Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ዮዲት 11 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ዮዲት ከሆሎፎርኒስ ጋር ያደረገችው የመጀመሪያው ትውውቅ 1 ሆሎፎርኒስም እንዲህ አላት፦ “አንቺ ሴት አይዞሽ፥ ልብሽም አይፍራ፥ የምድር ሁሉ ገዢ የሆነውን ንጉሥ ናቡከደነፆርን ለማገልገል የቆረጠን ሰው ጉዳት አድርሼ አላውቅምና። 2 አሁንም ቢሆን በተራራማው አገር የሚኖሩ ወገኖችሽ ባይንቁኝ ኖሮ በእርሱ ላይ ጦሬን ባላነሣሁም ነበር፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በራሳቸው ላይ አመጡ። 3 እስቲ አሁን ንገሪኝ፥ ከእነርሱ ሸሽተሽ ወደ እኛ ለምን መጣሽ? ሆኖም ወደ መዳን መጥተሻል፥ አይዞሽ፥ ዛሬና ለሁልጊዜም ትኖሪአለሽ። 4 ማንም ጉዳት አያደርስብሽም፤ እንዲያውም ለጌታዬ ለንጉሥ ናቡከደነፆር ባርያዎች እንደሚደረግላቸው ለአንቺም መልካም ይደረግልሻል።” 5 ዩዲትም እንዲህ አለችው፦ “የባርያህን ቃል ተቀበል፤ ባርያህ በፊትህ ትናገር፤ በዚች ምሽት ለጌታዬ አንድም የሐሰት ነገርን አልናገርም። 6 የባርያህን ቃል ከተከተልህ፥ እግዚአብሔር በአንተ ሥራህን ሁሉ ከፍፃሜ ያደርሰዋል፤ ጌታዬም ዕቅዱን ከማሳካት አይወድቅም። 7 የምድር ሁሉ ንጉሥ፥ ሕያው ፍጥረትን ሁሉ እንድታቀና በላከህ ናቡከደነፆርና በኃይሉ እምላለሁ፤ በአንተ በኩል ሰዎች ብቻ የሚገዙለት አይደሉም፤ ነገር ግን የዱር አራዊትና ከብቶች፥ በሰማይ የሚበሩ ወፎችም በኃይልህ ከናቡከደነፆርና ከቤቱ በታች ይገዙለታል እንጂ።” 8 “ጥበብህንና ክህሎትህን ሰምተናል፥ በመንግሥቱ ሁሉ አንተ ብቻ መልካም፥ በአስተዋይነትህ ኃያል፥ በሰልፍህም ሁሉ የተደነቅህ እንደሆንህ በምድሪቱ ሁሉ ተሰምቷል። 9 አኪዮርም በጉባኤህ ላይ ያደረገውን ንግግር ሰምተናል፤ ሕይወቱን ላተረፉት የቤቱሊያ ሰዎችም ለአንተ የነገረህን ሁሉ ነግሮአቸዋል። 10 ስለዚህ ጌታዬ ሆይ እርሱ የተናረገውን አቅልለህ አትመለከተው። ነገር ግን እውነት ስለሆነ በልብህ አኑረው፤ ሕዝባችን አይቀጣም፤ እግዚአብሔርን ካልበደሉ በስተቀር ሰይፍም ሊያጠፋቸው አይችልም። 11 አሁን ግን ጌታዬ የተጣለና የማይረባ እንዳይሆን ሞት በፊታቸው ይወድቅባቸዋል፤ ኃጢአት በእነርሱ ላይ ይዟቸዋል፥ የአምላካቸውን ቁጣ አስነስተዋል፥ ይህም ከመንገዳቸው ስለወጡ ነው። 12 የምግባቸው ስላለቀና ውኃው ስላጠራቸው፥ ከብቶቻቸውን ሁሉና እግዚአብሔር በሕጉ እንዳይበሉ የከለከላቸውን ሁሉ ሊበሉ ወስነዋል። 13 በኢየሩሳሌም በአምላካችን ፊት ለሚያገለግሉ ካህናት የተለየውን፥ ከሕዝቡ አንድም ሰው በእጁ ሊነካቸው የማይፈቀድለትን የእህሉን በኵራትና የወይኑንና የዘይቱን አስራት ሊበሉ ወስነዋል። 14 ከሽማግሌዎች ጉባኤ ፈቃድ እንዲያመጡላቸው ወደ ኢየሩሳሌም ላኩ፤ በዚያ የሚኖሩ ሰዎች እንዲህ አድርገዋልና። 15 መልሱ ሲደርሳቸውና የወሰኑትንም በፈጸሙ ሰዓት፥ በዚያች ቀን እንዲጠፉ በእጅህ ይሰጣሉ። 16 ስለዚህ እኔ ባርያህ ይህን በአወቅሁ ጊዜ ከፊታቸው ኰበለልሁ፤ በምድር ሁሉ ያለ፥ የሰማውን ሁሉ ስለ እነርሱ በሰማ ጊዜ የሚደነቅበት ሥራ ከአንተ ጋር እንድሠራ እግዚአብሔር ላከኝ። 17 ባርያህ የሰማይን አምላክ ቀንና ሌሊት የምታገለግል፥ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ናት፤ ስለዚህ ጌታዬ ከአንተ ጋር እቆያለሁ፤ ነገር ግን ባርያህ በየምሽቱ ወደ እግዚአብሔር ለመጸለይ ወደ ሸለቆው ትወርዳለች፤ እርሱም ኃጢአትን በሰሩ ጊዜ ይነግረኛል። 18 በዚያን ጊዜ መጥቼ እነግርሃለሁ፥ አንተም ከሠራዊትህ ሁሉ ጋር ትወጣለህ፥ ከእነርሱም የሚቋቋምህ አይኖርም። 19 ወደ ኢየሩሳሌም እስክትደርስ ድረስ በይሁዳ መካከል እመራሃለሁ፤ በዚያም ዙፋንህን እዘረጋልሃለሁ፤ እረኛ እንደሌላቸው በጐች ትመራቸዋለህ፥ ውሻም ምላሱን በአንተ ላይ አያንቀሳቅስም፤ ይህ አስቀድሞ ተነግሮኛል፤ ይህም ተብራራልኝ፥ ለአንተም እንድነግርህ ተላክሁ።” 20 ንግግርዋ ሆሎፎርኒስንና አገልጋዮቹን ደስ አሰኛቸው። በጥበቧ ተደነቁ፥ እንዲህም አሉ፦ 21 “ከምድር ጫፍ እስከ ጫፍ በፊት ውበትና በአነጋገር ጥበብ እንደዚህች ሴት ያለ የለም።” 22 ሆሎፎርኒስም እንዲህ አለ፦ “ኃይል በእጃችን፥ ጥፋት ግን ጌታዬን በካዱት ላይ እንዲሆን ከሕዝቡ ቀድሞ የላከሽ እግዚአብሔር መልካም አደረገ። 23 አሁንም አንቺ ውብ እና አንደበተ ርቱዕ ነሽ፤ እንደተናገርሽው ከአደረግሽ አምላክሽ አምላኬ ይሆናል፥ አንቺም በንጉሥ ናቡከደነፆር ቤት ትኖሪያለሽ፤ ስምሽም በምድር ሁሉ ይታወቃል።” |