Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘኍል 9 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የፋሲካ በዓል በሲና ምድረ በዳ መከበሩ

1 ከግብጽም ምድር በወጡ በሁለተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር በሲና ምድረ በዳ ጌታ ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦

2 “የእስራኤል ልጆች በተወሰነለት ጊዜ የፋሲካን በዓል ያክብሩ፤

3 በዚህ ወር በዓሥራ አራተኛው ቀን ምሽት ላይ፥ በተወሰነለት ጊዜ ታደርጉታላችሁ፤ እንደ ሥርዓቱ ሁሉ እንደ ደንቡም ሁሉ ታደርጉታላችሁ።”

4 ሙሴም የፋሲካን በዓል እንዲያከብሩ ለእስራኤል ልጆች ነገራቸው።

5 በመጀመሪያውም ወር በዓሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ በሲና ምድረ በዳ የፋሲካን በዓል አከበሩ፤ ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ የእስራኤል ልጆች አደረጉ።

6 የሞተ ሰው ሬሳን በመንካት የረከሱ ሰዎችም ነበሩ፥ ስለዚህም በዚያ ቀን የፋሲካን በዓል ለማክበር አልቻሉም ነበር። በዚያም ቀን በሙሴና በአሮን ፊት ቀረቡ።

7 እነዚያም ሰዎች እርሱን እንዲህ አሉት፦ “የሞተውን ሰው ሬሳ በመነንካት ብንረክስም እንኳ፥ በእስራኤል ልጆች መካከል የጌታን ቁርባን በተወሰነለት ጊዜ እንዳናቀርብ ለምን እንከለከላለን?”

8 ሙሴም፦ “ጌታ ስለ እናንተ የሚያዝዘውን እስክሰማ ድረስ ጠብቁ” አላቸው።

9 ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦

10 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ከእናንተ ወይም ከትውልዶቻችሁ ዘንድ ሰው ሬሳን በመንካት ቢረክስ፥ ወይም ሩቅ መንገድ ቢሄድ፥ እርሱ እንዲህም ሆኖ እንኳ ለጌታ የፋሲካን በዓል ያክብር።

11 በዓሉንም በሁለተኛው ወር በዓሥራ አራተኛው ቀን ምሽት ላይ ያክብሩ፤ እርሾ ካልገባበት ቂጣና ከመራራ ቅጠል ጋር ይብሉት።

12 ከእርሱም እስከ ማግስቱ ጥዋት ድረስ ምንም አያስቀሩ፥ ከእርሱም አጥንትን አይስበሩ፤ እንደ ፋሲካ ሥርዓት ሁሉ ያክብሩት።

13 ነገር ግን ንጹሕ የሆነ ሰው በመንገድም ላይ ያልሆነ የፋሲካን በዓል ባያከብር፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ዘንድ ተለይቶ ይጠፋል፤ የጌታን ቁርባን በተወሰነለት ጊዜ አላቀረበምና ያ ሰው ኃጢአቱን ይሸከማል።

14 በመካከላችሁም መጻተኛ ቢኖር፥ ለጌታም የፋሲካን በዓል ቢያከብር፥ እንደ ፋሲካ ሥርዓትና እንደ ደንቡ እንዲሁ ያክብር፤ ለመጻተኛና ለአገሩ ተወላጅ አንድ ዓይነት ሥርዓት ይኑራችሁ።”


ደመናውና እሳቱ

15 ማደሪያውም በተተከለ ቀን ደመናው ማደሪያውን፥ የምስክሩን ድንኳን ሸፈነው፤ ከማታም ጀምሮ እስከ ጥዋት ድረስ በማደሪያው ላይ ነበረ፤ እርሱም እንደ እሳት ያለ አምሳል ነበረ።

16 ሁልጊዜ በማደርያው ላይ እንዲሁ ነበረ፤ በቀን ደመና በሌሊትም የእሳት አምሳል ይሸፍነው ነበር።

17 ደመናውም ከድንኳኑ ላይ በማናቸውም ጊዜ ሲነሣ በዚያን ጊዜ የእስራኤል ልጆች ይጓዙ ነበር፤ ደመናውም ባረፈበት ስፍራ በዚያ የእስራኤል ልጆች ይሰፍሩ ነበር።

18 በጌታ ትእዛዝ የእስራኤል ልጆች ይጓዙ ነበር፥ በጌታም ትእዛዝ ይሰፍሩ ነበር፤ ደመናው በማደሪያው ላይ ባረፈበት ጊዜያት ሁሉ በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር።

19 ደመናውም በማደሪያው ላይ ለብዙ ቀኖች በቈየም ጊዜ እንኳ የእስራኤል ልጆች የጌታን ትእዛዝ ይጠብቁ ነበር፥ አይጓዙምም ነበር።

20 አንዳንድ ጊዜ ደመናው ለጥቂት ቀኖች በማደሪያው ላይ ይቈይ ነበር፤ በዚያ ጊዜ እንደ ጌታ ትእዛዝ በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር፤ እንደ ጌታም ትእዛዝ ይጓዙ ነበር።

21 አንዳንድ ጊዜም ደመናው ከማታ ጀምሮ እስከ ጥዋት ድረስ ይቈይ ነበር፤ በጥዋትም ደመናው በተነሣ ጊዜ ይጓዛሉ፥ ወይም ባለማቋረጥ ቀኑንም ሌሊቱንም የሚቈይ ቢሆን፥ ደመናው በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር።

22 ደመናውም ሁለት ቀን ወይም አንድ ወር ወይም ረጅም ጊዜ ቆይቶ በማደሪያው ላይ ቢቀመጥ የእስራኤል ልጆች በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር፥ አይጓዙምም ነበር፤ ነገር ግን በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር።

23 በጌታ ትእዛዝ ይሰፍሩ ነበር፥ በጌታም ትእዛዝ ይጓዙ ነበር፥ ጌታ በሙሴ አንደበት እንዳዘዘ የጌታን ትእዛዝ ይጠብቁ ነበር።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos