን?” አለው።

25 አዶንያስ በዛሬው ዕለት ብዙ ጥጆችንና የሰቡ ኰርማዎችን፥ በጎችን ዐርዶ መሥዋዕት አቅርቦአል፤ ሌሎቹን የንጉሡን ልጆች የሠራዊትህን አዛዥ ኢዮአብንና ካህኑን አብያታርን ጋብዞአል፤ እነሆ አሁን በዚህ ሰዓት “ረጅም ዕድሜ ለንጉሥ አዶንያስ!” በማለት እየደነፉ ከእርሱ ጋር በመብላትና በመጠጣት ላይ ናቸው።

26 ነገር ግን ይህ ሁሉ ሲሆን እኔን አገልጋይህን፥ ካህኑን ሳዶቅን፥ የዮዳሄን ልጅ በናያንና አገልጋይህን ሰሎሞንን ወደ ግብዣው አልጠራንም፤

27 ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በኋላ በዙፋንህ ላይ የሚቀመጠው ማን እንደሚሆን ለባለሟሎችህ ሳታስታውቅ ይህ የአዶንያስ መንገሥ ጉዳይ አንተ ያደረግኸው ነገር ነውን?

28 ንጉሥ ዳዊትም “ተመልሳ እንድትመጣ ቤርሳቤህን ጥሩ” ብሎ አዘዘ፤ እርስዋም መጥታ በፊቱ ቆመች፤

29 በዚህም ጊዜ እንዲህ አላት፥ “ከደረሰብኝ መከራ ሁሉ በታደገኝ በሕያው እግዚአብሔር ስም ቃል እገባልሻለሁ፤

30 ልጅሽ ሰሎሞን በእኔ እግር ተተክቶ እንደሚነግሥ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም ከዚህ በፊት የገባሁልሽን ቃል በዛሬው ዕለት የምፈጽም መሆኔን አረጋግጥልሻለሁ።”

31 ቤርሳቤህም ወደ መሬት ለጥ ብላ እጅ በመንሣት “ጌታዬ ንጉሥ ዳዊት ለዘለዓለም በሕይወት ይኑር!” አለች።

32 ከዚህ በኋላ ንጉሥ ዳዊት ካህኑን ሳዶቅን፥ ነቢዩን ናታንንና የዮዳሄን ልጅ በናያን አስጠራ፤ እነርሱም ገብተው ወደ እርሱ ቀረቡ።

33 ንጉሡም እንዲህ አላቸው፦ “በቤተ መንግሥቴ ከሚገኙት ባለሟሎቼ ጋር አብራችሁ ሂዱ፤ ልጄን ሰሎሞንንም እኔ በምቀመጥባት በቅሎ አስቀምጡትና አጅባችሁት ወደ ግዮን ምንጭ ውረዱ፤

34 በዚያም ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታን ቀብተው በእስራኤል ላይ ያንግሡት፤ ከዚህ በኋላ እምቢልታ በመንፋት ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ‘ረጅም ዕድሜ ለንጉሥ ሰሎሞን!’ በሉ።

35 በዙፋኔ ላይ ለመቀመጥ ወደዚህ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ አጅባችሁት ኑ፤ የእስራኤልና የይሁዳ ንጉሥ ገዢ እንዲሆን የመረጥኩት ስለ ሆነ እርሱ ከእኔ በኋላ ይነግሣል።”

36 የዮዳሄ ልጅ በናያም “ጌታዬ ንጉሡ እንዳለው ይሁን፤ ይህንንም አምላክህ እግዚአብሔር ይፈጽመው።

37 ንጉሥ ሆይ! እግዚአብሔር ከአንተ ጋር እንደ ሆነ ሁሉ ከሰሎሞንም ጋር ይሁን፤ መንግሥቱንም በዘመንህ ከነበረው የበለጠ ታላቅ ያድርገው!” አለው።

38 ስለዚህ ካህኑ ሳዶቅ፥ ነቢዩ ናታን፥ የዮዳሄ ልጅ በናያና የንጉሡ ክብር ዘበኞች ሰሎሞንን ዳዊት በሚቀመጥባት በቅሎ ላይ በማስቀመጥ ወደ ግዮን ምንጭ ወረዱ፤

39 ካህኑ ሳዶቅም ከተቀደሰው ድንኳን ይዞት የመጣውን የቅባት ዘይት መያዣ ቀንድ ወስዶ ሰሎሞንን ቀባው፤ በዚህን ጊዜ እምቢልታ ነፉ፤ ሕዝቡም ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው “ረጅም ዕድሜ ለንጉሥ ሰሎሞን!” አሉ፤

40 ወደ ቤተ መንግሥትም በሚመለሱበት ጊዜ አጅበው ተከተሉት፤ ከድምፃቸው ከፍተኛነት የተነሣ ምድር እስክትናወጥ ድረስ እምቢልታ በመንፋት እየጮኹ ደስታቸውን ገለጡ።

41 አዶንያስና የጠራቸው ተጋባዦች ሁሉ ግብዣውን በማገባደድ ላይ ሳሉ የሁካታ ድምፅ ሰሙ፤ ኢዮአብም የእምቢልታ ድምፅ በሰማ ጊዜ “ይህ በከተማው ውስጥ የሚሰማው የሁካታ ድምፅ ሁሉ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ፤

42 እርሱ ገና ተናግሮ ሳይጨርስ የካህኑ የአብያታር ልጅ ዮናታን ድንገት ደረሰ፤ አዶንያስም “እስቲ ና ግባ፤ አንተ ጥሩ ሰው ስለ ሆንክ መልካም ዜና ይዘህ ሳትመጣ አትቀርም” አለው።

43 ዮናታንም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ደኅና ወሬስ ይዤ አልመጣሁም፤ ግርማዊው ንጉሥ ዳዊት ሰሎሞንን አንግሦታል፤

44 ንጉሡም እርሱን ያጅቡት ዘንድ ካህኑን ሳዶቅን፥ ነቢዩን ናታንን፥ የዮዳሄን ልጅ በናያንና የቤተ መንግሥቱን ክብር ዘበኞች ልኮአል፤ እነርሱም ንጉሡ በሚቀመጥባት በቅሎ ላይ እንዲቀመጥ አድርገውታል።

45 ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በግዮን ምንጭ አጠገብ ቀብተው አንግሠውታል፤ ከዚህም በኋላ ሕዝቡ ሁሉ በደስታ ተሞልተው በእልልታና በሆታ ድምፃቸው እያስተጋባ ወደ ከተማ ተመልሰዋል፤ አሁን የምትሰሙትም ድምፅ ይኸው ነው፤

46 እነሆ ሰሎሞን ነግሦ በንጉሣዊ ዙፋን ላይ ተቀምጦአል፤

47 ከዚህም በላይ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ባለሟሎች ሁሉ ወደ ንጉሥ ዳዊት ቀርበው ‘አምላክህ እግዚአብሔር ሰሎሞንን ከአንተ ይበልጥ ዝናው የገነነ፥ መንግሥቱንም ይበልጥ ታላቅ ያድርገው!’ ሲሉ አክብሮታቸውን ገልጠዋል፤ ከዚህ በኋላ ንጉሥ ዳዊት በአልጋው ላይ ሳለ ለእግዚአብሔር ሰገደ።

48 ‘ዛሬ ከእኔ ዘሮች መካከል አንዱ በእኔ እግር ተተክቶ እንዲነግሥ ያደረገና ይህን ለማየት ያበቃኝ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን!’ ሲል እግዚአብሔርን አመሰገነ።”

49 አዶንያስ የጠራቸው ተጋባዦች ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ እጅግ ፈሩ፤ ሁሉም ተነሡ፤ እያንዳንዱም በየፊናው ተበተነ፤

50 አዶንያስም ሰሎሞንን ስለ ፈራ ወደ ተቀደሰው ድንኳን ሄዶ የመሠዊያውን ቀንዶች በመያዝ ተማጠነ።

51 ሰዎቹም ሰሎሞንን “አዶንያስ አንተን ከመፍራቱ የተነሣ የመሠዊያውን ቀንዶች ይዞ ‘ከሁሉ በፊት ንጉሥ ሰሎሞን የማይገድለኝ መሆኑን በማረጋገጥ በመሐላ ቃል ይግባልኝ’ በማለት እየተማጠነ ነው” ሲሉ ነገሩት።

52 ንጉሥ ሰሎሞንም “አካሄዱን ካሳመረ ከራስ ጠጒሩ አንዲት እንኳ አትነካበትም፤ ክፉ ሆኖ ከተገኘ ግን ይሞታል” ሲል መለሰ፤

53 ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን አዶንያስን ከመሠዊያው አውርደው ያመጡት ዘንድ መልእክተኞች ላከ፤ አዶንያስም ወደ ንጉሡ ፊት በመቅረብ ወደ መሬት ለጥ ብሎ እጅ ነሣ፤ ንጉሡም “ወደ ቤትህ መሄድ ትችላለህ” አለው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos