መዝሙር 8 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ለመዘምራን አለቃ በዋሽንት፥ የዳዊት መዝሙር። 2 አቤቱ ጌታችን፥ ስምህ በምድር ሁሉ ምን ያህል ገናና ነው፥ ክብርህን በሰማዮች ላይ የምታኖር። 3 በጠላቶችህ ምክንያት ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ፥ ጠላትንና ቂመኛን ለማጥፋት። 4 የጣቶችህን ሥራ ሰማዮችህን ባየሁ ጊዜ፥ ጨረቃንና ከዋክብትን አንተ የሠራሃቸውን፥ 5 ታስበው ዘንድ ሰው ምንድነው? ትጐበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድነው? 6 ከመላእክት እጅግ ጥቂት አሳነስኸው፥ በክብርና በምስጋና ዘውድ ከለልኸው። 7 በእጆችህም ሥራ ሁሉ ላይ ሾምኸው፥ ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት፥ 8 በጎችንም ላሞችንም ሁሉ ደግሞም የምድረ በዳውን እንስሶች፥ 9 የሰማይንም ወፎች የባሕርንም ዓሦች፥ በባሕር መንገድ የሚሄደውንም ሁሉ። 10 አቤቱ ጌታችን፥ ስምህ በምድር ሁሉ እጅግ ተመሰገነ። |