Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


መሳፍንት 20 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የእስራኤላዊያን ለጦርነት መዘጋጀት

1 ከዚያም ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያሉ እንዲሁም በገለዓድ ምድር የሚገኙ እስራኤላውያን ሁሉ እንደ አንድ ሰው ሆነው ወጡ፤ በምጽጳም በጌታ ፊት ተሰበሰቡ።

2 የእስራኤል ሕዝብ ነገዶች ሁሉ ቁጥራቸው አራት መቶ ሺህ በሚሆን፥ ሰይፍ በሚመዙ እግረኞች ወታደሮች በሆኑ በእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ መካከል ተገኙ።

3 በዚህ ጊዜ ብንያማውያን፥ እስራኤላውያን ወደ ምጽጳ መውጣታቸውን ሰሙ፤ ከዚያም እስራኤላውያን፥ “ይህ ክፉ ድርጊት እንዴት እንደ ተፈጸመ እስቲ ንገሩን” ተባባሉ።

4 ስለዚህ የተገደለችው ሴት ባል ሌዋዊ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔና አባቴ በዚያ ለማደር በብንያም ወደምትገኘው ወደ ጊብዓ መጣን።

5 የጊብዓም ሰዎች በሌሊት ሊገድሉኝ ያደርኩበትን ቤት ከበቡት፤ ከዚያም በቁባቴ ላይ ስለ አመነዘሩባት ሞተች።

6 የቁባቴንም ሬሳ ከቈራረጥሁ በኋላ እያንዳንዱን ቁራጭ፥ እያንዳንዱ የእስራኤል ርስት ወዳለበት አገር ሰደድሁ፤ ይህን ያደረግሁትም ሰዎቹ በእስራኤል ዘንድ አሠቃቂና አስነዋሪ ድርጊት ስለፈጸሙ ነው።

7 አሁንም እናንተ እስራኤላውያን ሁሉ በጉዳዩ ላይ ተወያዩበት፤ ፍርዳችሁንም ስጡ።”

8 ከዚያም ሕዝቡ እንደ አንድ ሰው ሆነው በመነሣት እንዲህ አሉ፤ “ከእኛ ማንም ሰው ወደ ድንኳኑ አይሄድም፤ ማንኛችንም ወደ ቤታችን አንመለስም።

9 ነገር ግን በጊብዓ ላይ የምናደርገው ይህ ነው፤ በዕጣው መሠረት እንዘምትበታለን።

10 ከመላው የእስራኤል ነገዶችም ለሠራዊቱ ስንቅ እንዲይዙ፥ ከመቶው ዐሥር፥ ከሺው አንድ መቶ፥ ከዐሥር ሺው ደግሞ አንድ ሺህ ሰው እንወስዳለን። ከዚያም ሠራዊቱ በብንያም ወደምትገኘው ጊብዓ በሚደርስበት ጊዜ፥ ነዋሪዎችዋ በእስራኤል ላይ ለፈጸሙት አስነዋሪ ድርጊት ተገቢውን ቅጣት ይሰጣቸዋል።”

11 ስለዚህ የእስራኤል ሰዎች ሁሉ እንደ አንድ ሰው ሆነው በመተባበር በከተማይቱ ላይ ዘመቱባት።

12 የእስራኤል ነገዶች ለመላው የብንያም ነገድ እንዲህ በማለት መልእክተኞች ላኩ፥ “በመካከላችሁ የተፈጸመው ይህ ክፉ ድርጊት ምንድነው?

13 አሁንም እነርሱን ገድለን ይህን ክፉ ድርጊት ከእስራኤል እንድናስወግድ፥ እነዚያን የጊብዓን ነውረኞች አሳልፋችሁ ስጡን።” ብንያማውያን ግን ወገኖቻቸውን እስራኤላውያንን አልሰሟቸውም ነበር፤

14 ስለዚህ እስራኤላውያንን ለመውጋት ከየከተሞቻቸው በአንድነት ወደ ጊብዓ መጡ።

15 ብንያማውያንም ከመላው የጊብዓ ነዋሪዎች መካከል ከተመረጡት ሰባት መቶ ሰዎች ሌላ፥ ሰይፍ የታጠቁ ሃያ ስድስት ሺህ ሰዎች በአንድ አፍታ ከየከተሞቻቸው በተጨማሪ አሰባሰቡ።

16 በእነዚህም ሁሉ መካከል እያንዳንዳቸው ድንጋይ ወንጭፈው ጠጉር እንኳ የማይስቱ ሰባት መቶ ምርጥ ግራኞች ነበሩ።

17 እስራኤላውያን፥ ብንያማውያንን ሳይጨምር፥ ሰይፍ የታጠቁ አራት መቶ ሺህ ተዋጊዎች አሰባሰቡ።

18 እስራኤላውያን ወደ ቤቴል ወጡ፤ እግዚአብሔርንም “ብንያማውያንን ለመውጋት ከመካከላችን ማን ቀድሞ ይውጣ?” ሲሉ ጠየቁ። ጌታም፥ “ይሁዳ ቀድሞ ይውጣ” ብሎ መለሰ።

19 በማግሥቱ ጧት እስራኤላዋያን ነሥተው በጊብዓ አጠገብ ሰፈሩ፤

20 የእስራኤል ሰዎች ብንያማውያንን ለመውጋት ሄዱ፤ በጊብዓ ለሚያደርጉትም ውጊያ ቦታ ቦታቸውን ያዙ።

21 ብንያማውያን ከጊብዓ ወጡ፤ በዚያችም ዕለት ከእስራኤላውያን ሃያ ሁለት ሺህ ሰዎች ገደሉ።

22 ይሁን እንጂ እስራኤላውያን እርስ በርሳቸው ተበረታትተው በመጀመሪያው ቀን ተሰልፈው በነበረበት ስፍራ ላይ እንደገና ቦታ ቦታቸውን ያዙ።

23 እስራኤላውያን ወጥተው እስኪመሽ ድረስ በጌታ ፊት አለቀሱ፤ “ወንድሞቻችንን ብንያማውያንን ለመውጋት እንደገና እንውጣን?” ብለው ጌታን ጠየቁ። ጌታም፥ “አዎን፤ ውጡና ውጉቸው” ብሎ መለሰላቸው።

24 በሁለተኛው ቀን እስራኤላውያን ወደ ብንያማውያን ተጠጉ።

25 በዚሁ ጊዜም ብንያማውያን፥ እስራኤላውያንን ሊወጉ ከጊብዓ ወጡ፤ እንደገናም በሙሉ ሰይፍ የታጠቁ ዐሥራ ስምንት ሺህ ሰዎች ገደሉ።

26 የእስራኤልም ሕዝብ ሁሉ ወደ ቤቴል ወጡ፤ እዚያም እያለቀሱ በጌታ ፊት ተቀመጡ፤ በዚያን ቀን እስኪመሽ ድረስ ጾሙ፤ በጌታ ፊት የሚቃጠል መሥዋትና የኅብረት መሥዋዕት አቀረቡ።

27 እስራኤላውያንም የጌታን ፈቃድ ጠየቁ፤ በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት እዚያው ነበር፤

28 የአሮን ልጅ፤ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስም በፊቱ ይቆም ነበር። እስራኤላውያንም፥ “ወንድሞቻችንን ብንያማውያንን እንደገና ሄደን ጦርነት እንግጠማቸው ወይስ ይቅር?” ሲሉ ጠየቁ። ጌታም፥ “ሂዱ፤ በነገው ዕለት በእጃችሁ እሳልፌ እሰጣችኋለሁ” አላቸው።

29 ከዚያም እስራኤላውያን በጊብዓ ዙሪያ ድብቅ ጦር አኖሩ።

30 በሦስተኛውም ቀን ብንያማውያንን ለመውጋት ወጡ፤ ከዚህ በፊት እንዳደረጉት ሁሉ ጊብዓን ለመውጋት ቦታ ቦታቸውን ያዙ።

31 ብንያማውያንም ሊገጥሟቸው ወጡ፤ ከከተማይቱም ርቀው እንዲሄዱ ተደረጉ፤ እንደ በፊቱም እስራኤላውያንን ይገድሉ ጀመር። ከዚህ የተነሣም በሜዳው እንዲሁም ወደ ቤቴልና ወደ ጊብዓ በሚወስደው መንገዶች ላይ ሠላሳ ያህል ሰዎች ወድቀው ነበር።

32 ብንያማውያኑ፥ “እንደ በፊቱ ይሄው ድል እያደረግናቸው ነው” አሉ፥ እስራኤላውያንም በበኩላቸው፥ “ወደ ኋላ እያፈገፈግን ከከተማይቱ ወደ መንገዶቹ እንዲርቁ እናድርጋቸው” ይሉ ነበር።

33 የእስራኤል ሰዎች በሙሉ ከነበሩበት ቦታ አፈግፍገው በበኣልታማር ስፍራ ስፍራቸውን ያዙ። ሸምቆ ይጠባበቅ የነበረው የእስራኤል ጦር ደግሞ ካደፈጠበት ከጊብዓ በስተ ምዕራብ ካለው ቦታ ወጣ።

34 ከዚያም ከመላው እስራኤል የተውጣጣው ዐሥር ሺህ ጦር በጊብዓ ላይ ፊት ለፊት አደጋ ጣለ። ውጊያው ከመበርታቱ የተነሣም፥ ብንያማውያን መጥፊያቸው እየቀረበ መምጣቱን ገና አላወቁም ነበር።

35 ጌታም ብንያምን በእስራኤል ፊት መታው፤ በዚያችም ዕለት እስራኤላውያን በሙሉ ሰይፍ የታጠቁ ሃያ አምስት ሺህ አንድ መቶ ብንያማውያንን ገደሉ።

36 ከዚህ የተነሣ ብንያማውያን ድል መሆናቸውን ተረዱ። በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ጊብዓ ላይ ባኖሩት ድብቅ ጦር ስለተማመኑ የተሸነፉ በመምሰል ለብንያማውያን ቦታ ለቀቁ።

37 ከዚያም ሸምቀው የነበሩት ሰዎች በድንገት እየተወረወሩ ወደ ጊብዓ ገቡ፤ በየቦታው ተሰራጭተውም መላይቱን ከተማ በሰይፍ መቱ።

38 የእስራኤል ሰዎች የሸመቀው ጦር በከተማይቱ ውስጥ ከባድ የጢስ ደመና ምልክት እንዲያሳዩ ተስማሙ፤

39 እስራኤላውያንም ወዲያውኑ እንዲያፈገፍጉ ነበር። ብንያማውያንን ማጥቃት እንደ ጀመሩ፥ ሠላሳ እስራኤላውያንን ስለ ገደሉ፥ “እንደ መጀመሪያው የጦርነት ጊዜ እያሸነፍናቸው ነው” አሉ።

40 ነገር ግን የጢሱ ዐምድ ከከተማይቱ መነሣት በጀመረ ጊዜ፥ ብንያማውያን ወደ ኋላቸው ዞረው የመላይቱ ከተማ ጢስ ወደ ሰማይ ሲወጣ አዩ።

41 ከዚያም እስራኤላውያን ዞረው አጠቋቸው፤ በዚህ ጊዜ ብንያማውያን ጥፋት እንደ ደረሰባቸው ስላወቁ እጅግ ደነገጡ።

42 ስለዚህም ጀርባቸውን አዙረው ከእስራኤላውያን ፊት ወደ ምድረ በዳው ሸሹ፤ ሆኖም ከጦርነት ማምለጥ አልቻሉም፤ ከየከተሞቹ የወጡ እስራኤላውያንም በዚያው ገደሏቸው።

43 ብንያማውያንንም ከበቧቸው፤ አሳደዷቸው፤ ከጊብዓ በስተ ምሥራቅ ትይዩ ባለውም ስፍራ አሳደው አሸነፏቸው፤

44 በጦርነቱም ላይ ዐሥራ ስምንት ሺህ ብንያማውያን ወደቁ፤ ሁሉም ምርጥ ተዋጊዎች ነበሩ።

45 ብንያማውያን ወደ ሁላ ዙረው በምድረ በዳው በኩል ወደ ሬሞን ዐለት በሚሸሹበት ጊዜ፥ እስራኤላውያን በመንገድ ላይ አምስት ሺህ ሰው ገደሉባቸው፤ እስከ ጊድኦምም ድረስ ተከታትለው ሁለት ሺህ ሰዎች በተጨማሪ ገደሉ።

46 በዚያች ዕለት ሰይፍ የታጠቊ ሃያ አምስት ሺህ ብንያማውያን በጦር ሜዳ ወደቊ፤ ሁሉም ምርጥ ተዋጊዎች ነበሩ።

47 ነገር ግን ስድስት መቶ ሰዎች ወደ ሁላ ዙረው በምድረ በዳው ውስጥ ወዳለው ወደ ሬሞን ዐለት ሸሹ፤ በዚያም አራት ወር ተቀመጡ።

48 ከዚያም እስራኤላውያን ወደ ብንያም ምድር ተመልሰው ከተሞቻቸውን በሙሉ እንዲሁም እንስሳቱንና በዚያ ያገኙትን ሁሉ በሰይፍ መቱ፤ በመንገዳቸው ያገኙትን ከተማ ሁሉ በእሳት አቃጠሉ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos