ዘሌዋውያን 24 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)መብራቱ 1 ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2 “መብራቱ ሁልጊዜ እንዲበራ ለመብራቱ ተወቅጦ የተጠለለ ንጹሕ የወይራ ዘይት እንዲያመጡልህ የእስራኤልን ልጆች እዘዝ። 3 አሮን ከማታ እስከ ማለዳ ድረስ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከምስክሩ መጋረጃ ውጭ በጌታ ፊት ሁልጊዜ ያዘጋጀው፤ ለዘለዓለም ለልጅ ልጃችሁ ሥርዓት ይሁን። 4 በጌታ ፊት በንጹሕ የወርቅ መቅረዝ ላይ መብራቶቹን ሁልጊዜ ያዘጋጃል። የመገናኛው ድንኳን ኅብስት 5 “መልካሙንም ዱቄት ውሰድ፤ በእርሱም ዐሥራ ሁለት ኅብስት ጋግር፤ በአንድ ኅብስት ውስጥ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ ይደረግበት። 6 እነዚህንም ስድስት ስድስቱን በሁለት ተርታ አድርገህ በጌታ ፊት በንጹሕ ወርቅ በተለበጠው ገበታ ላይ አኑራቸው። 7 ለጌታም በእሳት የሚቀርብ ቁርባን ተደርጎ፥ ለእንጀራው የመታሰቢያ ቁርባን እንዲሆን በሁለቱ ተርታ ላይ ንጹሕ የሆነ ዕጣን አድርግ። 8 ስለ እስራኤል ልጆች የዘለዓለም ቃል ኪዳን እንዲሆን በጌታ ፊት ሁልጊዜ በሰንበት ቀን ሁሉ በተርታ ያዘጋጀዋል። 9 እርሱም ለአሮንና ለልጆቹ ይሆናል፤ ለጌታም በእሳት ከሚቀርበው ቁርባን ውስጥ በዘለዓለም ሥርዓት፥ ለእርሱ እጅግ ቅዱስ የሆነ ድርሻ ነውና በተቀደሰ ስፍራ ይብሉት።” መሳደብ እና ቅጣቱ 10 አባቱ ግብፃዊ የነበረ የእስራኤላዊት ልጅ በእስራኤል ልጆች መካከል ወጣ፤ የእስራኤላዊቱ ልጅና አንድ እስራኤላዊ በሰፈር ውስጥ ተጣሉ፤ 11 የእስራኤላዊቱም ልጅ የጌታን ስም ሰደበ፥ አቃለለውም፤ ወደ ሙሴም አመጡት። እናቱም ከዳን ነገድ የደብራይ ልጅ ነበረች፥ ስምዋም ሰሎሚት ነበረ። 12 ጌታም ፍርዱን እስኪያሳውቃቸው ድረስ በእስር ቤት አኖሩት። 13 ከዚያም ጌታ ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 14 “ተሳዳቢውን ከሰፈሩ ውጭ አውጣው፤ የሰሙትም ሁሉ እጃቸውን በራሱ ላይ ይጫኑበት፤ ማኅበሩም ሁሉ ይውገረው። 15 ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ትናገራለህ፦ ማናቸውም ሰው አምላኩን ቢሰድብ ኃጢአቱን ይሸከማል። 16 የጌታንም ስም የሚሰድብ ፈጽሞ ይገደል፤ ማኅበሩም ሁሉ ይውገሩት፤ መጻተኛ ወይም የአገሩ ተወላጅ ቢሆን፥ የጌታን ስም በሰደበ ጊዜ ይገደል። 17 ማናቸውንም ሰው መትቶ የሚገድል ፈጽሞ ይገደል። 18 እንስሳንም መትቶ የሚገድል ሕይወት በሕይወት ፋንታ ካሣውን ይከፍላል። 19 ሰውም ባልንጀራው ላይ ጉዳት ቢያደርስ፥ እርሱ እንዳደረገ እንዲሁ ይደረግበት። 20 በስብራት ፋንታ ስብራት፥ በዐይን ፋንታ ዐይን፥ በጥርስ ፋንታ ጥርስ ይሁን፤ በሰው ላይ ጉዳት ያደረገ ሰው እንዲሁ ይደረግበት። 21 እንስሳንም የሚገድል በካሣ ይተካ፤ ሰውን ግን የሚገድል ይገደል። 22 እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝና ለመጻተኛና ለአገሩ ተወላጅ አንድ ዓይነት ሕግ ይኑራችሁ።” 23 ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ተናገረ፤ ተሳዳቢውንም ከሰፈሩ ውጭ አወጡት፥ በድንጋይም ወገሩት። የእስራኤልም ልጆች ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ። |