Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ዮዲት 16 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ዮዲት እንዲህ አለች፤ “ለአምላኬ በከበሮ መዝሙርን ጀምሩ፥ ለጌታ በጸናጽን ዘምሩለት፤ አዲስን መዝሙር ተቀኙለት፤ አክብሩት፥ ስሙንም ጥሩ። 2 ጌታ ሰልፍን የሚሰብር አምላክ ነውና፤ የጦር ሰፈሩን በሕዝቡ መካከል አደረገ፤ ከሚያሳድዱኝም ሰዎች እጅ አዳነኝ። 3 አሦር ከሰሜን ተራራዎች ወጣ፤ ከብዙ ሺህ ሠራዊቱም ጋር ወጣ። ብዛታቸው ፈሳሹን ዘጋ፤ ፈረሶቻቸው ኮረብታዎችን ሸፈነ። 4 ድንበሬን ሊያቃጥል፥ ጐልማሶቼን በሰይፍ ሊገድል፥ ጨቅላ ልጆቼን በምድር ላይ ሊጥል፥ ሕጻናቴንና ደናግላኔንም በምርኮ ሊወስድ ደፍሮ ተናግሮ ነበር። 5 ነገር ግን ሁሉን የሚችል ጌታ ሴት እጅ አስቆማቸው። 6 ኃያላቸው በጐልማሶች እጅ አልወደቀም፤ የቲታንስ ልጆችም አልመቱትም፤ ረጃጅም ግዙፎችም አላጠቁትም፤ የሜራሪ ልጅ ዮዲት ግን በውበቷ ሽባ አደረገችው። 7 በእስራኤል የተጨቆኑትን ለማንሳት የመበለትነቷን ልብስ አወለቀች፥ ፊትዋንም ቅባት ተቀባች። 8 ጠጉርዋን ተሠርታ ሻሽ አሰረች፤ ለመሳብም የተልባ እግር ልብስ ለበሰች። 9 ጫማዋ ዐይኖቹን ያዘ፤ ውበቷ ነፍሱን ማረከ፤ ሰይፉም በአንገቱ አለፈ። 10 የፋርስ ሰዎች በድፍረቷ ደነገጡ፤ የሜዶን ሰዎች በጽናቷ ፈሩ። 11 በዚያን ጊዜ የእኔ ትሑታን ጮኹ፥ የእኔ ደካሞች በጣም ጮኹ፤ እነዚያም በድንጋጤ ተዋጡ፤ የእኔ ሰዎች ድምፃቸውን ከፍ አደረጉ፥ እነዚያም ደንግጠው ሸሹ። 12 የሴቶች ልጆች ወጉአቸው፤ እንደ ከሐዲ ልጆችም አቆሰሏቸው፤ በጌታዬ ሰልፍም ጠፉ። 13 ለአምላኬ አዲስ የምስጋናን መዝሙር እዘምራለሁ፤ ጌታ ሆይ አንተ ትልቅና ክቡር፥ በብርታትህ የምትደነቅና የማትሸንፍ ነህ። 14 ፍጥረቶችህ ሁሉ ያገልግሉህ፤ አንተ ተናገርህ እነርሱም ተፈጠሩ፤ መንፈስህን ላክህ፥ እነርሱም ታነጹ፤ ድምጽህን መቃወም የሚችል ማንም የለም። 15 ተራሮች ከውኆች ጋር ከመሠረታቸው ይንዋወጣሉና፤ ዓለቶችም በአንተ ፊት እንደ ሰም ይቀልጣሉ፤ ለሚፈሩህ ግን ምሕረትን ታደርጋለህ። 16 ጥሩ መዓዛ ያለው መሥዋዕት ሁሉ ለአንተ ትንሽ ነው፥ የሚቃጠለው መሥዋዕት ሁሉ ስብ ለአንተ በጣም ጥቂት ነው፤ ጌታን የሚፈራ ግን ሁልጊዜ ታላቅ ነው። 17 በወገኖቼ ላይ የሚነሡ አሕዛብ ወዮላቸው፤ ሁሉን የሚችል ጌታ በፍርድ ቀን ይበቀላቸዋል፤ በሥጋቸውም ላይ እሳትንና ትልን ያመጣባቸዋል፤ በስቃይም ለዘለዓለም ያለቅሳሉ።” 18 ወደ ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤ ሕዝቡም በነጹ ጊዜ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችንና በፈቃዳቸው የሚያቀርቡት መባዎችንና ስጦታዎችን አቀረቡ። 19 ዮዲትም ሕዝቡ የሰጣትን የሆሎፎርኒስን ንብረቶች ሁሉ ለእግዚአብሔር አቀረበች። ከመኝታ ቤቱ ያመጣችውን መጋረጃ እንደ ስእለት አድርጋ ለጌታ ሰጠች። 20 ሕዝቡ ሁሉ በኢየሩሳሌም በቤተ መቅደስ ፊት ሦስት ወር ሙሉ ደስታ አደረጉ፤ ዮዲትም ከእነርሱ ጋር ተቀመጠች። የዮዲት እርጅናና እረፍት 21 ከዚህ ጊዜ በኋላ እያንዳንዱ ወደ ርስቱ ተመለሰ። ዮዲትም ወደ ቤቱሊያ ተመለሰች፥ በንብረቷም ላይ ተቀመጠች በዘመኗ ሁሉ በምድር ሁሉ ላይ የተከበረች ሆነች። 22 ብዙ ሰዎች ሊያገቧት ፈልገው ነበረ፥ ነገር ግን ባሏ ምናሴ ከሞተበትና ወደ ሕዝቡ ከተሰበሰበበት ጊዜ ጀምሮ በሕይወት ዘመኗ ሁሉ ራሷን ለማንም አልሰጠችም። 23 እጅግ በጣም ከበረች፥ መቶ አምስት ዓመት እስኪሆናት ድረስ በባሏ ቤት አረጀች፤ አገልጋይዋን ነጻ ለቀቀቻት። በቤቱሊያ ዓረፈች፥ በባሏ በምናሴ ዋሻ ተቀበረች፤ 24 የእስራኤል ቤት ለሰባት ቀን አለቀሰላት። ከመሞቷ በፊት ያላትን ሁሉ ለባሏ ለምናሴ የቅርብ ዘመዶችና ለቅርብ ዘመዶቿ አካፈለች። 25 ዮዲት በነበረችበት ጊዜና ከሞተችም በኋላ ለብዙ ጊዜ የእስራኤልን ልጆች የሚያስፈራ ማንም አልነበረም። |