መዝሙር 112 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ሃሌ ሉያ። ጌታን የሚፈራ፥ ትእዛዙንም እጅግ የሚወድድ ሰው ብፁዕ ነው። 2 ዘሩ በምድር ላይ ኃያል ይሆናል፥ የቅኖች ትውልድ ትባረካለች። 3 ክብርና ሀብት በቤቱ ነው፥ ጽድቁም ለዘለዓለም ይኖራል። 4 ለቅኖች ብርሃን በጨለማ ወጣ፥ መሓሪ፥ ርኅሩኅና ጻድቅ ነው። 5 ቸር ሰው ይራራል ያበድራልም፥ ነገሩንም በቀና መንገድ ይፈጽማል። 6 ለዘለዓለም አይናወጥም፥ የጻድቅ መታሰቢያ ለዘለዓለም ይኖራል። 7 ክፉ ዜናን አይፈራም፥ ልቡ የጸና፥ በጌታም የታመነ ነው። 8 በጠላቶቹ ላይ እስኪኮራ ድረስ ልቡ ጽኑ ነው፥ አይፈራምም። 9 በተነ፥ ለችግረኞችም ሰጠ፥ ጽድቁ ለዘለዓለም ዓለም ይኖራል፥ ቀንዱም በክብር ከፍ ከፍ ይላል። 10 ክፉ ሰውም አይቶት ይቈጣል፥ ጥርሱንም ያፋጫል፥ ይቀልጣልም፥ የክፉዎች ምኞት ትጠፋለች። |