ዘሌዋውያን 21 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የካህናት ቅድስና 1 ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለካህናቱ ለአሮን ልጆች እንዲህ ብለህ ለእነርሱ ተናገር፦ ማንም ሰው ከሕዝቡ መካከል ስለ ሞተው ራሱን አያርክስ፤ 2 ነገር ግን የቅርብ ዘመዱ ስለሆኑት ስለ እናቱ፥ ወይም ስለ አባቱ፥ ወይም ስለ ወንድ ልጁ፥ ወይም ስለ ሴት ልጁ፥ ወይም ስለ ወንድሙ፥ 3 ወይም በእርሱ ዘንድ በቅርብ ስላለችው ያላገባች ድንግል እኅቱ ስለ እርሷ ራሱን ያርክስ። 4 በሕዝቡ መካከል ያሚገኝ አለቃ የረከሰ እዳይሆን ራሱን አያርክስ። 5 ካህናት አናታቸውን አይላጩ፥ ጢማቸውንም አይላጩ፥ ገላቸውንም በመቁረጥ አይተልትሉ። 6 ለአምላካቸው የተቀደሱ ይሆናሉ፥ የአምላካቸውንም ስም አያረክሱም፤ እነርሱም የአምላካቸው እንጀራ የሆነውን፥ ለጌታ በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን ያቀርባሉና የተቀደሱ ይሆናሉ። 7 ካህኑ ለአምላኩ የተቀደሰ ነውና አመንዝራይቱን ሴት ወይም የረከሰችውን አያግባ፤ ወይም በባልዋ የተፈታችውን አያግባ። 8 የአምላክህን እንጀራ ያቀርባልና ስለዚህ ትቀድሰዋለህ፤ እኔም የምቀድሳችሁ ጌታ ቅዱስ ነኝና እርሱ ቅዱስ ይሆንልሃል። 9 የካህንም ልጅ ራስዋን በዝሙት ብታረክስ አባትዋን ታረክሰዋለች፤ በእሳት ትቃጠል። 10 “በራሱም ላይ የቅባዓት ዘይት የፈሰሰበት፥ የክህነትም ልብስ እንዲለብስ የተቀደሰው፥ ከወንድሞቹ ይበልጥ ከፍ ያለው ካህን የራሱን ጠጉር አያጐስቁል ልብሱንም አይቅደድ። 11 በድንም ወደ አለበት ስፍራ ሁሉ አይሂድ፥ ስለ አባቱም ወይም ስለ እናቱ አይርከስ። 12 የሚቀድስውም የአምላኩ የቅባዓት ዘይት በእርሱ ላይ ነውና ከመቅደስ አይውጣ፥ የአምላኩንም መቅደስ አያርክስ፤ እኔ ጌታ ነኝ። 13 እርሱም ድንግል የሆነችውን ሴት ያግባ። 14 ባልዋ የሞተባትን፥ ወይም የተፈታችውን፥ ወይም የረከሰችውን፥ ወይም አመንዝራይቱን አያግባ፤ ነገር ግን ከሕዝቡም መካከል ከወገኑ ድንግሊቱን ያግባ። 15 ስለዚህ በሕዝቡ መካከል ዘሩን አያርክስ፤ እኔ የምቀድሰው ጌታ ነኝና።” 16 ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 17 “ለአሮን እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ከዘርህ በትውልዳቸው ነውር ያለበት ሰው ሁሉ የአምላኩን እንጀራ ለማቅረብ አይቅረብ። 18 ዓይነ ስውር፥ ወይም የሚያነክስ፥ ወይም የፊቱ ቅርጽ የተበላሸ፥ ወይም ትርፍ አካል ያለው፥ 19 ወይም እግሩ የተሰበረ፥ ወይም እጁ የተሰበረ፥ 20 ወይም ከወገቡ የጐበጠ፥ ወይም ድንክ፥ ወይም የማየት ችግር ያለበት፥ ወይም የእከክ ደዌ ያለበት፥ ወይም ቋቁቻ የወጣበት፥ ወይም የብልቱ ፍሬ የፈረጠ፥ ነውረኛ ሁሉ አይቅረብ። 21 ከካህኑ ከአሮን ዘር ነውር ያለበት ማናቸውም ሰው ለጌታ በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን ለማቅረብ አይቅረብ፤ ነውረኛ ነውና የአምላኩን እንጀራ ለማቅረብ አይቅረብ። 22 እጅግ ቅዱስ የሆነውን እና የተቀደሰውን የአምላኩን እንጀራ ይብላ፤ 23 ነገር ግን ነውረኛ ነውና መቅደሶቼን እንዳያረክስ ወደ መጋረጃው አይግባ፥ ወደ መሠዊያውም አይቅረብ፤ የምቀድሳቸው እኔ ጌታ ነኝና።” 24 ሙሴም ይህን ለአሮን፥ ለልጆቹም፥ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ ተናገረ። |