Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ጥበብ 16 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ሁለተኛው ተቃርኖ፥ ዕንቁራሪቶችና ድርጭቶች 1 በዚህም የተነሣ በተመሳሳይ ፍጥነቶች መቀጣታቸው፥ በተባይም መንጋ መሠቃየታቸው ተገቢ ነው። 2 ከዚህ ቅጣት በተቃራኒ ለሕዝቦችህ ደግነትን አደረግህ፤ ልባቸውን አስታገስህ፤ ጣፋጭ የሆኑት ድርጭቶችም በምግብነት ሰጠሃቸው። 3 ግብጻውያኑ ግን በእነርሱ ላይ የተላኩት ፍጥረታት ስለ አስጠሉዋቸው፥ እጅግ ቢራቡም የምግብ ፍላጐታቸውን ጨርሰው አጡ፤ ያንተ ሕዝቦች ግን ጥቂት ከተቸገሩ በኋላ ለየት ያለ ጣፋጭ ምግብ አገኙ። 4 የቀድሞ ጨቋኞች የማያባራ ችግር ይወድቅባቸው ዘንድ አይቀርም፤ ጠላቶቻቸው ምን ያህል እንደተሠቃዩ ማየት ላንተ ሕዝቦች በቂያቸው ነው። ሶስተኛው ተቃርኖ፥ አንበጦችና የነሐስ እባባ 5 አራዊቱ ሕዝብህን በአስፈሪ ቁጣ በወረሯቸው ጊዜ፥ በሚጥመለመሉ እባቦች እየተነደፉ በሚያልቁበት ወቅት፥ ቅጣትህ እስከ መጨረሻው አልዘለቀም። 6 ማስጠንቀቂያ ይሆናቸው ዘንድ፥ ለአጭር ጊዜ ተሠቃዩ፥ የሕግህን ትእዛዝ የሚያስታውስ የድኀንነት ምልክት ሆናቸው፤ 7 ወደ ነሐሱ እባብ የሚያይ ሁሉ ይድናል፤ መዳንን የሚያገኘው ግን ባየው ነገር ሳይሆን የሁሉም አዳኝ በሆንከው ባንተ ነው። 8 ይህን በማድረግህም ከክፉ ነገር ሁሉ የምታድን አንተ መሆንህን ጠላቶቻችን እንዲገነዘቡ አደረገህ። 9 ለእነርሱ የአምበጦችና የዝንቦች ንክሻ የሚገድል ነበር፤ ሕይወታቸውንም ለማዳን ፈውስ አልተገኘም፤ በእነኚህ ፍጥረታት ሊቀጡ ይገባቸዋልና። 10 ያንተ ልጆች ግን የመርዘኞች አበቦች ጥርሶች እንኳ ሊጥሏቸው አልቻሉም፤ ይህም የሆነው በምሕረትህ ረዳትነት በመዳናቸው ነው። 11 አንድ ንድፊያ፥ ፈጥኖ ይድናል፤ ቃልህን ግን እንዳይዘነጉ ያደርጋቸዋል፤ በመርሳት ባሕር ሰጥመው ደግነትህ እንዳይጓደልባቸው ያነቃቃቸዋል። 12 ጌታ ሆይ ሥርም ሆነ መጠቅለያ አላዳናቸውም፥ ሁሉን የሚያድነው ቃልህ እንጂ። 13 በሕይወትና በሞት ላይ ሥልጣን ያለህ አንተ ነህ፤ ወደ ሲኦል ታወርዳለህ፤ ከሲኦልም ታወጣለህ። 14 ከጥላቻ የተነሣ ሰው ሊገድል ይችላል፤ የሄደውን መንፈስ ወይም ሲኦል የተረከበቻትን ነፍስ ግን ፈጽሞ ሊመልስ አይችልም። አራተኛው ተቃርኖ፥ በረዶና መና 15 ከእጅህ ማምለጥ ከቶ አይቻልም፤ 16 አንተን አናውቅም ያሉ ከሐዲዎች፥ በጠንካራው ክንድህ ተመቱ፤ ያልተለመደ ዝናብና በረዶ ወረደባቸው፤ የማያባራ ዶፍ አጥለቀለቃቸው፤ እሳትም በላቸው። 17 ከሁሉም የሚያስደንቀው ደግሞ ሁሉን በሚያጠፋው ውሃ ውስጥ እሳቱ እጅጉን አስፈሪ ሆነ፤ ሁሉም ለጻድቃን ይዋጋልና። 18 ከሐዲዎቹን ለማጥፋት የተላኩትን እንስሶች አብሮ እንዳይደመስስ ባንድ ወቅት እሳቱ በረድ ይላል፤ እነርሱም ይህን ባዩ ጊዜ የእግዚአብሔር ፍርድ እንዳልተዋቸው ይረዳሉ፤ 19 በሌላ ጊዜ ደግሞ፥ ከተረገመችው ምድር የተገኘውን ፍሬ ለማጥፋት፥ በውሃው መሐከል ከእሳት የበለጠ ይንበለበላል። 20 ለሕዝብህ ያደረግኸው ግን እንደምን የተለየ ነው የመላእክትን ምግብ ሰጠኻቸው፤ ሁሉንም የሚያስደስት፥ ጣዕሙም ለሁሉም የሚስማማውን የሰማይ መና ያለመሰልቸት አቀረብክላቸው። 21 ለልጆችህ ያቀረብኸላቸው ልዩ ምግብ፥ ለእነርሱ ያለህን ፍቅር ያሳያል፤ የያንዳንዱን ሰው ፍላጐት ለማርካት የምግቡ ጣዕምም እንደ በላተኛው ይቀያየር ነበር። 22 ውርጭና ብርድ እሳቱን ተቋቁመው፥ ሳይሟሙ ቀሩ፤ ይህ የሆነው የጠላቶቻቸውን መክር ለማጥፋት፥ እሳት በበረዶ ውስጥ እንደሚነድ፥ በዝናብም ውስጥ ቦግ ብሎ እንደሚቀጣጠል ለእነርሱ ለማሳየት ነው፤ 23 በሌላ በኩል ደግሞ ጻድቃኑን ለመመገብ ሲል፥ እሳት ብርታቱን እንኳን ይዘነጋል። 24 ፍጡርህ ያንተ የፈጣሪው አገልጋይ ነውና፥ ኃጥአተኛውን ለመቅጣት ይወጠራል፤ አንተን ለሚያምኑት ሲል ደግሞ ይላላል። 25 ሁሉንም ለመሆን በመለዋወጥ፥ የተቸገሩት ሰዎች በሚስማማቸው መልክ በመቅረብ፥ እነርሱን ለመመገብ ያሳየኸውን ችሮታ ተቀብለው የታዘዙልህ ለዚህ ነው። 26 ጌታ ሆይ ይህን የተመለከቱ የተወደዱ ልጆችህም ለሰው ምግብ የሚሆነው እህል ሳይሆን ባንተ የሚያምኑትን ሁሉ የሚጠብቀው ቃልህ እንደሆነ ያውቁ ዘንድ አደረግህ። 27 እሳት ያላጠፋው፥ ባንዲት የፀሐይ ጨረር የቀለጠውም፥ 28 አንተን ለማመስገን ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት መነሣትና ጎኅም ሳይቀድ አንተን ማግኘት እንዳለብን ለማሳየት ነው። 29 የምስጋና ቢሱ ተስፋ ግን እንደ ክረምት ውርጭ ይሟሟል፤ እንደማይጠቅም ውሃም ይፈሳል። |