Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ጥበብ 17 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)አምስተኛው ተቃርኖ፦ ጨለማና የእሳት ዓምድ 1 ፍርዶችህ ታላላቅና ድብቅ ናቸው፤ ያልተማሩ ነፍሶች ከመንገድ የወጡትም ለዚህ ነው። 2 ክፉዎች ቅዱሱን ሕዝብ በኃይል ያንበረከኩ ቢመስላቸውም፥ በረጅሙ ሌሊት ከጣራቸው ስር ተተብትበው፥ ከዘላለማዊው ጥበቃ ተባረሩ። 3 ከሠሯቸው ሥውር በደሎች ጋር ሳይታዩ ለማምለጥ ቢያስቡም፤ ጥቁሩ ዝንጉነት ጋርዷቸው፥ በጣረ ሞት ተሳቅቀው፥ በአስፈሪ ተስፋ መቁረጥ ተበታተኑ። 4 መደበቂያ ብለው የያዙት ከለላቸው ፍርሃትን ሊያባርርለቸው አልቻለም፤ አስደንጋጭ ድምጾች በዙሪያቸው ያስተጋባሉ፤ ፊታቸው የጠቆረ ጐስቋላ መናፍስት ያስፈራሯቸዋል። 5 የቱንም ያህል የሚነድ እሳት፥ በድምቀት የሚያበሩትም ከዋክብት ቢሆኑ ብርሃን ሊሰጧቸው አልቻሉም። 6 ብቸኛው ብርሃናቸው፥ ድንገተኛው፥ አስፈሪውና ታላቁ ያ ትርዒት በጠፋ ጊዜም ከፍርሃታቸው የነሣ ምንም ጊዜ ካዩት ሁሉ እጅጉን አስደንጋጭ ሆነባቸው። 7 በዚህ ጊዜ አስማታዊ ምትሃታቸው ኃይሉ ሁሉ ከዳው፤ አውቃለሁ ባይነታቸውም የማይጨበጥ ሆነ። 8 ከታመሙ ነፍሶች ድንጋጤንና ፍርሃትን እናባርራለን ይሉ የነበሩ ሁሉ፥ በሚያስገርም ፍርሃት ተያዙ። 9 የሚያስፈራ ነገር ባጠገባቸው ባይኖርም፥ የትናንሽ እንስሳት ሩጫና የአበቦች ፉጨት ያሸብራቸው ጀመር። 10 ሊያመልጡት የማይችሉትን ነጻውን አየር እንኳን ለማየት አሻፈረን ብለው፥ በፍርናት ተቆራምደው ሞቱ። 11 ክፋት በጣም ፈሪ ነው፤ ለዚህም ራሱን ያወግዛል፤ የኀሊና ተጽዕኖ ሲበዛበት ደገሞ ይብስበታል። 12 ፍርሃት የአእምሮ እርዳታ መቋረጥ ከመሆን ውጭ ሌላ ሊሆን አይችልም፤ 13 በአእምሮህ ላይ ያለህ መተማመን ከቀነሰ፥ የጭንቀትህን ምክንያት አለማወቅህ የበለጠ አሳሳቢ ነው። 14 እጅግ ደካማ የሆነውና እርሱኑ ከመሰለው የሲኦል ጉድጓድ የመነጨው ጨለማ ሳይገፍ በአንድ ዓይነት እንቅልፍ ተሸንፈው ነበር። 15 አሁን ደግሞ ግዙፍ መናፍስት ያባርሯቸዋል፥ ነፍሶቻቸውም በመደንገጣቸው ሽባ ሆነዋል፤ ድንገተኛና ያልተጠበቀ ሽብር አጥቅቷቸዋል። 16 በዚያ የወደቀ ማንም ሰው ቢሆን፥ ካረፈበት ቦታ ተጣብቆ መዝጊያ በሌለው በዚህ እስር ቤት ይማቅቃል። 17 ገበሬም ይሁን እረኛ፥ በበረሃም የሚሠራ ቢሆን፥ በድንገት እየተያዘ የወደቀበትን የማይታለፍ ዕጣ በግደ ይቀበላል፤ ሁሉም ባንድ የጨለማ ሠንሠለት ታሥረው ነበርና። 18 የነፍሱ ፉጨት፥ እንደ ልብ በተዘረጉት ቅርንጨፎች ላይ ሆነው ወፎች የሚያሰሙት ጣዕም ያለው ዜማ፥ የሚንፍዋፍዋው የወራጅ ውሃ ድምፅ፥ እየተምዘገዘጉ የሚወርዱ ዐለቶች ኳኳታ፥ 19 የማይታየው የሚቦርቁ እንስሳት መንገድ፥ ከዱር አራዊት የአስፈሪዎቹ ግሳት፥ ከተራሮች ላይ ካሉ ጉድባዎች የሚስተጋባው የገደል ማሚቶ፥ ሁሉም በፍርሃት ያሸማቅቃቸዋል። 20 መላው ዓለም በቀን ብርሃን ደምቆ፥ ያለ ምንም ችግር ሥራውን ይሠራ ነበር። 21 እነርሱ ላይ ብቻ ድቅድቅ ጨለማ ተንሠራፋ፤ የሚቀበላቸው ጽልመት ምስል ነው፤ እነርሱ ለራሳቸው ሸክም የሆኑትን ያህል፥ ጨለማው አልከበዳቸውም። |