Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa

መጽሐፈ ዮዲት 4 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የአይሁዳውያን ዝግጅት

1 በይሁዳ አገር የሚኖሩ እስራኤላውያን የአሦር ንጉሥ የናቡከደነፆር ዋና የጦር አዛዥ ሆሎፎርኒስ በአሕዛብ ላይ የደረገውን ሁሉ፥ መቅደሳቸውን እንዳፈረሰና እነርሱንም ለጥፋት እንደሰጣቸው በሰሙ ጊዜ፥

2 እጅግ እጅግ ፊቱን ፈሩ፤ ስለ ኢየሩሳሌምና ስለ ጌታ አምላካቸው ቤተ መቅደስ ተጨነቁ።

3 ምክንያቱም ከምርኮ የመለሱት በቅርቡ ስለሆነና የይሁዳም ሕዝብ የተሰባሰቡት፥ ዕቃዎቹን መሠዊያውንና መቅደሱንም ከረከሰ በኋላ ያነጹት በቅርቡ ስለ ነበረ ነው።

4 ስለዚህም ወደ ሰማርያ፥ ወደ ኮና፥ ወደ ቤትሖሮን፥ ወደ ቤልሜይን፥ ወደ ኢያሪኮ፥ ወደ ቾባ፥ ወደ አይሶራና ወደ ሳሌም ሸለቆ ሁሉ ላኩ።

5 የተራሮችን ሁሉ ጫፍ ያዙ፥ በተራሮች ላይ ያሉትንም መንደሮች ቅጥር ሰሩ፥ አዝመራቸው ቀደም ብሎ ተሰብስቦ ስለ ነበር ለጦርነት የሚሆን ስንቅን አዘጋጁ።

6 በዚያን ዘመን ሊቀ ካህን የነበረው ኢዮአቄም በቤቱሊያና በዶታይም ሜዳ አጠገብ በኤስድራሎን ፊት ለፊት በምትገኘው በቤቶሜስታይም ለሚኖሩ ሰዎች ጻፈ፤

7 ወደ ተራራው የሚወስደውን መተላለፊያ እንዲይዙ ነገራቸው፤ ምክንያቱም ወደ ይሁዳ መግቢያ በዚያ ስለሆነ፥ መተላለፊያውም በጣም ጠባብ ስለሆነና በአንድ ጊዜ ሁለት ሰው ብቻ የሚያስተላልፍ ስለሆነ የሚገቡትን ሰዎች ለመከላከል ቀላል ስለሆነ ነው።

8 የእስራኤልም ልጆች ሊቀ ካህኑ ኢዮአቄምና በኢየሩሳሌም የሚቀመጡ የእስራኤል ሽማግሌዎች ጉባኤ እንደ አዘዙአቸው አደረጉ።


የሕዝብ ጸሎት

9 የእስራኤልም ሰዎች ወደ እግዚአብሔር በብርቱ እጅግ ጮሁ፥ በብርቱም ነፍሳቸውን ዝቅ አደረጉ።

10 እነርሱና ሚስቶቻቸው፥ ልጆቻቸው፥ ከብቶቻቸው፥ በዚያ የሚኖሩ እንግዶች ሁሉ፥ ቅጥረኞችና በብር የተገዙ ሁሉ በወገባቸውን በማቅ ታጠቁ።

11 በኢየሩሳሌም የሚኖሩ የእስራኤል ሰዎች ሁሉ፥ ሴቶችና ሕፃናትም በቤተ መቅደሱ ፊት ተደፉ፤ በራሶቻቸውም ላይ አመድ ነሰነሱ፥ በጌታ ፊት ማቃቸውን ዘረጉ።

12 መሠዊያውንም ማቅ አለበሱ፤ ልጆቻቸውና ሚስቶቻቸው እንዳይዘረፉ፤ የወረሱአቸው ከተሞቻቸው እንዳይደመሰሱ፤ የተቀደሰው ቦታ በአረመኔዎች እንዳይረክስና እንዳይዋረድ ወደ እግዚአብሔር አጥብቀው ባንድነት አለቀሱ።

13 ጌታ ድምጻቸውን ሰማ፥ መከራቸውንም አየ፤ ሕዝቡ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ሁሉን በሚችል በጌታ መቅደስ ፊት ለብዙ ቀኖች ጾሙ።

14 ሊቀ ካህኑ ኢዮአቄምና በጌታ ፊት የሚቆሙት ካህናት ሁሉና ጌታን የሚያገለግሉ ሁሉ በወገባቸው ማቅ ታጥቀው የሕዝቡን የሚቃጠል መሥዋዕት፥ የዘወትር መሥዋዕት፥ ስእለትና በፈቃድ የሚሰጠውንም ሥጦታ አቀረቡ።

15 ጥምጣማቸው ላይ አመድ ነስንሰው፥ መላውን የእስራኤል ቤት በመልካም እንዲጎበኝ በሙሉ ኃይላቸው ወደ ጌታ ጮኹ።

Síguenos en:



Anuncios