Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa

መጽሐፈ ጥበብ 19 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ሰባተኛው ተቃርኖ፦ ቀይ ባሕር

1 በክፉዎች ላይ ግን እስክ መጨረሻው ምሕረት የለሹ ቁጣ ሠርቶባቸዋል፤ ቀድሞውኑም ምን እንደሚሠሩ እራሱ ያውቅ ነበር፤

2 ሕዝቡን ካሰናበቱና በፍጥነትም እንዲወጡ ካደረጉ በኋላ እንደምን ሐሳባቸውን ቀይረው እንደሚያሳድዳቸውም እራሱ ያውቅ ነበርና።

3 በኀዘን ላይ ሳሉ፥ በሞቱባቸው ዘመዶቻቸው መቃብር ላይ በመሪር ኀዘን ያለቅሱ በነበሩበት ጊዜ፥ ሌላ የእብደት ሐሳብ ብልጭ አለባቸው፤ ያባረሯቸውንና እንዲወጡ የለመኗቸውን ሰዎችም እንደ ኮብላዮች ያሳድዷቸው ጀመር።

4 ዋጋቸው የሆነው ዕጣቸውም እንዲህማወደ ከፋው ድርጊት ገፋፋቸው፤ ከዚህ ቀደም የሆነውንም ሁሉ ረሱ። በመከራ ላይ መከራን ይጨምሩ ዘንድ፥ ቀሪውን ከፍተኛም ቅጣት ይቀበሉ ዘንድ ይህን ፈጸሙ።

5 ሕዝቦችህ ግን ፈጽሞ ያልታሰበ ጉዞ አደረጉ፤ በዚያም እጅግ ያልተጠበቀ ሞትም አጋጠማቸው።

6 ልጆችህ ከመጐዳት ይድኑ ዘንድ፥ ፍጥረታታ በሙሉ ትእዛዞችህን በማክበር ሁለመናቸውን ለወጡ።

7 ደመና በሠፈራቸው ላይ አጠላ፤ ውሃ በነበረበት ደረቅ መሬት ብቅ አለ፤ ቀይ ባሕር መሰናክል የሌለበት መንገድ፥ ሞገደኛውም ማዕበል የለመለመ መስክ ሆነ።

8 ሕዝቡ በእጅህ ከለላ ስር ሆኖ፥ በድንቅ ሥራዎችህ እየተደመመ ባሕሩን አቋረጠ።

9 እነርሱ ለግጦሽ በመስክ እንደተሰማሩ ፈረሶች ሆኑ፤ እንደ በግ ግልገሎቾ ዘለሉ፤ ጌታ ሆይ አንተን አዳኛቸውንም እየዘመሩ ያመሰግኑህ ነበር።

10 በዚያን ጊዜ፥ የስደት ጉዟቸውን አስታውሱ፤ መሬት በእንስሳት ፈንታ ትንኞችን አፈራች፤ ወንዙም በአሳዎች ምትክ እልፍ አዕላፍ ዕንቁራሪቶችን ተፋ።

11 ቆየት ብለውም፥ ወፎች ህልውናቸውን በአዲስ መንገድ ሲያገኙ ተመለከቱ፤ የምግብ አምሮታቸው በተቀሰቀሰ ጊዜም ጣፋጭ ምግብን ለመኑ፤

12 እነርሱንም ለማጥገብ፥ ድርጭቶች ከባሕር ውስጥ ወጡ።


ግብጽ ከሶዶም የበለጠ ወንጀለኛ ነች

13 ከአሸባሪው ነጐድጓዳዊ ማስጠንቀቂያ በኋላ፥ ቅጣቱ በኃጢአተኞቹ ላይ ዘነበ። በመጻተኞች ላይ ላሳዩትም ጥላቻ የወንጀሎቻቸውን ዋጋ አገኙ።

14 ሌሎቹም ቢሆኑ ባዕዳኑን በጥሩ ሁኔታ አላስተናገዱም፤ ግብጻውያኑ ግን እንግዳዎቻቸውንና ባለውለታዎቻቸውን ባሮች አደረጉ።

15 በበለጠ ደግሞ ኃጢአተኞቺ ይቀጡበታል፤ ባዕዳኑን ከጥላቻ የተነሣ በሚገባ አላስተናገዷቸውም።

16 የኋላኞቹ ግን እንደ እነርሱ መብት ያላቸውን ሰዎች በደመቀ ሥነ ሥርዓት ከተቀበሏቸው በኋላ፥ እጅግ አድካሚ ሥራዎችን ሰጧቸው።

17 በጻድቁ በር ላይ እንደነበሩት ኃጢአተኞች፥ እነርሱም ታወሩ፤ ጨለማ ሊውጣቸው በዙሪያቸው ባሰፈሰፈ ጊዜም፥ በበሩ ለመውጣት እያንዳንዱ መንገድን በዳሰሳ ማግኘት ነበረበት።


አዲስ ስምምነት በተፈጥሮ ውስጥ

18 የበገና ዜማ ቃናው ሳይለወጥ የድምፁ አወራረድ ሊለዋወጥ እንደሚችል፥ የተፈጥሮም አካላት እንዲሁ በአዲስ ተቀናጁ፤ የሆነውም ሁሉ እንዲህ ነበር፥

19 በመሬት የሚኖሩት እንስሳት፥ በውሃ ውስጥ እየዋኙ ይኖሩ የነበሩ ደግሞ፥ በመሬት ላይ ይኖሩ ጀመር፤

20 እሳት በውሃ ውስጥ ኃይሉን ጨመረ፤ ውሃም እርሱን የማጥፋት ኃይሉን ዘነጋ፤

21 የእሳት ነበልባሎች ደግሞ፥ በውስጣቸው ዘለው የሚገቡትን ትናንሽ እንስሳት ሥጋ መለብለብ አቃታቸው፤ በረዶ የሚመስለውንና በቀላሉ የሚቀልጠውንም ሰማያዊ ምግብ ሊያሟሙት አልቻሉም።


መደምደሚያ

22 ጌታዬ ሆይ በእርግጥም ሕዝብህን በሁሉም ነገር ከፍ አድርገሃል፤ አክብረሃልም፤ በየትኛውም ጊዜና ሥፍራ እርዳታህን አልነፈግኻቸውም።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos