Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ራእይ 10 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ትንሽቱን መጽሐፍ የያዘ መልአክ

1 ሌላም ብርቱ መልአክ ደመና ተጐናጽፎ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ በራሱም ላይ ቀስተ ደመና ነበረ፤ ፊቱም እንደ ፀሐይ እግሮቹም እንደ እሳት ዓምዶች ነበሩ፤

2 የተከፈተችንም ትንሽ መጽሐፍ በእጁ ይዞ ነበር። ቀኝ እግሩንም በባሕር ላይ ግራውንም በምድር ላይ አኖረ፤

3 እንደሚያገሣም አንበሳ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ በጮኸም ጊዜ ሰባቱ ነጐድጓዶች በየድምፃቸው ተናገሩ።

4 ሰባቱ ነጐድጓድ በተናገሩ ጊዜ ልጽፍ አሰብሁ፤ ከሰማይም “ሰባቱ ነጐድጓዶች የተናገሩትን ነገር በማኅተም ዝጋው፤ አትጻፈውም፤” የሚል ድምፅ ሰማሁ።

5 በባሕርና በምድርም ላይ ሲቆም ያየሁት መልአክ ቀኝ እጁን ወደ ሰማይ አነሣ፤

6 ሰማይንና በእርሱም ያሉትን፥ ምድርንና በእርሷም ያሉትን፥ ባሕርንና በእርሱም ያሉትን በፈጠረው፥ ከዘለዓለምም እስከ ዘለዓለም ድረስ ሕያው ሆኖ በሚኖረው ምሎ “ወደ ፊት አይዘገይም

7 ዳሩ ግን ሰባተኛው መልአክ ለመንፋት የተዘጋጀው መልአክ የመለከቱን ድምፁም በሚያሰማባቸው ቀኖች፥ የእግዚአብሔር ምሥጢር ለባርያዎቹ ለነቢያት የምሥራች በሰበከላቸው መሠረት ይፈጸማል፤” አለ።

8 ከሰማይም የሰማሁት ድምፅ እንደገና ሲናገረኝና “ሂድና በባሕርና በምድር ላይ በቆመው መልአክ በእጅ ያለችውን የተከፈተችውን መጽሐፍ ውሰድ፤” ሲል ሰማሁ።

9 ወደ መልአኩም ሄጄ “ታናሺቱን መጽሐፍ ስጠኝ፤” አልሁት። እርሱም “ውሰድና ብላት፤ ሆድህንም መራራ ታደርገዋለች፤ በአፍህ ግን እንደ ማር ትጣፍጣለች፤” አለኝ።

10 ከመልአኩም እጅ ታናሺቱን መጽሐፍ ወስጄ በላኋት፤ በአፌም እንደ ማር ጣፋጭ ሆነች፤ ከበላኋት በኋላም ሆዴ መራራ ሆነ።

11 “በብዙ ወገኖችና በአሕዛብም በቋንቋዎችም በነገሥታትም ላይ እንደገና ትንቢት ትናገር ዘንድ ይገባሃል፤” ተባልሁ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos