መዝሙር 110 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 የዳዊት መዝሙር። ጌታ ጌታዬን፦ “ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው።” 2 ጌታ የኃይልን በትር ከጽዮን ይልክልሃል፥ በጠላቶችህም መካከል ግዛ። 3 ግርማዊ ክብር ከልደትህ ጊዜ አንሥቶ፥ የተቀደሰ ሞገስም ከማኅጸን፥ የወጣትነትም ጠል የአንተ ነው። 4 “እንደ መልከጼዴቅ ሥርዓት አንተ ለዘለዓለም ካህን ነህ ብሎ”፥ ጌታ ማለ፥ አይጸጸትምም። 5 ጌታ በቀኝህ፥ ነገሥታትን በቁጣው ቀን ይቀጠቅጣቸዋል። 6 በአሕዛብ መካከል ይፈርዳል፥ ሬሳዎችንም ይከምራል፥ በሰፊ ምድር ላይ ራሶችን ይቀጠቅጣል። 7 በመንገድ ከፈሳሽ ውኃ ይጠጣል፥ ከዚህም የተነሣ ራሱን ከፍ ከፍ ያደርጋል። |