Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘሌዋውያን 17 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ለመሥዋዕት እንሶችን ማረድ

1 ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦

2 “ለአሮንና ለልጆቹ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ ተናገር እንዲህም በላቸው፦ ጌታ ያዘዘው ቃል ይህ ነው።

3 ከእስራኤል ቤት ማናችውም ሰው በሬ ወይም በግ ወይም ፍየል በሰፈሩ ውስጥ ቢያርድ፥ ወይም ከሰፈሩ ውጭ ቢያርደው፥

4 በጌታ ማደሪያ ፊት ለፊት ለጌታ እንደ ቁርባን አድርጎ ለማቅረብ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው፥ ደሙ በዚያ ሰው ላይ ይቈጠርበታል፤ ደም አፍስሶአል፤ ያም ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጥፋ።

5 በዚህም የእስራኤል ልጆች በሜዳ የሚያርዱትን መሥዋዕታቸውን እንዲያመጡ፥ ወደ ጌታ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደ ካህኑ አምጥተዋቸው የአንድነት መሥዋዕት አድርገው ለጌታ እነርሱን እንዲያርዱ ለማድረግ ነው።

6 ካህኑም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባለው በጌታ መሠዊያ ላይ ደሙን ይረጨዋል፥ ስቡንም ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን ያቃጥለዋል።

7 ስለዚህ ተከትለዋቸው ላመነዘሩባቸው ለሰይጣናት ከእንግዲህ ወዲህ መሥዋዕታቸውን አይሠዉም። ይህ ለእነርሱ ለልጅ ልጃቸው ለዘለዓለም ሥርዓት ይሁን።

8 “ለእነርሱም እንዲህ በላቸው፦ ከእስራኤል ቤት በመካከላቸውም ከሚኖር እንግዳ ማናቸውም ሰው የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ሌላ መሥዋዕት ቢያቀርብ፥

9 ለጌታ ሊሠዋው ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ።

10 “ከእስራኤልም ልጆች ወይም በመካከላቸው ከሚኖር እንግዳ ማናቸውም ሰው ደም ቢበላ፥ ደም በሚበላው በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አጠቊርበታለሁ፥ ያንንም ሰው ከሕዝቡ መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ።

11 የሥጋ ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና፤ ደሙም ከሕይወቱ የተነሣ ያስተሰርያልና በመሠዊያው ላይ ለነፍሳችሁ ማስተስረያ እንዲሆን እኔ ለእናንተ ሰጠሁት።

12 ስለዚህ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ አልሁ፦ ከእናንተ ማንም ሰው ደምን አይብላ፥ በመካከላችሁም ከሚኖር እንግዳ ማንም ሰው ደምን አይብላ።

13 እንዲሁም ከእስራኤል ልጆች በመካከላቸውም ከሚኖር እንግዳ ማናቸውም ሰው የሚበላ እንስሳ ወይም ወፍ አድኖ ቢይዝ፥ ደሙን ያፈስሳል በአፈርም ይሸፍነዋል።

14 “ሥጋን የለበሰ ሕያው ፍጥረት ሁሉ ሕይወቱ ደሙ ነውና ስለዚህ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ አልሁ፦ ሥጋን የለበሰ ሕያው ፍጥረት ሁሉ ሕይወቱ ደሙ ነውና የሥጋውን ሁሉ ደም አትብሉ፤ የሚበላውም ሁሉ ተለይቶ ይጥፋ።

15 የሞተውን ወይም አውሬ የገደለውን የሚበላ ሰው ሁሉ፥ የአገሩ ተወላጅ ወይም እንግዳ ቢሆን፥ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል።

16 ነገር ግን ልብሱን ባያጥብ፥ ገላውንም ባይታጠብ ኃጢአቱን ይሸከማል።”

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos