መሳፍንት 8 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የኤፍሬም ሰዎች በቀል 1 በዚያን ጊዜ የኤፍሬም ሰዎች፥ “ምድያማውያንን ለመውጋት ስትሄድ ለምን አልጠራኸንም? ለምንስ እንዲህ ያለ ነገር አደረግህ?” በማለት ጌዴዎንን እጅግ ነቀፉት። 2 ጌዴዎን ግን፥ “እናንተ ካደረጋችሁት ጋር ሲነጻጸር የእኔ ከምን ይቈጠራል? የኤፍሬም የወይን ቃርሚያ ተጠቃሎ ከገባው ከአቢዔዝር የወይን መከር አይበልጥምን? 3 እግዚአብሔር የምድያማውያንን መሪዎች ሔሬብንና ዜብን በእጃችሁ አሳልፎ ሰጣችሁ፤ታዲያ እናንተ ከፈጸማችሁት ጋር የሚወዳደር ምን ማድረግ እችል ነበር?” ይህን ሲሰሙ ቊጣቸው በረደ። 4 ጌዴዎንና ሦስት መቶዎቹ ሰዎች ዮርዳኖስን ተሻገሩ፤ ምንም እንኳ ድካም ቢሰማቸውም ጠላቶቻቸውን ያሳድዱ ነበር። 5 የሱኮትንም ሰዎች፥ “የምድያምን ነገሥታት ዜባሕንና ጻልሙናን በማሳደድ ላይ ስለ ሆንኩ የተከተሉኝም ሰዎች ስለ ደከሙ ብኝ እባካችሁ የሚበሉትን እንጀራ ስጧቸው” አላቸው። 6 የሱኮት ሹማምንት ግን፥ “ለተከተሉህ ሰዎች እንጀራ እንሰጥ ዘንድ ዜባሕና ጻልሙና በእጅህ ገብተዋልን?” አሉት። 7 ጌዴዎንም መልሶ፥ “እንግዲህ ደህና፤ ጌታ ዜባሕንና ጻልሙናን በእጄ አሳልፎ በሚሰጥበት ጊዜ በምድረ በዳ እሾኽና አሜከላ ሥጋችሁን እገርፋለሁ” አላቸው። 8 ከዚያም ወደ ጵኒኤል ሰዎች ሄዶ ያንኑ ጥያቄ አቀረበላቸው፤ የእነርሱም መልስ የሱኮት ሰዎች ከሰጡት መልስ ጋር ተመሳሳይ ነበር። 9 እርሱም የጵኒኤልን ሰዎች፥ “በድል አድራጊነት በሰላም ስመለስ ከተማችሁን የምትጠብቁበትን ይህን ግንብ አፈርሰዋለሁ” አላቸው። 10 በዚህ ጊዜ ዜባሕና ጻልሙና ዐሥራ አምስት ሺህ ከሆነ ሠራዊታቸው ጋር ቀርቀር በተባለ ስፍራ ነበሩ፤ ይህም ከምሥራቅ ሕዝቦች ከተውጣጣውና በጦር ሜዳ ከወደቀው መቶ ሃያ ሺህ ሰይፍ ታጣቂ ሠራዊት የተረፈው ነበር። 11 ከዚያም ጌዴዎን ተነሣ፤ ከኖባህና ከዮግብሃ በስተ ምሥራቅ የሚኖሩ ዘላኖች የሚሄዱበትን መንገድ ተከትሎ በጠላት ሠራዊት ላይ በድንገት አደጋ ጣለ። 12 ሁለቱ የምድያም ነገሥታት ዛብሄልና ጻልሙና ሸሹ፤ ጌዴዎን ግን አሳዶ ያዛቸው፤ መላ ሠራዊታቸውንም እጅግ በታተነው። 13 ከዚህ በኋላ የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን በሐሬስ ዳገት በኩል ከጦርነቱ ተመለሰ፤ 14 እርሱም የሱኮት ሰው የሆነ አንድ ወጣት ማረከ፤ መረመረውም፤ ወጣቱም የሰባ ሰባት የሱኮት ሹማምንትና የከተማይቱንም አለቆች ስም ጻፈለት። 15 ከዚያም ጌዴዎን ወደ ሱኮት ሰዎች መጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ ‘ለደከሙት ሰዎችህ እንጀራ እንሰጥ ዘንድ ዜባሕና ጻልሙና በእጅህ ገብተዋልን’ በማለት ያላገጣችሁብኝ ዜባሕና ጻልሙና እነዚሁላችሁ።” 16 ጌዴዎን የከተማይቱን አለቆች ወሰደ፤ በምድረ በዳ እሾኽና አሜኬላ በመቅጣት የሱኮትን ሰዎች ትምህርት ሰጣቸው። 17 እንዲሁም በጵኒኤል ያለውን የከተማ መጠበቂያ ግንብ አፈረሰ፤ የከተማይቱንም ሰዎች ገደለ። 18 ዜባሕና ጻልሙናንም፥ “በታቦር ላይ የገደላችኋቸው ሰዎች እንዴት ያሉ ነበሩ?” በማለት ጠየቃቸው። እነርሱም፥ “ሁሉም እንዲህ እንዳንተ ያሉ የንጉሥ ልጆች የሚመስሉ ናቸው” አሉት። 19 ጌዴዎንም፥ “እነርሱ የእናቴ ልጆች ወንድሞቼ ናቸው፤ ባትገድሏቸው ኖሮ እኔም እንደማልገድላችሁ በሕያው ጌታ ስም አረጋግጥላችሁ ነበር” ብሎ መለሰላቸው። 20 ከዚያም የበኲር ልጁ ወደ ሆነው ዮቴር ዘወር ብሎ፥ “ግደላቸው” አለው፤ ዮቴር ግን ትንሽ ልጅ ነበርና ስለ ፈራ ሰይፉን አልመዘዘም። 21 ዜባሕና ጻልሙናም፥ “የሰው ጉልበቱ እንደ ሰውነቱ መጠን ነውና፥ አንተው ራስህ ግደለን አሉት፤” ጌዴዎንም ተነሥቶ ገደላቸው፤ በግመሎቻቸው አንገት ላይ የነበሩትንም ጌጦች ወሰደ። 22 እስራኤላውያንም ጌዴዎንን፥ “ከምድያማውያን እጅ ታድገኸናልና አንተ፥ ልጅህና የልጅ ልጅህ ግዙን” አሉት። 23 ጌዴዎን ግን መልሶ፥ “እኔም ሆንሁ ልጄ አንገዛችሁም፤ የሚገዛችሁ ጌታ ነው” አላቸው። 24 እርሱም “አንድ የምጠይቃችሁ ነገር አለኝ፤ ይኸውም እያንዳንዳችሁ ከምርኮ ካገኛችሁት ውስጥ የጆሮ ጉትቻችሁን እንድትሰጡኝ ነው” አላቸው፤ የወርቅ ጉትቻ ማድረግ የእስማኤላውያን ባህል ነበርና። 25 እነርሱም መልሰው፤ “ደስ እያለን እንሰጥሃለን” አሉት፤ ወዲያው ልብስ አነጠፉ፤ በላዩም ላይ እያንዳንዳቸው ከማረኩት ውስጥ የጆሮ ጉትቻ ጣል ጣል አደረጉለት። 26 ሌሎቹን ጌጣ ጌጦች ይኸውም የአንገት ሐብሉን ከነእንጥልጥሉ፥ የምድያም ነገሥታት ይለብሱት የነበረውን ሐምራዊ ልብስ ወይም በግመሎቻቸው አንገት ላይ ያሉትን ጌጦች ሳይጨምር ጌዴዎን በጠየቃቸው መሠረት የሰጡት የወርቅ ጉትቻ ክብደት ሺህ ሰባት መቶ ሰቅል ያህል መዘነ። 27 ጌዴዎን በወርቁ ኤፉድ ሠራ፤ በተወለደበትም ከተማ በዖፍራ አኖረው። እስራኤልም በሙሉ ኤፉዱን በማምለክ ስላመነዘሩ፥ ኤፉዱ ለጌዴዎንና ለቤተ ሰቡ ወጥመድ ሆነ። የጌዴዎን መሞት 28 ስለዚህ ምድያማውያን በእስራኤላውያን ተሸነፉ፤ ዳግመኛም ራሳቸውን ከፍ ከፍ አላደረጉም። ጌዴዎን በሕይወት እስካለ ጊዜ ድረስ ምድሪቱ አርባ ዓመት ሰላም አገኘች። 29 የኢዮአስ ልጅ ይሩባኣል ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ በዚያም ተቀመጠ፤ 30 ብዙ ሚስቶች ስላገባ ሰባ ልጆች ነበሩት፤ 31 በሴኬም የምትኖረው ቁባቱም እንደዚሁ ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ስሙንም አቤሜሌክ አለው። 32 የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን ዕድሜ ጠግቦ ሞተ፤ በአቢዔዝራውያን ምድር ባለችው በዖፍራ፥ በአባቱ በኢዮአስ መቃብር ተቀበረ። 33 ጌዴዎን ሞቶ ብዙም ሳይቈይ እስራኤላውያን የበኣልን አማልክት በማምለክ አመነዘሩ፤ በኣልብሪትንም አምላካቸው አደረጉ፤ 34 በዙሪያቸው ከነበሩት ጠላቶቻቸው እጅ የታደጋቸውን ጌታ አምላካቸውን አላሰቡትም። 35 እንዲሁም ይሩባኣል የተባለው ጌዴዎን ያደረገላቸውን በጎ ነገር ሁሉ አስበው ለቤተ ሰቡ ውለታ መላሽ ሆነው አልተገኙም። |