Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ማቴዎስ 4 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የኢየሱስ ክርስቶስ መፈተን
( ማር. 1፥12-13 ፤ ሉቃ. 4፥1-13 )

1 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በዲያብሎስ እንዲፈተን መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው።

2 አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ተራበ።

3 ፈታኙ መጥቶ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ እዘዝ” አለው።

4 እርሱ ግን “‘ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፎአል” ሲል መለሰለት።

5 ከዚህ በኋላ ዲያቢሎስ ወደ ቅድስት ከተማ ወስዶ በቤተ በመቅደሱ ጫፍ ላይ አቆመውና

6 “‘መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል፤ እግርህም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል’ ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ ራስህን ወደ ታች ወርውር” አለው።

7 ኢየሱስም “‘ጌታ አምላክህን አትፈታተነው’ ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል” አለው።

8 እንደገና ዲያቢሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፤ የዓለምን መንግሥታት ሁሉና ክብራቸውን አሳየውና፥

9 “ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው።

10 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ “ሂድ አንተ ሰይጣን ‘ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ’ ተብሎ ተጽፎአልና” አለው።

11 ከዚህ በኋላ ዲያቢሎስ ተወው፤ እነሆ መላእክት መጥተው አገለገሉት።


ኢየሱስ የማስተማር ሥራውን በገሊላ እንደ ጀመረ
( ማር. 1፥14-15 ፤ ሉቃ. 4፥14-15 )

12 ኢየሱስ ዮሐንስ እንደታሰረ በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ ሄደ።

13 ናዝሬትንም ትቶ በዛብሎንና በንፍታሌም ክልል ወደ አለችው በባሕር አጠገብ ወደምትገኝ ወደ ቅፍርናሆም መጥቶ ኖረ።

14 ይህም የሆነው በነቢዩ በኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው እንዲፈጸም ነው፤

15 “የዛብሎን ምድርና የንፍታሌም ምድር፥ በዮርዳኖስ ማዶ ያለ፥ የባሕር መንገድ፥ የአሕዛብ ገሊላ፤

16 በጨለማ የተቀመጠ ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፤ በሞት አገርና በሞት ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው።”

17 ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢየሱስ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” እያለ መስበክ ጀመረ።


ኢየሱስ አራት ዓሣ አጥማጆችን እንደ ጠራ
( ማር. 1፥16-20 ፤ ሉቃ. 5፥1-11 )

18 በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ ሳለ፥ ሁለት ወንድማማቾች፥ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንንና ወንድሙን እንድርያስን ዓሣ አጥማጆች ነበሩና መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ።

19 እርሱም “ኑ ተከተሉኝ፤ ሰዎችን አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው።

20 ወዲያውኑ መረባቸውን ጥለው ተከተሉት።

21 ከዚያም እልፍ ብሎ ሌሎች ሁለት ወንድማማቾች የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን በታንኳ ውስጥ ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር መረባቸውን ሲጠግኑ አየና ጠራቸው።

22 እነርሱም ወዲያውኑ ታንኳይቱንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት።


ኢየሱስ ብዙ ሰዎችን እንዳስተማረና እንደ ፈወሰ
( ሉቃ. 6፥17-19 )

23 ኢየሱስም በምኵራቦቻቸው እያስተማረ፥ የመንግሥትን ወንጌል እየሰበከ፥ በሕዝቡ መካከል ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዘዋወር ነበር።

24 ዝናው በመላዋ ሶርያ ሁሉ ተሰማ፤ በልዩ ልዩ ደዌና ሥቃይ ተይዘው የታመሙትን ሁሉ፥ አጋንንት ያደሩባቸውን፥ በጨረቃ የሚነሣባቸውንና ሽባዎችን ወደ እርሱ አመጡ፤ እርሱም ፈወሳቸው።

25 ከገሊላ፥ ከዐሥሩ ከተሞች፥ ከኢየሩሳሌም፤ ከይሁዳና ከዮርዳኖስ ማዶ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos