ዘሌዋውያን 12 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ሴቶች ልጅ ከወለዱ በኋላ የሚደረግ የመንጻት ሥርዓት 1 ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2 ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ሴት ፀንሳ ወንድ ልጅም ብትወልድ፥ ሰባት ቀን ያኽል የረከሰች ትሆናለች፤ እንደ ወር አበባዋም ጊዜያት ትረክሳለች። 3 በስምንተኛውም ቀን ልጁ ከሥጋው ሸለፈት ይገረዝ። 4 ከደምዋም እስክትነጻ ሠላሳ ሦስት ቀን ትቀመጥ፤የመንጻትዋ ቀንም እስኪፈጸም ድረስ የተቀደሰን ነገር ሁሉ አትንካ፥ ወደ መቅደስም አትግባ። 5 ነገር ግን ሴት ልጅ ብትወልድ እንደ ወር አበባዋ ጊዜያት ሁለት ሳምንት ያኽል የረከሰች ትሆናለች፤ ከደምዋም እስክትነጻ ድረስ ስልሳ ስድስት ቀን ትቀመጥ። 6 “የመንጻትዋ ወራትም በተፈጸመ ጊዜ፥ ለወንድ ልጅ ወይም ለሴት ልጅ፥ የአንድ ዓመት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ የርግብም ግልገል ወይም ዋኖስ ለኃጢአት መሥዋዕት ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደ ካህኑ ታምጣ። 7 እርሱም በጌታ ፊት ያቀርበዋል ያስተሰርይላታልም፤ ከሚፈስሰውም ደምዋ ትነጻለች። ወንድ ወይም ሴት ለምትወልድ ሴት ሕጉ ይህ ነው። 8 ጠቦት ለማቅረብ በቂ ገንዘብ ባታገኝ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ትውሰድ፥ አንዱን ለሚቃጠል መሥዋዕት ሌላውንም ለኃጢአት መሥዋዕት ታድርገው፤ ካህኑም ያስተሰርይላታል፥ እርሷም ትነጻለች።” |