ዘካርያስ 7 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ስለ ጾም ጥያቄ 1 በንጉሡም በዳርዮስ በአራተኛው ዓመት፥ ካሴሉ በሚባል በዘጠነኛው ወር በአራተኛው ቀን፥ የጌታ ቃል ወደ ዘካርያስ መጣ። 2 የቤቴልም ሰዎች በጌታ ፊት ልመና እንዲያቀርቡ ሳራሳርንና ሬጌሜሌክን ከሰዎቻቸው ጋር ላኩ፤ 3 ለሠራዊት ጌታ ቤት ካህናት ለነቢያትም፦ “ለብዙ ዓመታት እንዳደረግሁት በአምስተኛው ወር መጾምና ማልቀስ ይገባኛልን?” ብለው እንዲናገሩ ልኳቸው ነበር። 4 የሠራዊትም ጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 5 ለምድሩ ሕዝብና ለካህናት ለሁሉም እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ በዚህ በሰባው ዓመት በአምስተኛውና በሰባተኛው ወር ስትጾሙና ስታለቅሱ፥ በውኑ ለእኔ ነው የጾማችሁልኝ? 6 ስትበሉና ስትጠጡስ፥ የምትበሉትና የምትጠጡት ለራሳችሁ አይደለምን? 7 ኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ ያሉ ከተሞች ገና ሰዎች እየኖሩባቸው፥ በሰላም ተቀምጠው እያሉ፥ ደቡቡና ቈላውም ሰዎች እየኖሩባቸው በነበረ ጊዜ አይደለም እንዴ፥ ይህንን ቃል ጌታ በቀደሙት ነቢያት አማካኝነት የተናገረው? 8 የጌታም ቃል ወደ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 9 የሠራዊት ጌታ እንዲህ ብሎ ተናግሮአል፦ እውነተኛውን ፍርድ ፍረዱ፤ እርስ በርሳችሁ ደግነትና ርኅራኄ ይኑራችሁ፤ 10 መበለቲቱንና ድኻ አደጉን፥ መጻተኛውንና ችግረኛውን አትበድሉ፤ ከእናንተም ማንም በወንድሙ ላይ ክፉ ነገር በልቡ አያስብ። 11 እነርሱ ግን መስማት አልፈለጉም፤ በእልኸኝነት ጀርባቸውን አዞሩ፤ ጆሮአቸውንም ደፈኑ። 12 የሠራዊት ጌታም በቀደሙት ነቢያት እጅ በመንፈሱ የላከውን ሕጉንና ቃሉን እንዳይሰሙ ልባቸውን እንደ አልማዝ አጠነከሩ፤ ስለዚህ ከሠራዊት ጌታ ታላቅ ቁጣ መጣ። 13 እኔ ስጠራቸው እነርሱ አልሰሙኝም፥ እንዲሁ እነርሱ በሚጠሩኝ ጊዜ እኔ አልሰማቸውም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። 14 በማያውቋቸው በባዕዳን አሕዛብ መካከል በዐውሎ ነፋስ በተንኳቸው። ስለዚህ ከእነርሱ በኋላ ምድሪቱ ባድማ ሆናለች፥ የሚዘዋወርባትና የሚመላለስባትም አልነበረም፤ ያማረችውንም ምድር ባድማ አደረጉአት። |