መሳፍንት 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የጌታ መልአክ በቦኪም 1 የጌታ መልአክ ከጌልገላ ወደ ቦኪም ወጥቶ እንዲህ አለ፤ “ከግብጽ ምድር አወጣኋችሁ፤ ለቀደሙትም አባቶቻችሁ ልሰጣቸው ወደ ማልሁላቸው ምድር አመጣኋችሁ፤ እንዲህም አልሁ፤ ከእናንተ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን አላፈርስም፤ 2 እናንተም ከዚህች ምድር ነዋሪዎች ጋር ቃል ኪዳን አታድርጉ፤ መሠዊያቸውንም አፍርሱ፤ እናንተ ግን አልታዘዛችሁኝም፤ ይህን ያደረጋችሁት ለምንድነው? 3 ስለዚህ አሁንም ከፊታችሁ አሳድጄ እንደማላስወጣቸው እነግራችኋለሁ፤ ነገር ግን እነርሱ የጐን ውጋት፥ አማልክቶቻቸውም ወጥመድ ይሆኑባችኋል።” 4 የጌታም መልአክ ይህን ቃል ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በተናገረ ጊዜ ሕዝቡ ድምፃቸውን አንሥተው አለቀሱ። 5 ያንን ስፍራ ቦኪምሠ ብለው ጠሩት፤ በዚያም ለጌታ መሥዋዕት አቀረቡ። የመሳፍንት ዘመን አጠቃላይ ይዘት 6 ኢያሱ ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ እያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ ምድሪቱን ለመውረስ ወደ የርስቱ ሄደ። 7 ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ እንዲሁም ከእርሱ በኋላ ጌታ ለእስራኤል ያደረገውን ታላላቅ ነገሮች ሁሉ ያዩ አለቆች በነበሩበት ዘመን ሁሉ ሕዝቡ ጌታን አመለኩ። 8 የጌታ አገልጋይ የነዌ ልጅ ኢያሱ በመቶ ዐሥር ዓመቱ ሞተ። 9 እነርሱም በኰረብታማው በኤፍሬም አገር በምትገኘው ከገዓስ ተራራ በስተ ሰሜን ባለችው በራሱ ርስት ላይ በቲምናሔሬስ ቀበሩት። 10 ያ ሁሉ ትውልድ ወደ አባቶቹ ከተከማቸ በኋላ ጌታንም ሆነ እርሱ ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገውን ነገር የማያውቅ ሌላ ትውልድ ተነሣ። የመሳፍንት ዘመን ሃይማኖታዊ ትርጒም 11 ከዚያም እስራኤላውያን በጌታ ፊት ክፉ ነገር አደረጉ፤ የበኣል አማልክትንም አመለኩ። 12 ከግብጽ ምድር ያወጣቸውን የአባቶቻቸውን አምላክ ጌታን ተው፤ በዙሪያቸው ያሉት ሕዝቦች የሚያመልኩአቸውን አማልክት ተከተሉ፤ ሰገዱላቸውም፤ ጌታንም አስቈጡት፤ 13 ጌታን ትተው በዓልንና አስታሮትን አመለኩ፤ 14 ስለዚህ ጌታ በእስራኤል ላይ በመቈጣቱ ለሚዘርፏቸው አሳልፎ ሰጣቸው፤ በዙሪያቸው ላሉ ጠላቶቻቸው ሸጣቸው። 15 እስራኤላውያን ለውጊያ በሚወጡበት ጊዜ ሁሉ ጌታ አስቀድሞ በእነርሱ ላይ እንደተናገረውና እንደማለው እንዲሸነፉ የጌታ እጅ ትከፋባቸው ነበር፤ ከዚህም የተነሣ እጅግ ተጨነቁ። 16 ጌታም ከእነዚህ ወራሪዎች እጅ የሚያድኗቸውን መሳፍንት አስነሣላቸው። 17 እስራኤላውያን ግን ሌሎችን አማልክት ተከትለው አመነዘሩ፤ ሰገዱላቸውም እንጂ መሳፍንቶታቸውን አልሰሙም። አባቶቻቸው ጌታን በመታዘዘ በሄዱበት መንገድ ሳይሆን፥ አባቶቻቸው የጌታን ሕግ በመከተል ከሄዱበት መንገድ ፈጥነው ፈቀቅ አሉ። 18 ጌታ መሳፍንትን ባስነሣላቸው ጊዜ ከመስፍኑ ጋር ስለሚሆን፥ እርሱ በሕይወት እስካለ ድረስ ጌታ ከጠላቶቻቸው ያድናቸው ነበር፤ ከጠላቶቻቸው ሥቃይና መከራ ሲደርስባቸው በሚጮኹበት ጊዜ ጌታ ይራራላቸው ነበር። 19 መስፍኑ ከሞተ በኋላ ግን ሕዝቡ ሌሎችን አማልክት በመከተል፥ እነርሱን በማገልገልና በማምለክ ከአባቶቻቸው ይልቅ ወደ ክፉ መንገድ ተመለሱ፤ ክፉ ሥራቸውንና የእልኸኝነት መንገዳቸውንም አይተውም ነበር። የባዕዳን ነገዶች ከከነዓን ያልወጡበት ምክንያት 20 ስለዚህ ጌታ በእስራኤል ላይ እጅግ ተቈጣ፤ እንዲህም አለ፤ “ይህ ሕዝብ ለቀደሙ አባቶቹ የሰጠሁትን ቃል ኪዳን ስለተላለፈ፥ እኔንም ስላልሰማ፥ 21 ኢያሱ በሞተ ጊዜ ከተዋቸው በምድሪቱ ከነበሩት ሕዝቦች አንዳቸውንም በፊታቸው አሳድጄ አላስወጣም። 22 ይህን የሚያደርገውም አባቶቻቸው እንዳደረጉት ሁሉ፥ እስራኤላውያን የጌታን መንገድ የሚጠብቁ መሆን አለመሆናቸውን ለማወቅ እፈትናቸው ዘንድ እነርሱን መሣሪያ ለማድረግ ነው።” 23 ስለዚህ ጌታ እነዚያን ሕዝቦች በዚያው እንዲኖሩ አደረገ፤ በኢያሱ እጅ አሳልፎ በመስጠት ወዲያውኑ አሳዶ አላስወጣቸውም። |