Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘኍል 12 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


አሮንና ማርያም በሙሴ ላይ መቅናታቸው

1 ሙሴም ኢትዮጵያይቱን በእርግጥ አግብቶአልና ባገባት በኢትዮጵያይቱ ምክንያት ማርያምና አሮን በእርሱ ላይ ተናገሩ።

2 እነርሱም፦ “በውኑ ጌታ የተናገረው በሙሴ በኩል ብቻ ነውን? በእኛስ በኩል ደግሞ ተናገሮ የለምን?” አሉ፤ ጌታም ሰማ።

3 ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበረ።

4 በድንገትም ጌታ ሙሴንና አሮንን ማርያምንም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ሦስታችሁ ወደ መገኛኛው ድንኳን ውጡ፤” ሦስቱም ወጡ።

5 ጌታም በደመና ዓምድ ውስጥ ሆኖ ወረደ፥ በድንኳኑም ደጃፍ ቆሞ አሮንንና ማርያምን ጠራ፥ ሁለቱም ወደ እርሱ መጡ።

6 እርሱም እንዲህ አለ፦ “እባካችሁ፥ ቃሎቼን ስሙ፤ በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር፥ እኔ ጌታ በራእይ እገለጥለታለሁ፥ ወይም በሕልም እናገረዋለሁ።

7 ከባርያዬ ከሙሴ ጋር ግን እንዲህ አይደለም፤ እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው።

8 እኔ በምሳሌ ሳይሆን እፊት ለፊት ከእርሱ ጋር በግልጥ እነጋገራለሁ፤ የጌታንም ሀልዎተ-ቅርፅ ይመለከታል፤ ታዲያ፥ በባርያዬ በሙሴ ላይ ለመናገር ለምን አልፈራችሁም?”

9 በእርሱም ላይ የጌታ ቁጣ ነደደ፤ እርሱም ትቶአቸው ሄደ።

10 ደመናውም ከድንኳኑ በተነሣ ጊዜ እነሆ፥ ማርያም በለምጽ ደዌ ተይዛ እንደ በረዶ ነጭ ሆና ነበር፤ አሮንም ወደ ማርያም ዘወር አለ፥ እነሆም፥ በለምጽ ደዌ ተይዛ ተመለከተ።

11 አሮንም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ጌታዬ ሆይ! ተሞኝተን ይህን አድርገናልና፥ ኃጢአትንም ሠርተናልና እባክህ፥ ኃጢአትን በእኛ ላይ አትቁጠርብን።

12 ከእናቱ ሆድ በወጣ ጊዜ ግማሽ ሥጋው ተበልቶ በማኅፀን እንደ ሞተ ልጅ እርሷ እባክህ፥ አትሁን።”

13 ሙሴም እንዲህ ብሎ ወደ ጌታ ጮኸ፦ “አቤቱ፥ እባክህ፥ ፈውሳት።”

14 ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አባትዋ ምራቁን በፊትዋ ቢተፋባት እንኳ እርሷ ሰባት ቀን ልታፍር አይገባትምን? ሰባት ቀን ከሰፈሩ ውጪ ተዘግቶባት ትቀመጥ፥ ከዚያም በኋላ ትመለስ።”

15 ማርያምም ከሰፈሩ ውጪ ሰባት ቀን ተዘግቶባት ተቀመጠች፤ ማርያምም እስክትመለስ ድረስ ሕዝቡ አልተጓዙም።

16 ከዚያም በኋላ ሕዝቡ ከሐጼሮት ተጓዙ፥ በፋራንም ምድረ በዳ ሰፈሩ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos