ዘሌዋውያን 27 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የመጠጥ ቁርባን 1 ጌታ ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ለእነርሱ ተናገር፦ ማናቸውም ሰው ሰውን ለጌታ ሊሰጥ ቢሳል፥ አንተ እንደምትገምተው መጠን ስለ ሰው ተመጣጣኝ የሆነውን ዋጋ ይስጥ። 3 ለወንድ ከሃያ ዓመት ጀምሮ እስከ ስልሳ ዓመት ድረስ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ግምትህ ኀምሳ የብር ሰቅል ይሁን። 4 ሴትም ብትሆን ግምትህ ሠላሳ ሰቅል ይሁን። 5 ከአምስት ዓመትም ጀምሮ እስከ ሀያ ዓመት ድረስ ግምትህ ለወንድ ሀያ ሰቅል፥ ለሴትም ዐሥር ሰቅል ይሁን። 6 ከአንድ ወርም እስከ አምስት ዓመት ድረስ ለወንድ ግምትህ አምስት የብር ሰቅል፥ ለሴትም ግምትህ ሦስት የብር ሰቅል ይሁን። 7 ዕድሜውም ስልሳ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆነው ሰው ቢሆን ለወንድ ግምትህ ዐሥራ አምስት ሰቅል፥ ለሴትም ዐሥር ሰቅል ይሁን። 8 ማናቸውም ሰው ለግምትህ ከድህነቱ የተነሣ የሚከፍለውን ቢያጣ እርሱም በካህኑ ፊት የስለቱን ሰው የምጣው፥ ካህኑም እርሱን ይገምተው፤ ካህኑም የተሳለው ሰው አቅሙ እንደሚፈቅደው መጠን ይገምትለት። 9 “ለጌታም መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርበው እንስሳ ቢሆን፥ ሰው ከእነዚህ ለጌታ የሚሰጠው ሁሉ ቅዱስ ይሆናል። 10 መልካሙን በክፉ ወይም ክፉውን በመልካም ቢሆንም እንኳ እርሱን በሌላ አትተካ ወይንም አትለውጥ፤ እንስሳንም በእንስሳ ቢለውጥ እርሱና ልዋጩ ሁለቱም የተቀደሱ ይሆናሉ። 11 እንስሳው ለጌታ መሥዋዕት መሆን የማይገባው ርኩስ ቢሆን፥ እንስሳውን በካህኑ ፊት ያምጣው። 12 ካህኑም መልካም ወይም መጥፎ እንደሆነ ይገምተዋል፤ ካህኑም እንደሚገምተው መጠን እንዲሁ ይሁን። 13 እርሱም ሊቤዠው ቢወድድ ግን በተገመተው ላይ አምስት እጅ ይጨምር። 14 “ለጌታም ቅዱስ ይሆን ዘንድ ሰው ቤቱን ቢቀድስ፥ ካህኑ መልካም ወይም መጥፎ እንደሆነ ይገምተዋል፤ ካህኑም እንደሚገምተው መጠን እንዲሁ ይጸናል። 15 የቀደሰውም ሰው ቤቱን ሊቤዠው ቢወድድ በገመትከው የገንዘብ መጠን ላይ አምስት እጅ ይጨምራል፤ ቤቱም ለእርሱ ይሆናል። 16 “ሰውም ከርስቱ እርሻ ለጌታ ቢቀድስ፥ ግምትህ ለእርሻው እንደሚያስፈልገው የዘር መጠን ይሁን፤ አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ገብስ የሚዘራበት እርሻ ኀምሳ የብር ሰቅል ይገመታል። 17 እርሻውንም ከኢዮቤልዩ ዓመት ጀምሮ ቢቀድስ፥ እንደ ግምትህ መጠን ይጸናል። 18 ነገር ግን እርሻውን ከኢዮቤልዩ ዓመት በኋላ ቢቀድስ፥ ካህኑ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ እንደ ቀሩት ዓመታት ቊጥር ገንዘቡን ያስላልህስ፤ ከዚያም ከግምትህ ላይ ይቀነሳል። 19 እርሻውንም የቀደሰ ሰው ሊቤዠው ቢወድድ፥ በገመትከው የገንዘብ መጠን ላይ አምስት እጅ ይጨምራል፤ ከዚያም ለእርሱ ይጸናለታል። 20 እርሻውንም ባይቤዠው፥ ወይም ለሌላ ሰው ቢሸጥ፥ እንደገና ሊቤዠው አይችልም። 21 እርሻው ግን በኢዮቤልዩ ነፃ ሲወጣ እንደ እርም ለጌታ የተቀደሰ እርሻ ይሆናል፤ ለካህኑ ርስቱ ይሆናል። 22 ከርስቱ እርሻ ያልሆነውን የገዛውን እርሻ ለጌታ ቢቀድስ፥ 23 ካህኑ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ የግምቱን ዋጋ ያሰላለታል፤ በዚያም ቀን ግምቱን እንደ ተቀደሰ ነገር ለጌታ ይሰጣል። 24 በኢዮቤልዩ ዓመት እርሻው የምድሪቱ ባለ ርስት ወደነበረው ወደሸጠው ሰው ይመለሳል። 25 ግምትህም ሁሉ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ይሆናል፤ ሰቅሉ ሀያ አቦሊ ይሆናል። 26 “ዳሩ ግን ለጌታ የሆነውን የእንስሳ በኵራት ማንም ሰው ሊቀድሰው አይችልም፤ በሬ ቢሆን ወይም በግ ለጌታ ነው። 27 የረከሰም እንስሳ ቢሆን እንደ ግምትህ መጠን ይቤዠዋል፤ በእርሱም ዋጋ ላይ አምስት እጅ ይጨምርበታል፤ ባይቤዥም እንደ ግምትህ ይሸጣል። 28 “ነገር ግን ሰው የእርሱ ከሆነው ነገር ሁሉ ለጌታ ለይቶ እርም ያደረገው፥ ሰው ቢሆን ወይም እንስሳ ወይም የርስቱ እርሻ ቢሆን፥ አይሸጥም፥ አይቤዥም፤ እርም የሆነ ነገር ሁሉ ለጌታ እጅግ የተቀደሰ ነው። 29 ከሰዎችም እርም የሆነ ሰው ሁሉ አይዋጅም፤ ፈጽሞ ይገደላል። 30 “የምድሪቱም አሥራት ሁሉ፥ ከምድሪቱ ዘር ወይም ከዛፍ ፍሬ ቢሆን፥ የጌታ ነው፤ ለጌታ የተቀደሰ ነው። 31 ሰውም አሥራቱን ሊቤዥ ቢወድድ፥ በእርሱ ላይ አምስት እጅ ይጨምርበት። 32 ከበሬም ሁሉ ከዐሥር አንድ፥ ከእረኛውም በትር በታች ከሚያልፍ በግና ፍየል ሁሉ ከዐሥር አንድ ለጌታ የተቀደሰ ይሆናል። 33 መልካም ወይም መጥፎ እንደሆነ አይመርምር፥ አይለውጥም፤ ቢለውጠውም እርሱና ልዋጩ ሁለቱም የተቀደሱ ይሆናሉ፤ አይቤዥም።” 34 ጌታ በሲና ተራራ ላይ ለእስራኤል ልጆች ሙሴን ያዘዘው ትእዛዛት እነዚህ ናቸው። |