Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘሌዋውያን 10 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ናዳብና አብዩድ

1 የአሮንም ልጆች ናዳብና አብዩድ እያንዳንዳቸው ጥናቸውን ወስደው እሳት አደረጉበት፥ በላዩም ዕጣን አኖሩበት፥ በጌታም ፊት እርሱ ያላዘዛቸውን ያልተፈቀደውን እሳት አቀረቡ።

2 እሳትም ከጌታ ዘንድ ወጥቶ እነርሱን በላቸው፥ በጌታም ፊት ሞቱ።

3 ሙሴም አሮንን፦ “ጌታ፦ ‘ወደ እኔ በሚቀርቡ እቀደሳለሁ፥ በሕዝቡም ሁሉ ፊት እከብራለሁ’ ብሎ የተናገረው ይህ ነው” አለው፤ አሮንም ዝም አለ።

4 ሙሴም የአሮንን አጎት የዑዝኤልን ልጆች ሚሳኤልንና ኤልጻፋንን ጠርቶ፦ “ቅረቡ፥ ወንድሞቻችሁንም ከመቅደሱ ፊት አንሥታችሁ ከሰፈሩ ውጭ ውሰዱአቸው” አላቸው።

5 ሙሴም እንደ ተናገረው ቀርበው ቀሚሳቸውን ይዘው አነሡአቸው፥ ከሰፈሩም ውጭ ወሰዱአቸው።

6 ሙሴም አሮንን፥ ልጆቹንም አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ አላቸው፦ “እንዳትሞቱ በማኅበሩም ሁሉ ላይ እርሱ እንዳይቈጣ የራሳችሁን ጠጉር አታጐስቁሉ፥ ልብሳችሁንም አትቅደዱ፤ ጌታ እሳትን ልኮ ስላደረገው ማቃጠል ግን ወንድሞቻችሁ የእስራኤል ቤት ሁሉ ያልቅሱ።

7 እንዲሁም የጌታ የቅባት ዘይት በላያችሁ ነውና እንዳትሞቱ ከመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አትውጡ።” እንደ ሙሴ ቃልም አደረጉ።

8 ጌታም አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦

9 “እንዳትሞቱ ወደ መገናኛው ድንኳን ስትገቡ አንተና ከአንተ ጋር ያሉት ልጆችህ የወይን ጠጅና የሚያሰክርን መጠጥ አትጠጡ፤ ይህም ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዓት ነው፤

10 በዚህም በተቀደሰውና ባልተቀደሰው፥ በርኩሱና በንጹሑም መካከል እንድትለዩ፥

11 ጌታም በሙሴ አንደበት የነገራቸውን ሥርዓት ሁሉ ለእስራኤል ልጆች እንድታስተምሩ ነው።”

12 ሙሴም አሮንን፥ የተረፉለትንም ልጆቹን አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ አላቸው፦ “እጅግ የተቀደሰ ነውና ለጌታ ከሆነው በእሳት ከሚቀርበው ቁርባን የተረፈውን የእህሉን ቁርባን ውሰዱ፥ እርሾም ያልገባበት ቂጣ አድርጋችሁ በመሠዊያው አጠገብ ብሉት፤

13 ለጌታም ከሆነው በእሳት ከሚቀርበው ቁርባን ለአንተም ለልጆችህም የተሰጠ ድርሻ ነውና በቅዱስ ስፍራ ትበሉታላችሁ፤ ይህንንም እንዲህ ታዝዣለሁና።

14 ነገር ግን የሚወዘወዘውን ፍርምባ፥ የሚነሣውንም ወርች አንተ፥ ከአንተ ጋር ያሉት ወንዶች ልጆችህና ሴቶች ልጆችህም በንጹሕ ስፍራ ትበላላችሁ፤ እነዚህ ከእስራኤል ልጆች ከሰላም መሥዋዕት ለአንተና ለልጆችህ ድርሻ እንዲሆኑ የተሰጡ ናቸውና።

15 የሚነሣውን ወርች የሚወዘወዘውንም ፍርምባ፥ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን ከሆነው ስብ ጋር ለመወዝወዝ ቁርባን በጌታ ፊት እንዲወዘወዝ ያመጣሉ፤ ጌታ እንዳዘዘ ለአንተ ከአንተ ጋርም ላሉት ለልጆችህ የዘለዓለም ድርሻ ይሆናል።”

16 ሙሴም የኃጢአት መሥዋዕት ስለ ሆነው ፍየል አጥብቆ ጠየቀ፥ እነሆም ተቃጥሎ ነበር፤ ሙሴም የተረፉትን የአሮንን ልጆች አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ ብሎ ተቆጣ፦

17 “እጅግ የተቀደሰ ነውና፥ የሕዝቡንም ኃጢአት እንድትሸከሙ፥ በጌታም ፊት እንድታስተሰርዩላቸው ለእናንተ ሰጥቶአልና ለምን የኃጢአት መሥዋዕት የሆነውን በቅዱሱ ስፍራ አልበላችሁም?

18 እነሆ፥ ደሙን ወደ መቅደሱ ውስጥ አላገባችሁትም፤ እኔ እንደ ታዘዝሁ በቅዱሱ ስፍራ ውስጥ ትበሉት ይገባችሁ ነበር።”

19 አሮንም ሙሴን፦ “እነሆ፥ ዛሬ የኃጢአታቸውን መሥዋዕትና የሚቃጠለውን መሥዋዕታቸውን በጌታ ፊት አቀረቡ፤ ሆኖም ይህ ሁሉ ነገር በእኔ ላይ ደረሰብኝ፤ ዛሬስ የኃጢአት መሥዋዕት ብበላ ኖሮ በጌታ ፊት መልካም ይሆን ነበርን?” አለው።

20 ሙሴም ሰማ በፊቱም መልካም ሆነ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos