መዝሙር 144 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ስለ ጎልያድ፥ የዳዊት መዝሙር። 1 ስለ ጎልያድ፥ የዳዊት መዝሙር። ጌታዬ ዐለቴ፥ ይባረክ፥ ለእጆቼ ሰልፍን፥ ለጣቶቼም ዘመቻን የሚያስተምር፥ 2 መሓሪዬና መሸሸጊያዬ፥ መጠጊያዬና መድኃኒቴ፥ ረዳቴና መታመኛዬም፥ ሕዝቤንም ከእኔ በታች የሚያስገዛልኝ። 3 አቤቱ፥ እርሱን ታውቀው ዘንድ ሰው ምንድነው? ታስብለት ዘንድ የሰው ልጅ ምንድነው? 4 ሰው ከንቱን ነገር ይመስላል፥ ዘመኑ እንደ ጥላ ያልፋል። 5 አቤቱ፥ ሰማዮችህን ዝቅ ዝቅ አድርጋቸው ውረድም፥ ተራሮችን ዳስሳቸው ይጢሱም። 6 መብረቆችህን ብልጭ አድርጋቸው በትናቸውም፥ ፍላጾችህን ላካቸው አስደንግጣቸውም። 7-8 እጅህን ከአርያም ላክ አድነኝም ከብዙ ውኆች፥ አፋቸውም ምናምንን ከሚናገር፥ ቀኛቸው የሐሰት ቀኝ ከሆነ፥ ከባዕድ ልጆች እጅ አስጥለኝ። 9 አቤቱ፥ አዲስ ቅኔ እቀኛልሃለሁ፥ ዐሥር አውታር ባለው በገና እዘምርልሃለሁ። 10 ለነገሥታት መድኃኒትን የሚሰጥ፥ ባርያውን ዳዊትን ከክፉ ሰይፍ የሚያድነው እርሱ ነው። 11 አድነኝ፥ አፋቸውም ምናምንን ከሚናገር፥ ቀኛቸውም የሐሰት ቀኝ ከሆነ፥ ከባዕድ ልጆች እጅ አስጥለኝ። 12 ልጆቻቸን በጉልማስነታቸው እንደ አዲስ አትክልት ይሁኑ፥ ሴቶች ልጆቻቸንም እንደ እልፍኝ ይመሩና ያጊጡ፥ 13 ዕቃ ቤቶቻቸንም ይሞሉ፥ በየዓይነቱም ዕቃ ይኑራቸው፥ በጎቻቸንም ብዙ ይውለዱ፥ በማሰማርያችንም ይብዙ፥ 14 ላሞቻቸንም የሰቡ ይሁኑ፥ ቅጥራቸውም መፍረሻና መውጫ አይኑረው፥ በአደባባዮቻችንም ዋይታ አይኑር፥ 15 እንደዚህ የሚሆንለት ሕዝብ የተመሰገነ ነው፥ ጌታ አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ምስጉን ነው። |