ራእይ 17 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ታላቂቱ አመንዝራ ሴትና አውሬው 1 ሰባቱንም ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ “ና፤ በብዙም ውሃዎች ላይ የተቀመጠችውን የታላቂቱን አመንዝራ ሴት ፍርድ አሳይሃለሁ፤ 2 የምድርም ነገሥታት ከእርሷ ጋር ሴሰኑ፤ በምድርም የሚኖሩ በዝሙትዋ ወይን ጠጅ ሰከሩ፤” ብሎ ተናገረኝ። 3 በመንፈስም ወደ በረሓ ወሰደኝ፤ የስድብም ስሞች በሞሉበት፥ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶችም ባሉት በቀይ አውሬ ላይ አንዲት ሴት ተቀምጣ አየሁ። 4 ሴቲቱም ሐምራዊና ቀይ ልብስ ለብሳ በወርቅና በከበሩ ድንጋዮች በዕንቈችም ተሸልማ ነበር፤ በእጅዋም የሚያስጸይፍ ነገርና የዝሙትዋ ርኩሰት የሞላባትን የወርቅ ጽዋ ይዛ ነበር 5 በግምባርዋም “ታላቂቱ ባቢሎን፥ የአመንዝሮችና የምድር ርኩሰት እናት” የሚል ምስጢራዊ የሆነ ስም ተጻፈ። 6 ሴቲቱም በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ አየኋት። ባየኋትም ጊዜ በእጅጉ ተደነቅሁ። 7 መልአኩም እንዲህ አለኝ፦ “ለምንድን ነው የምትደነቀው? የሴቲቱን ምስጢርና የሚሸከማትን፥ ሰባት ራሶችና ዐስር ቀንዶች ያሉትን የአውሬውን ምስጢር እኔ እነግርሃለሁ። 8 ያየኸው አውሬ አስቀድሞ ነበረ፤ አሁን ግን የለም፤ ከጥልቁም ሊወጣ ነው፤ ወደ ጥፋትም ይሄዳል፤ ስሞቻቸውም ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ በሕይወት መጽሐፍ ያልተጻፉ የምድር ኗሪዎች አውሬው አስቀድሞ እንደ ነበረ አሁን ደግሞ እንደሌለ፥ ነገር ግን ተመልሶ እንደሚመጣ ሲያዩ ይደነቃሉ። 9 ጥበብ ያለው አእምሮ የሚያስፈልገው እዚህ ላይ ነው። ሰባቱ ራሶች ሴቲቱ የተቀመጠችባቸው ሰባት ተራራዎች ናቸው፤ ሰባትም ነገሥታት ናቸው፤ 10 አምስቱ ወድቀዋል፤ አንዱም አለ፤ የቀረውም ገና አልመጣም፤ ሲመጣም፥ ጥቂት ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል። 11 የነበረውና የሌለውም አውሬ ራሱ ደግሞ ስምንተኛው ነው፤ ከሰባቱም አንዱ ነው፤ ወደ ጥፋትም ይሄዳል። 12 ያየሃቸውም ዐሥሩ ቀንዶች ገና ያልነገሡ ዐሥር ነገሥታት ናቸው፤ ዳሩ ግን ከአውሬው ጋር ለአንድ ሰዓት ያህል እንደ ነገሥታት ሥልጣንን ይቀበላሉ። 13 እነዚህ አንድ እቅድ አላቸው፤ ኀይላቸውንና ሥልጣናቸውንም ለአውሬው ይሰጣሉ። 14 እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፤ ከእርሱም ጋር ያሉት የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ናቸው።” 15 እንዲህም አለኝ “አመንዝራይቱ የተቀመጠችባቸው ያየሃቸው ውሃዎች፥ ወገኖችና ብዙ ሰዎች፥ አሕዛብም፥ ቋንቋዎችም ናቸው። 16 ያየሃቸውም ዐሥር ቀንዶችና አውሬው አመንዝራይቱን ይጠላሉ፤ ይበዘብዟታል፥ ራቁትዋንም ያደርጓታል፤ ሥጋዋንም ይበላሉ፤ በእሳትም ያቃጥሉአታል። 17 የእግዚአብሔርም ቃል እስኪፈጸም ድረስ ዕቅዱን በአንድ ልብ እንዲያደርጉና መንግሥታቸውንም ለአውሬው እንዲሰጡ እግዚአብሔር በልባቸው አሳድሮአልና። 18 ያየሃትም ሴት በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ ታላቂቱ ከተማ ናት።” |