ሚልክያስ 4 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ታላቁ የጌታ ቀን 1 “እነሆ፥ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድ ቀን ይመጣል፤ ትዕቢተኞች ሁሉና ኃጢአትን የሚሠሩ ሁሉ ገለባ ይሆናሉ፤ የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋል” ይላል የሠራዊት ጌታ፤ ሥርንና ቅርንጫፍንም አያስቀርላቸውም። 2 ስሜን ለምትፈሩት ለእናንተ ግን የጽድቅ ፀሐይ ትወጣላችኋለች፥ ፈውስም በክንፎችዋ ውስጥ ይሆናል፤ እናንተም ትወጣላችሁ፥ ከጋጣ እንደ ወጡ ጥጃዎች ትቦርቃላችሁ። 3 እኔ በምሠራበት ቀን ክፉዎችን ትረግጧቸዋላችሁ፥ ከእግራችሁ ጫማ በታች አመድ ይሆናሉና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። 4 ለእስራኤል ሁሉ ሥርዓትንና ፍርድን አድርጌ በኮሬብ ያዘዝሁትን የአገልጋዬን የሙሴን ሕግ አስታውሱ። 5 እነሆ፥ ታላቁና አስፈሪው የጌታ ቀን ከመምጣቱ በፊት ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ። 6 መጥቼ ምድርን በእርግማን እንዳልመታ፥ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፥ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶቻቸው ይመልሳል። |