ሚክያስ 6 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)እግዚአብሔር እስራኤልን እንደ ወቀሰ 1 ጌታ የሚለውን ስሙ፥ ተነሥ፥ በተራሮች ፊት ክርክራችሁን አቅርቡ፥ ኮረብቶች ቃልህን ይስሙ። 2 ተራሮች ሆይ፥ ጠንካሮች የምድር መሠረቶችም ሆይ፥ የጌታን ወቀሳ ስሙ፤ ጌታ ከሕዝቡ ጋር ክርክር አለውና፥ ከእስራኤልም ጋር ይዋቀሳልና። 3 ሕዝቤ ሆይ፥ ምን አደረግሁህ? ያደከምኩህስ እንዴት ነው? መልስልኝ። 4 ከግብጽ ምድር አውጥቼሃለሁ፥ ከባርነት ቤትም ተቤዥቼሃለሁና፤ በፊትህም ሙሴን፥ አሮንንና ማርያምን ላክሁልህ። 5 ሕዝቤ ሆይ፥ የሞዓብ ንጉሥ ባላቅ ያቀደውን፥ የቤዖር ልጅ በለዓም የመለሰለትን፥ የጌታን ጽድቅ እንድታውቅ ከሺጢም ጀምሮ እስከ ጌልገላ ድረስ የሆነውን እባክህን አስታውስ። እግዚአብሔር ከሕዝቡ የሚፈልገው ነገር 6 ምን ይዤ ወደ ጌታ ፊት ልቅረብ፥ በልዑል አምላክ ፊት ልስገድን? የሚቃጠል መሥዋዕትና የአንድ ዓመት ጥጃ ይዤ በፊቱ ልቅረብን? 7 ጌታስ በእልፍ አውራ በጎች፥ በብዙ የዘይት ፈሳሾች ደስ ይለዋልን? የበኩር ልጄን ስለ በደሌ፥ የሆዴንም ፍሬ ስለ ነፍሴ ኃጢአት ልስጠውን? 8 ሰው ሆይ፥ መልካም ምን እንደሆነ ለአንተ ነግሮሃል፤ ፍትሕን እንድታደርግ፥ ምሕረትን እንድትወድና ከአምላክህም ጋር በትሕትና እንድትሄድ ካልሆነ በቀር ጌታ ከአንተ የሚፈልገው ምንድነው? ማታለልና ዓመጽ እንደሚያስቀጣ 9 የጌታ ድምፅ ከተማይቱን ይጠራታል፤ ስምህን መፍራት ጥበብ ነው፤ ወገን ሆይ፥ ያዘጋጀው ማን እንደሆነ ስሙ። 10 በክፉ ቤት የክፋት መዝገብ፥ አስጸያፊ ሐሰተኛ መስፈሪያ አሁንም አለን? 11 የክፋት ሚዛንንና የአታላይ መመዘኛ ከረጢት አነጻለሁን? 12 ባለ ጠጎችዋ ግፍ ተሞልተዋል፤ በውስጧ የሚኖሩትም ሐሰት ተናግረዋል፥ ምላሳቸውም በአፋቸው ውስጥ አታላይ ነው። 13 ስለዚህ እኔ ደግሞ በክፉ ቁስል መታሁህ፤ ስለ ኃጢአትህም አፈረስሁህ። 14 ትበላለህ፥ ነገር ግን አትጠግብም፥ ባዶነትህም በመካከልህ ይሆናል፤ ትወስዳለህ፥ ነገር ግን ወደ ደህንነት አታመጣም፥ ወደ ደህንነት ያመጣኸውንም ለሰይፍ እሰጣለሁ። 15 ትዘራለህ፥ ነገር ግን አታጭድም፤ ወይራ ትጨምቃለህ፥ ነገር ግን ዘይቱን አትቀባም፤ ወይን ትጨምቃለህ፥ ነገር ግን የወይን ጠጁን አትጠጣም። 16 የዖምሪን ሥርዓትና የአክዓብን ቤት ሥራ ሁሉ ጠብቀሃልና፥ በምክራቸውም ሄዳችኋልና፤ ስለዚህ አንተን ለጥፋት ነዋሪዎቿን ደግሞ ለመዘባበቻ ሰጥቻችኋለሁ፥ የሕዝቤንም ስድብ ትሸከማላችሁ። |