Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘሌዋውያን 3 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የአንድነት ቁርባን

1 “ቁርባኑም የአንድነት መሥዋዕት ቢሆን፥ ከበሬ መንጋ ተባት ወይም እንስት ቢያቀርብ፥ ነውር የሌለበትን በጌታ ፊት ያቅርብ።

2 እጁንም ለቁርባን ባቀረበው እንስሳ ራስ ላይ ይጭናል፥ በመገናኛውም ድንኳን ደጃፍ አጠገብ ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል።

3 ከሰላሙም መሥዋዕት ለጌታ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን አድርጎ የሚያቀርበው፤ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥

4 ሁለቱንም ኩላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኩላሊቶች ጋር ወስዶ ነው።

5 የአሮንም ልጆች ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋር በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በእንጨቱ ላይ ያቃጥሉታል፤ ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ የሆነ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን ነው።

6 “ለጌታም ለአንድነት መሥዋዕት የሚያቀርበው ቁርባኑ ከበጎች ተባት ወይም እንስት ቢሆን፥ ነውር የሌለበትን ያቀርባል።

7 ለቁርባኑ ጠቦትን ቢያቀርብ በጌታ ፊት ያቀርበዋል፤

8 እጁንም ለቁርባን ባቀረበው እንስሳ ራስ ላይ ይጭናል፥ በመገናኛውም ድንኳን ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል።

9 ከሰላሙም መሥዋዕት ለጌታ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን አድርጎ የሚያቀርበው፤ ስቡን፥ እስከ ጀርባውም ድረስ የተቈረጠ ላቱን ሁሉ፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥

10 ሁለቱንም ኩላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኩላሊቶች ጋር ወስዶ ነው።

11 ካህኑም ለጌታ በእሳት ላይ የሚቀርብ ማዕድ አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል።

12 “ቁርባኑም ፍየል ቢሆን በጌታ ፊት ያቀርበዋል፤

13 እጁንም በራሱ ላይ ይጭንበታል፥ በመገናኛውም ድንኳን ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል።

14 ከእርሱም ለጌታ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን አድርጎ ከቁርባኑ የሚያቀርበው፤ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥

15 ሁለቱንም ኩላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኩላሊቶች ጋር ወስዶ ነው።

16 ካህኑም መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርብ ማዕድ አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። ስቡ ሁሉ ለጌታ ነው።

17 በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ ፈጽሞ ማንኛውንም ስብና ደም እንዳትበሉ የዘለዓለም ሥርዓት ነው።”

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos