Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘሌዋውያን 7 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 “የበደል መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው፤ እርሱም እጅግ የተቀደሰ ነው።

2 የሚቃጠለውን መሥዋዕት በሚያርዱበት ስፍራ የበደሉን መሥዋዕት ያርዱታል፤ ደሙንም በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጨዋል።

3 ስቡንም ሁሉ፥ ላቱንም፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ ያቀርበዋል።

4 ሁለቱንም ኩላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኩላሊቶቹ ጋር ይወስዳል።

5 ካህኑም ለጌታ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ እርሱ የበደል መሥዋዕት ነው።

6 ከካህናት ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ይበላዋል፤ በተቀደሰ ስፍራ ይበላል፤ እርሱም እጅግ የተቀደሰ ነው።

7 የበደል መሥዋዕት እንደ ኃጢአት መሥዋዕት ነው፤ ለሁለቱ አንድ ሕግ አለ፤ ያም በእነርሱ የሚያስተሰርይ ካህን ከእነርሱ ላይ ለራሱ ስለ ሚወስድ ነው።

8 እንዲሁም የማናቸውንም ሰው የሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርብ ካህን፥ ያቀረበው የሚቃጠለው መሥዋዕት ቆዳ ለዚያው ካህን ይሆናል።

9 በምድጃ ላይ የተጋገረው፥ በመጥበሻም ወይም በምጣድ ላይ የተዘጋጀው የእህል ቁርባን ሁሉ ለሚያቀርበው ካህን ይሆናል።

10 በዘይትም የተለወሰው ወይም የደረቀው የእህል ቁርባን በጠቅላላ ለአሮን ልጆች ሁሉ ይሆናል፤ እያንዳንዱም እንደሌላው ወንድሙ ይደርሰዋል።


ተጨማሪ ትእዛዛት

11 “ሰው ለጌታ የሚያቀርበው የአንድነት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው።

12 የሚያቀርውም ለምስጋና ቢሆን፥ ከምስጋናው መሥዋዕት ጋር እርሾ ያልገባበት በዘይት የተለወሰ የቂጣ እንጎቻ፥ እርሾ ያልነካው በዘይትም የተቀባ ስስ ቂጣ፥ በዘይትም የተለወሰ መልካም ዱቄት ያቀርባል።

13 ለምስጋና የሚሆነውን የአንድነት መሥዋዕቱን ባቀረበ ጊዜ እርሾ ያለበትን ኅብስት ያቀርባል።

14 ለጌታ እንደ ስጦታ አድርጎ አንድ ኅብስት ከእያንዳንዱ ቁርባን ያቀርባል። ከእርሱም የቀረው የአንድነትን መሥዋዕት ደም ለሚረጨው ካህን ይሆናል።

15 “ለምስጋና የሚሆነውን የአንድነት መሥዋዕቱን ሥጋ በሚያቀርብበት ቀን ይበላ፤ ከእርሱ እስከ ነገ ምንም አያሳድር።

16 የቁርባኑም መሥዋዕት የስእለት ወይም የፈቃድ ቢሆን፥ መሥዋዕቱን በሚያቀርብበት ቀን ይበላ፤ ከእርሱም የቀረውን በማግስቱ ይበላ፤

17 ነገር ግን በሦስተኛው ቀን ከመሥዋዕቱ የተረፈው ሥጋ በእሳት ይቃጠል።

18 በሦስተኛው ቀን ከአንድነቱ መሥዋዕት ከቶ ሥጋ ቢበላ፥ አይሠምርለትም ላቀረበው ሰው የተጠላ ይሆንበታል እንጂ ቁርባን ሆኖ አይቈጠርለትም፤ ሰውም ከእርሱ ቢበላ ኃጢአቱን ይሸከማል።

19 “ሥጋው ማናቸውንም ርኩስ ነገር ከነካ አይበላ፤ በእሳት ይቃጠል። ሌላውን ሥጋ ግን ንጹሕ የሆነ ሰው ሁሉ ከሥጋው ይብላ።

20 ነገር ግን የረከሰ ሰው ሆኖ ሳለ፥ ለጌታ ከሆነው ከአንድነት መሥዋዕት ሥጋ የበላ እንደሆነ፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ።

21 ማንም ሰው የሰውን ርኩሰት ወይም የረከሰን እንስሳ ወይም ምንም ዓይነት ርኩስ ሆኖ የተጠላን ማናቸውንም ርኩስ ነገር ነክቶ፥ ለጌታ ከሆነው ከአንድነት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ።”

22 ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦

23 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ የበሬ ወይም የበግ ወይም የፍየል ስብ ከቶ አትብሉ።

24 ሞቶ የተገኘን የእንስሳ ስብ፥ እንዲሁም አውሬ የገደለውን የእንስሳ ስብ ለማናቸውም ለሌላ ተግባር አድርጉት እንጂ ከእርሱ ፈጽሞ ምንም አትብሉ፤

25 ለጌታ በእሳት ከሚያቀርበው ከእንስሳ ስብ የሚበላ ሰው ሁሉ፥ ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋ።

26 በማደሪያዎቻችሁም ሁሉ የወፍ ወይም የእንስሳ ደም ቢሆን ፈጽሞ አትብሉ።

27 ማንም ሰው ደም የሚበላ ያ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጥፋ።”

28 ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦

29 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ለጌታ የአንድነትን መሥዋዕት የሚያቀርብ ሰው ቁርባኑን ለጌታ ከሰላሙ መሥዋዕት ያመጣል።

30 የእርሱ እጆች ለጌታ በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን ያመጣሉ፤ እርሱም ፍርምባው በጌታ ፊት ለመወዝወዝ ቁርባን እንዲወዘወዝ ፍርምባውን ከስቡ ጋር ያመጣዋል።

31 ካህኑም ስቡን በመሠዊያው ላይ ያቃጥላል፤ ፍርምባው ግን ለአሮንና ለልጆቹ ይሆናል።

32 ከሰላም መሥዋዕታችሁ ቀኝ ወርቹን እንደ ቁርባን አድርጋችሁ ለካህኑ ትሰጡታላችሁ።

33 ከአሮንም ልጆች መካከል የአንድነትን መሥዋዕት ደሙንና ስቡን ለሚያቀርበው ለእርሱ ቀኝ ወርቹ ድርሻው ይሆናል።

34 የሚወዘወዘውን ፍርምባና እንደ ቁርባን የሚቀርበውን ወርች ከእስራኤል ልጆች ከሰላም መሥዋዕታቸው ወስጄ፥ ለካህኑ ለአሮንና ለልጆቹም ለዘለዓለም ድርሻ እንዲሆን ከእስራኤል ልጆች ዘንድ እነርሱን ሰጥቼአቸዋለሁ።

35 “ጌታን በክህነት እንዲያገለግሉት እነርሱን ባቀረባቸው ቀን ለጌታ በእሳት ከሚቀርበው ቁርባን የአሮንና የልጆቹ ድርሻ ይህ ነው።

36 ለልጅ ልጃቸው ለዘለዓለም ድርሻቸው እንዲሆን በቀባቸው ቀን ከእስራኤል ልጆች እንዲሰጣቸው ጌታ ያዘዘው ይህ ነው።

37 የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቁርባን፥ የኃጢአትና የበደል መሥዋዕት፥ የቅድስናና የአንድነት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው።

38 ጌታ በሲና ምድረ በዳ ቁርባናቸውን ለጌታ እንዲያቀርቡ ለእስራኤል ልጆች ባዘዘ ጊዜ በሲና ተራራ ለሙሴ ያዘዘው ይህ ነው።”

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos