Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


መዝሙር 7 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 ስለ ብንያማዊ ሰው ስለ ኩዝ ቃል ለጌታ የዘመረው የዳዊት መዝሙር።

2 አቤቱ አምላኬ፥ በአንተ ታመንሁ፥ ከሚያሳድዱኝ ሁሉ አድነኝና አውጣኝ፥

3 ነፍሴን እንደ አንበሳ ነጥቀው እንዳይሰብሩዋት፥ የሚያድንና የሚታደግ ሳይኖር።

4 አቤቱ አምላኬ፥ እንዲህ አድርጌ ከሆነ፥ ዓመፃም በእጄ ቢኖር፥

5 መልካም ላደረጉልኝም ክፉን መልሼላቸው ከሆነ፥ ጠላቴንም በከንቱ ገፍቼው ከሆነ፥

6 ጠላት ነፍሴን ያሳድዳት ያግኛትም፥ ሕይወቴንም በምድር ላይ ይርገጣት፥ ክብሬንም በትቢያ ላይ ያዋርዳት።

7 አቤቱ፥ በመዓትህ ተነሥ፥ በጠላቶቼ ላይ በቁጣ ተነሣባቸው፥ አቤቱ አምላኬ፥ ባዘዝኸው ትእዛዝ ንቃ።

8 የአሕዛብም ጉባኤ ይከብብሃል፥ በእነርሱም ላይ ወደ ከፍታ ተመለስ።

9 ጌታ በሕዝቦች ላይ ይፈርዳል፥ አቤቱ፥ እንደጽድቄ ፍረድልኝ፥ እንደ የዋህነቴም ይሁንልኝ።

10 የክፉዎች በደል ይጥፋ፥ ጻድቁን ግን አቅና፥ እግዚአብሔር ልብንና ኩላሊትን ይመረምራል።

11 ጋሻዬ በእግዚአብሔር ዘንድ ነው ልበ ቅኖችን የሚያድናቸው።

12 እግዚአብሔር ጻድቅ ዳኛ ነው፥ ሁልጊዜ ትክክለኛ ፈራጅ ነው፥

13 ለማይመለስ ግን ሰይፉን ይስላል፥ ቀስቱን ወጥሮአል አዘጋጅቷልም፥

14 የሞት መሣርያንም አሰናድቷል፥ ፍላጻዎቹንም የሚንበለበሉ አደረገ።

15 እነሆ፥ ክፋትን ያማጠ ተንኮልን ፀነሰ፥ ውሸትንም ወለደ።

16 ጉድጓድን ማሰ ቈፈረም። በሠራውም ጉድጓድ ይወድቃል።

17 ጉዳቱ በራሱ ይመለሳል፥ ዓመፃውም በአናቱ ላይ ትወርዳለች።

18 ጌታን ስለ ጽድቁ አመሰግነዋለሁ፥ ለልዑል ጌታም ስም እዘምራለሁ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos