Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘካርያስ 11 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የዛፎች፥ የእረኞችና የአንበሶች ለቅሶ

1 ሊባኖስ ሆይ፥ ደጆችህን ክፈት፥ እሳትም ዝግባዎችህን ትብላ!

2 የጥድ ዛፍ ሆይ፥ ዝግባ ወድቆአልና፥ የከበሩትም ዛፎች ጠፍተዋልና አልቅሱ! እናንተም የባሳን ዛፎች ሆይ፥ ጽኑው ጫካ ተቈርጦአልና አልቅሱ!

3 የእረኞች ክብር ተዋርዶአልና የዋይታቸውን ድምፅ ስሙ! የዮርዳኖስ ጥቅጥቅ ደን ወድሟልና የአንበሶች ግሣት ድምፅ ስሙ!


የእረኞች ትረካ

4 አምላኬ ጌታ እንዲህ ብሏል፦ ለእርድ የሚሆኑትን በጎች ጠብቅ።

5 የገዙአቸው ያርዱአቸዋል፥ እንደ በደለኞች አይቆጠሩም፥ የሸጧቸውም፦ “ባለ ጠጋ ሆኛለሁ፤ ጌታ ይመስገን!” ይላሉ። እረኞቻቸው እንኳን አይራሩላቸውም።

6 ከእንግዲህ ወዲህ በምድር ላይ ለሚኖሩ አልራራም፥ ይላል ጌታ፤ እነሆም፥ ሰውን ሁሉ ለባልንጀራውና ለንጉሡ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ ምድሪቱንም ይመታሉ፥ ከእጃቸውም አላስጥላቸውም።

7 እኔም ለእርድ የሚሆኑትን በጎች፥ የመንጋውን ችግረኞች ጠበቅሁ። ሁለት በትሮችንም ወሰድሁ፤ የአንዲቱን ስም “ደስታ” የሁለተኛይቱንም ስም “አንድነት” ብዬ ጠራሁ፤ መንጋውንም አሰማራሁ።

8 በአንድ ወር ጊዜም እኔንም ስለሰለቹኝ፥ እነርሱም ስለጠሉኝ፥ ሦስቱን እረኞች አስወገድኩ።

9 እኔም፦ “እናንተን አልጠብቅም፤ የሚሞተው ይሙት፥ የሚጠፋውም ይጥፋ፤ የቀሩትም እርስ በእርሳቸው ተበላልተው ይጨራረሱ።” አልሁ።

10 እኔም ከሕዝቦች ሁሉ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን ለማፍረስ “ደስታ” የተባለችውን በትሬን ወስጄ ሰበርኳት።

11 በዚያም ቀን ኪዳኑ ፈረሰ፤ እንዲሁም እኔን ሲመለከቱ የነበሩ የተጨነቁ መንጋዎች የጌታ ቃል እንደ ነበረ አወቁ።

12 እኔም፦ “ደስ ብሎአችሁ እንደሆነ ዋጋዬን ስጡኝ፥ ያለዚያ ግን ተውት” አልኩት። እነርሱም ለዋጋዬ ሠላሳ ብር መዘኑ።

13 ጌታም፦ ሊከፍሉኝ የተስማሙበት ጥሩ ዋጋ በግምጃ ቤቱ ውስጥ አኑረው አለኝ። እኔም ሠላሳውን ብር ወስጄ በጌታ ቤት ባለው ግምጃ ክፍል ውስጥ አኖርኩት።

14 ከዚያም በይሁዳና በእስራኤል መካከል ያለውንም ወንድማማችነት ለመለያየት “አንድነት” የተባለቸውን ሁለተኛይቱን በትሬን ሰበርኳት።

15 ጌታም እንዲህ አለኝ፦ አሁን እንደገና የሰነፍን እረኛ ዕቃ ውሰድ።

16 እነሆ፥ በአገር ውስጥ እረኛ አስነሣለሁ፤ እርሱም የጠፋውን አያስተውልም፥ የባዘነውን አይፈልግም፥ የተሰበረውን አይጠግንም፥ የዳነውንም አይቀልብም፤ ነገር ግን የሰባውን ሥጋ ይበላል፥ ሰኰናውንም ይቀለጣጥማል።


ለማይረቡ እረኞች ትንቢት

17 መንጋውን ለሚተው ለማይረባ እረኛ ወዮለት! ሰይፍ ክንዱንና ቀኝ ዓይኑን ይውጋው፤ ክንዱም ፈጽማ ትሰልስል፤ ቀኝ ዓይኑም ፈጽማ ትታወር።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos