ዘካርያስ 3 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ነቢያዊ ራእይ፦ ሊቀ ካህኑ ኢያሱ 1 ከዚያም እርሱ ታላቁን ካህን ኢያሱን በጌታ መልአክ ፊት ቆሞ አሳየኝ፥ ሰይጣንም እርሱን ለመክሰስ በስተ ቀኙ ቆሞ ነበር። 2 ጌታም ሰይጣንን፦ “ሰይጣን ሆይ፥ ጌታ ይገሥጽህ፤ ኢየሩሳሌምን የመረጠ ጌታ ይገሥጽህ! በውኑ ይህ ከእሳት የተነጠቀ ትንታግ አይደለምን?” አለው። 3 ኢያሱም እድፋም ልብስ ለብሶ በመልአኩ ፊት ቆሞ ነበር። 4 መልአኩም መልሶ በፊቱ የቆሙትን፦ “እድፋሙን ልብስ ከእርሱ ላይ አውልቁ” አላቸው። እርሱንም፦ “እነሆ፥ አበሳህን ከአንተ አርቄአለሁ፥ ጥሩ ልብስም አለብስሃለሁ” አለው። 5 ከዚያም፥ “ንጹሕ የራስ ላይ ጥምጣም ያድርጉለት” አለ። እነርሱም በራሱ ላይ ንጹሕ ጥምጥም አደረጉ፥ ልብስንም አለበሱት፤ የጌታም መልአክ በአጠገቡ ቆሞ ነበር። 6 የጌታም መልአክ በኢያሱ ላይ እንዲህ ሲል ብያኔ ሰጠ፦ 7 “የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ በመንገዴ ብትሄድ ትእዛዜንም ብትጠብቅ፥ በቤቴ ላይ ትፈርዳለህ፥ አደባባዮቼንም ትጠብቃለህ፤ እኔም በዚህ ስፍራ ከቆሙት ጋር ስፍራን እሰጥሃለሁ።” ተጨማሪ ትንቢት 8 ሊቀ ካህን ኢያሱ ሆይ፥ ስማ! በፊትህም የሚቀመጡት ባልንጀሮችህ ለሚመጣው ነገር ምልክት የሚሆኑ ሰዎች ናቸውና ይስሙ! እነሆ፥ እኔ አገልጋዬን ቁጥቋጡን አወጣለሁ። 9 በኢያሱ ፊት ያኖርሁትን ድንጋይ ተመልከት፤ በአንዱ ድንጋይ ላይ ሰባት ዐይኖች አሉ፤ እነሆ፥ ቅርጹን እቀርጻለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፥ የዚያችንም ምድር በደል በአንድ ቀን አስወግዳለሁ። 10 በዚያ ቀን፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፥ እያንዳንዱ በወይኑና በበለሱ ስር ሆኖ ባልንጀራውን ይጠራል። |