መሳፍንት 7 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ጌዴዎን ምድያማውያንን ድል ማድረጉ 1 ይሩበኣል የተባለው ጌዴዎን፥ ከእርሱም ጋር የነበሩት ሰዎች ሁሉ በጠዋት ተነሥተው በሐሮድ ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ። የምድያማውያንም ሰፈር እስራኤላውያን ከሰፈሩበት በስተ ሰሜን በኩል፥ በሞሬ ኰረብታ አጠገብ በሸለቆው ውስጥ ነበረ። 2 ጌታም ጌዴዎንን፦ ከአንተ ጋር ያለው ሕዝብ በዝቶአል፥ ስለዚህ እስራኤል፦ እጄ አዳነኝ ብሎ እንዳይታበይብኝ እኔ ምድያምን በእጃቸው አሳልፌ አልሰጣቸውም። 3 አሁንም እንግዲህ፦ የፈራ የደነገጠም ከገለዓድ ተራራ ተነሥቶ ይመለስ ብለህ በሕዝቡ ጆሮ አውጅ አለው። ከሕዝቡም ሀያ ሁለት ሺህ ተመለሱ፥ ዐሥርም ሺህ ቀሩ። 4 ጌታ ጌዴዎንን እንዲህ አለው፥ “አሁንም ሰዎቹ ብዙ ናቸው፤ ወደ ወንዝ ይዘሃቸው ውረድ፤ በዚያም እጸልይልሃለሁ። ‘ይህ ከአንተ ጋር ይሂድ’ የምለው፥ ከአንተ ጋር ይሄዳል፤ ነገር ግን፥ ‘ይህ ከአንተ ጋር አይሂድ’ የምለው፥ ከአንተ ጋር አይሄድም።” 5 ስለዚህ ጌዴዎን ሰዎቹን ወደ ወንዝ ይዞአቸው ወረደ፤ እዚያም ጌታ፥ “ውሻ በምላሱ እየጨለፈ እንደሚጠጣ ሁሉ፥ በምላሳቸው የሚጠጡትን፥ በጉልበታቸው ተንበርክከው ከሚጠጡት ለይ” አለው። 6 ሦስት መቶ ሰዎች ውሃውን በእጃቸው እያፈሱ ጠጡ፤ የቀሩት ሁሉ ግን ለመጠጣት በጉልበታቸው ተንበረከኩ። 7 ጌታም ጌዴዎንን፥ “ውሃውን በእጃቸው እያፈሱ በጠጡት ሦስት መቶ ሰዎች አድናችኋለሁ፤ ምድያማውያንንም በእጃችሁ አሳልፌ እሰጣችሃለሁ፤ የቀሩት በሙሉ ወደየመጡበት ይመለሱ” አለው። 8 ጌዴዎንም የቀሩትን እስራኤላውያን በሙሉ ወደየድንኳናቸው እንዲመለሱ አደረገ፤ ሦስት መቶውን ግን አስቀራቸው፤ እነርሱም የሚመለሱትን ሰዎች ስንቅና መለከት ወሰዱ። በዚህ ጊዜ የምድያማውያኑ ሰፈር ከእነርሱ በታች በሸለቆአማው ውስጥ ነበር። 9 በዚያች ሌሊት ጌታ ጌዴዎንን እንዲህ አለው፥ “ተነሥ፤ በሰፈሩም ላይ ውረድ፤ በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼሃለሁና። 10 አደጋ ለመጣል የምትፈራ ከሆነ ግን፥ ፉራ ከተባለው አገልጋይህ ጋር ወደ ሰፈሩ ውረድ፤ 11 የሚሉትንም አድምጥ፤ ከዚያ በኋላ በሰፈሩ ላይ አደጋ ለመጣል ድፍረት ታገኛለህ፤” ስለዚህም ጌዴዎን አገልጋዩን ፉራን አስከትሎ እስከ ሰፈሩ ዳርቻ ወረደ። 12 ብዛታቸው እንደ አንበጣ መንጋ የሆነ ምድያማውያን፥ አማሌቃውያንና ሌሎችም የምሥራቅ ሕዝቦች በሸለቆው ውስጥ ሰፍረው ነበር፤ የግመሎቻቸውም ብዛት በባሕር ዳርቻ እንዳለ አሸዋ ስፍር ቍጥር አልነበረውም። 13 አንድ ሰው ያየውን ሕልም ለጓደኛው በሚነግርበት ጊዜ ጌዴዎን እዚያ ደረሰ። ያም ሰው፥ “በሕልሜ ክብ የሆነ አንድ የገብስ ቂጣ ከላይ ተንከባሎ በምድያማውያን ሰፈር ላይ ሲወርድ፥ ድንኳኑንም ሲመታው ከአመታተም ኀይለኛነት የተነሣድንኳኑ ተገልብጦ ሲፈራርስ አየሁ” በማለት ይነግረው ነበር። 14 ጓደኛውም መልሶ፥ “ይህ የእስራኤላዊው የኢዮአስ ልጅ የጌዴዎን ሰይፍ እንጂ ሌላ ነገር ሊሆን አይችልም፤ እነሆ፤ እግዚአብሔር ምድያማውያንንና ሰፈሩን በሙሉ በእጁ አሳልፎ ሰጥቶታልና” አለው። 15 ጌዴዎንም ሕልሙንና ፍቺውን በሰማ ጊዜ ለጌታ ሰገደ፤ ከዚያም ወደ እስራኤላውያን ሰፈር ወጥቶ፥ “ጌታ የምድያማውያንን ሰፈር በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአልና ተነሡ!” አላቸው። 16 ሦስቱን መቶ ሰዎች በሦስት ቡድን ከፍሎ፥ እያንዳንዱን ሰው ቀንደ መለከትና በውስጡ ችቦ ያለበት ባዶ ማሰሮ በእጁ እንዲይዝ አደረገ። 17 ጌዴዎንም እንዲህ አላቸው፤ “እኔን ተመልከቱ፤ የማደርገውንም አድርጉ፤ በሰፈሩ ዳርቻ ስደርስ እኔ የማደርገውን አይታችሁ ልክ እንደዚያው አድርጉ። 18 እኔና አብረውኝ ያሉት ሁሉ ቀንደ መለከቶቻችንን በምንነፋበት ጊዜ እናንተም በሰፈሩ ዙሪያ ሁሉ ቀንደ መለከቶቻቸሁን እየነፋችሁ፥ ‘ለጌታና ለጌዴዎን’ ብላችሁ ጩኹ።” 19 ዘቦቹ ተቀያይረው የእኩለ ሌሊቱን ጥበቃ በጀመሩበት ጊዜ፥ ጌዴዎንና አብረውት የነበሩት መቶ ሰዎች በሰፈሩ ዳርቻ ደረሱ፤ እነርሱም ቀንደ መለከቶቻቸውን ነፉ፤ የያዟቸውንም ማሰሮች ሰበሩ። 20 በሦስት ቡድን የተከፈሉት ሰዎች ቀንደ መለከቶቻቸውን ነፉ፤ ማሰሮቻቸውንም ሰበሩ፤ ችቦዎቻቸውን በግራ እጆቻቸው፥ ቀንደ መለከቶቻቸውንም በቀኝ እጆቻቸው ይዘው፥ “የጌታና የጌዴዎን ሰይፍ” በማለት ጮኹ። 21 እያንዳንዱ ሰው በሰፈሩ ዙሪያ የተመደበበትን ቦታ እንደያዘም ምድያማውያኑ እየጮሁ ሸሹ። 22 የሦስት መቶው ቀንደ መለከት ድምፅ እንደተሰማም ጌታ በሰፈሩ ውስጥ ያለው ሰው አንዱ በሌላው ላይ ሰይፉን እንዲመዝበት አደረገ፤ ሠራዊቱ በጽሬራ አቅጣጫ እስከ ቤትሺጣ፥ ከዚያም አልፈው በጠባት አጠገብ እስካለው እስከ አቤልመሖላ ድንበር ድረስ ሸሽተው ሄዱ። 23 በንፍታሌም፥ በአሴርና በመላው የምናሴ ምድር የሚገኙ እስራኤላውያን ተጠርተው ወጡ፤ ምድያማውያንንም አሳደዱ። 24 ጌዴዎንም በኤፍሬም ኰረብታማ አገር ለሚኖሩት ሁሉ፥ “በምድያማውያን ላይ ውረዱ፤ እስከ ቤትባራ ድረስ ያለውንም የዮርዳኖስ ወንዝ ቀድማችሁ ያዙ” አላቸው። ስለዚህ የኤፍሬም ሰዎች ሁሉ ተጠርተው ወጡ፤ እስከ ቤትባራ ድረስ ያለውንም የዮርዳኖስን ወንዝ ያዙ። 25 እንዲሁም ሔሬብና ዜብ የተባሉትን ሁለቱን የምድያም መሪዎች ያዙ። ሔሬብን በሔሬብ ዐለት አጠገብ፥ ዜብን ደግሞ በዜብ የወይን መጭመቂያ ላይ ገደሏቸው፤ ምድያማውያንንም አሳደዱ፤ የሔሬብንና የዜብን ራስ ቈርጠው ጌዴዎን ወዳለበት ወደ ዮርዳኖስ ይዘው መጡ። |