መዝሙር 74 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 የአሳፍ ትምህርት። 1 የአሳፍ ትምህርት። አቤቱ፥ ስለምን ለሁልጊዜ ጣልኸኝ? በማሰማርያህ በጎች ላይስ ቁጣህ ስለምን ጨሰ? 2 አስቀድመህ የፈጠርሃትን ማኅበርህን፥ የተቤዠሃትንም የርስትህን በትር፥ በእርሷ ያደርህባትን የጽዮንን ተራራ አስብ። 3 መጠን ወደሌላቸው ፍርስራሶች እርምጃህን አቅና፥ ጠላት በመቅደስ ያለውን ሁሉ አጥፍቶአል። 4 ጠላቶችህ በአደባባይህ ላይ አገሡ፥ ለድል ምልክት ዐላማቸውን አኖሩ። 5 በላይኛው መግቢያ ውስጥ፥ በዱር፥ በመጥረቢያ እንጨቶችን የሚቆርጡ ሰዎችን ይመስላሉ። 6 እንዲሁ በመጥረቢያና በመዶሻ ሰበሩአት። 7 መቅደስህን በእሳት አቃጠሉ፥ የስምህንም ማደሪያ በምድር ውስጥ አረከሱ። 8 አንድ ሆነው በልባቸው በየሕዝባቸው፦ ኑ፥ የእግዚአብሔርን የተቀድሱ ቦታዎችን አቃጠሉ። 9 ምልክታችንን አናይም ከእንግዲህ ወዲህም ነቢይ አይኖርም፥ ይህም እስከ መቼ እንደሚቆይ የሚያውቅ በኛ ዘንድ የለም። 10 አቤቱ፥ ጠላት እስከ መቼ ይሳደባል? ስምህን ጠላት ለሁልጊዜ ያቃልላልን? 11 እጅህንም ለምን ትመልሳለህ? ቀኝ እጅህንም ለምን በብብትህ መካከል ታቆያለህ? 12 እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፥ በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ። 13 አንተ ባሕርን በኃይልህ ከፈልካት፥ የአውሬዎችን ራስ በውኃ ውስጥ ሰበርህ። 14 አንተ የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ፥ ለኢትዮጵያ ሰዎችም እንደ ምግብ ሰጠሃቸው። 15 አንተ ምንጮቹንና ፈሳሾቹን ሰነጠቅህ፥ አንተ ሁልጊዜ የሚፈስሱትን ወንዞች አደረቅህ። 16 ቀኑ የአንተ ነው ሌሊቱም የአንተ ነው፥ አንተ ፀሓዩንና ጨረቃውን አዘጋጀህ። 17 አንተ የምድርን ዳርቻ ሁሉ አረጋገጥህ፥ በጋንም ክረምትንም አንተ ሠራህ። 18 ይህንንም አስታውስ፥ ጠላት በጌታ ተሳለቀ፥ አላዋቂ ሕዝብም በስምህ ቀለደ። 19 የምትገዛልህን እርግብ ለአራዊት አትስጣት፥ የችግረኞችህን ነፍስ መቼውንም አትርሳ። 20 ወደ ኪዳንህ ተመልከት፥ የምድር የጨለማ ስፍራዎች በዓመፅ ቤቶች ተሞልተዋልና። 21 ችግረኛ አፍሮ አይመለስ፥ ችግረኛና ምስኪን ስምህን ያመሰግናሉ። 22 አቤቱ፥ ተነሥ በቀልህንም ተበቀል፥ አላዋቂዎች ዘወትር የተሳለቁብህን አስብ። 23 የጠላቶችህን ቃል አትርሳ፥ የተቃዋሚዎችህ ድንፋታ ሳያቋርጥ ወደ አንተ ይወጣል። |