Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘሌዋውያን 23 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የጌታ በዓላት

1 ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦

2 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ለእነርሱ ተናገር፦ የተቀደሱ ጉባኤዎች ብላችሁ የምታውጁአቸው በዓላቶቼ፥ የጌታ በዓላት፥ እነዚህ ናቸው።


ሰንበት፥ ፋሲካ፥ የቂጣ በዓል

3 “ስድስት ቀን ሥራ ይሠራል፤ በሰባተኛው ቀን ግን የዕረፍት ሰንበት ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ ይደረግበታል፤ ምንም ሥራ አትሠሩም፤ በምትኖሩበት ሁሉ ለጌታ ሰንበት ነው።

4 “እነዚህ የጌታ በዓላት፥ ለእነርሱ በተወሰነላቸው ጊዜ የምታውጁአቸው፥ የተቀደሱ ጉባኤዎች ናቸው።

5 በመጀመሪያው ወር በዓሥራ አራተኛው ቀን ሲመሽ የጌታ ፋሲካ ነው።

6 በዚህም ወር በዓሥራ አምስተኛው ቀን ለጌታ የቂጣ በዓል ነው፤ ሰባት ቀን እርሾ ያልነካው የቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ።

7 በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ፤ የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት።

8 ሰባት ቀንም ለጌታ በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን አቅርቡ፤ በሰባተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ነው፤ የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት።”


የበኵራት ፍሬ ቁርባን

9 ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦

10 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር ገብታችሁ መከሩን ባጨዳችሁ ጊዜ፥ የእናንተን መከር በኵራት ነዶ ወደ ካህኑ አምጡ፤

11 እርሱም ነዶውን በጌታ ፊት እንዲሠምርላችሁ ይወዝውዘው፤ ካህኑ የሚወዘውዘው በማግስቱ ከሰንበት በኋላ ነው።

12 ነዶውንም በወዘወዛችሁበት ቀን ነውር የሌለበትን የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት ለጌታ አቅርቡ።

13 የእህልም ቁርባን ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርብ ቁርባን ይሁን፤ ለመጠጥም ቁርባን የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ የሆነ የወይን ጠጅ ይቅረብ።

14 የአምላካችሁን ቁርባን እስከምታመጡበት እስከዚህ ቀን ድረስ እንጀራውንም፥ የተጠበሰውንም እሸት፥ ለምለሙንም እሸት አትብሉ። ይህ በምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዓት ነው።


ሰንበት

15 “ለመወዝወዝ ቁርባን ነዶውን ካመጣችሁበት ቀን ከሰንበት በኋላ በማግስቱ ያሉትን ቀኖች ቁጠሩ። እነርሱም ሰባት ሙሉ ሳምንታት ይሁኑ።

16 እስከ ሰባተኛ ሰንበት ማግስት ድረስ ኀምሳ ቀን ቁጠሩ። ከዚያም አዲሱን የእህል ቁርባን ለጌታ አቅርቡ።

17 ከየማደሪያችሁ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ ከሆነ መልካም ዱቄት የተሠራ ሁለት የመወዝወዝ እንጀራ ታመጣላችሁ። ለጌታ ለበኵራት ቁርባን እንዲሆን በእርሾ ተቦክቶ ይጋገራል።

18 ከእንጀራውም ጋር ነውር የሌለባቸውን የአንድ ዓመት ሰባት ተባት ጠቦቶች፥ አንድ ወይፈንም፥ ሁለትም አውራ በጎች ታቀርባላችሁ። ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርብ ቁርባን ሆኖ ከእህል ቁርባናቸውና ከመጠጥ ቁርባናቸው ጋር ለጌታ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናሉ።

19 እንዲሁም አንድ አውራ ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሁለትም የአንድ ዓመት ተባት ጠቦቶች ለአንድነት መሥዋዕት አቅርቡ።

20 ካህኑም ከበኩራቱ እንጀራ ከሁለቱም ጠቦቶች ጋር በጌታ ፊት ለመወዝወዝ ቁርባን ይወዘውዛቸዋል። ለካህኑ ለጌታ የተቀደሱ ይሆናሉ።

21 በዚያም ቀን ታውጃላችሁ፤ የተቀደሰ ጉባኤም ታደርጋላችሁ። የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። በምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዓት ነው።

22 “የምድራችሁንም መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ እስከ እርሻችሁ ድንበር ድረስ ፈጽማችሁ አትሰብስቡ። የመከሩንም ቃርሚያ አትልቀሙ፤ ለድሀውና ለእንግዳው ተዉት። እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ።”


የመለከት ድምፅ መታሰብያ

23 ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦

24 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ በሰባተኛው ወር፥ ወሩ በገባ በመጀመሪያው ቀን ፈጽሞ የምታርፉበት፥ በመለከት ድምፅ መታሰቢያ የምታውጁበት፥ የተቀደሰ ጉባኤ የምታደርጉበት ይሁንላችሁ።

25 የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። ለጌታም በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን አቅርቡ።”


የማስተስረያ ቀን

26 ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦

27 “በዚህ በሰባተኛው ወር አሥረኛው ቀን የማስተስረያ ቀን ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ ራሳችሁን አዋርዱ፥ ለጌታም በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን አቅርቡ።

28 በአምላካችሁም በጌታ ፊት ማስተስረያ እንዲሆንላችሁ የማስተስረያ ቀን ነውና በዚያ ቀን ሥራ ሁሉ አትሥሩ።

29 በዚያም ቀን ራሱን የማያዋርድ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ።

30 በዚያም ቀን ማናቸውንም ሥራ የሚሠራውን ሰው ሁሉ ከሕዝቡ መካከል አጠፋዋለሁ።

31 ሥራ ሁሉ አትሥሩበት፤ በምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዓት ነው።

32 ለእናንተ የዕረፍት ሰንበት ነው፤ ራሳችሁንም አዋርዱ፤ በወሩ በዘጠነኛው ቀን ከማታ ጀምሮ፥ ከማታ እስከ ማታ ድረስ ሰንበታችሁን አድርጉ።”


የዳስ በዓል

33 ጌታ ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦

34 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ በዚህ በሰባተኛው ወር ከዐሥራ አምስተኛው ቀን ጀምሮ ሰባት ቀን ለጌታ የዳስ በዓል ነው።

35 በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁን፤ የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት።

36 ሰባት ቀን ለጌታ በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን አቅርቡ፤ በስምንተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፥ ለጌታም በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን አቅርቡ፤ ዋና ጉባኤ ነው፤ የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት።

37 “የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የእህሉንም ቁርባን፥ መሥዋዕቱንም፥ የመጠጡንም ቁርባን፥ ለጌታም በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን፥ እያንዳንዳቸውን ተገቢ በሆነው ቀናቸው እንድታቀርቡባቸው የተቀደሱ ጉባኤዎች እንዲሆኑ የምታውጁአቸው የጌታ በዓላት እነዚህ ናቸው።

38 እነዚህም ከጌታ ሰንበታት ሌላ፥ ለጌታም ከምትሰጡት ከስጦታችሁ ሌላ፥ ከስእለታችሁም ሁሉ ሌላ፥ በፈቃዳችሁም ከምታቀርቡአቸው ሁሉ ሌላ ናቸው።

39 “በሰባተኛውም ወር በዓሥራ አምስተኛው ቀን የምድሪቱን ምርት በሰበሰባችሁ ጊዜ የጌታን በዓል ሰባት ቀን ጠብቁ፤ በመጀመሪያው ቀን ዕረፍት ይሁን፥ በስምንተኛውም ቀን ዕረፍት ይሁን።

40 በመጀመሪያው ቀን የመልካም ዛፍ ፍሬ፥ የዘንባባ ዝንጣፊ፥ የለመለመውን ዛፍ ቅርንጫፍ፥ የወንዝም አኻያ ዛፍ ውሰዱ፤ በአምላካችሁም በጌታ ፊት ሰባት ቀን ደስ ይበላችሁ።

41 ይህንንም በዓል በየዓመቱ ሰባት ቀን ለጌታ አድርጉ፤ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዓት አድርጋችሁ በሰባተኛው ወር ትጠብቁታላችሁ።

42 ሰባት ቀን በዳሶች ውስጥ ትቀመጣላችሁ፤ በእስራኤል ያሉት የአገሩ ተወላጆች ሁሉ በዳሶች ውስጥ ይቀመጣሉ፤

43 በዚህም ከግብጽ ምድር ባወጣኋቸው ጊዜ የእስራኤልን ልጆች በዳሶች ውስጥ እንዳስቀመጥኋቸው የልጅ ልጆቻችሁ እንዲያውቁ ነው፤ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ።”

44 ሙሴም የጌታን በዓላት ለእስራኤል ልጆች ተናገረ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos