Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


መሳፍንት 19 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ኤፍሬማዊው ሌዋዊና እቊባቱ

1 በዚያን ዘመን በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም፤ በዚሁ ጊዜም በኰረብታማው በኤፍሬም አገር የሚኖር አንድ ሌዋዊ ከይሁዳ ምድር ከቤተልሔም አንዲቱን ሴት ቁባት አድርጎ ወሰዳት።

2 ሴቲቱ ግን በታማኝነት አልጸናችም፤ ትታውም በይሁዳ ምድር ወደሚገኘው ወደ አባቷ ቤት ወደ ቤተልሔም ሄደች፤ እዚያም አራት ወር ከቈየች በኋላ፥

3 ባሏ ታርቆ ሊመልሳት ወደ እርሷ ሄደ፤ ሲሄድም አሽከሩንና ሁለት አህዮችን ይዞ ነበር፤ ሴቲቱም ወደ አባቷ ቤት አስገባችው፤ አባቷም ባየው ጊዜ በደስታ ተቀበለው።

4 የልጂቱ አባትም እዚያው እንዲቈይ አጥብቆ ለመነው፤ ስለዚህ እየበላ እየጠጣ ሦስት ቀን አብሮት ተቀመጠ።

5 በአራተኛው ቀን ማልደው ተነሡ፤ እንግዳውም ለመሄድ ተዘጋጀ፤ የልጂቱ አባት ግን፥ “እንድትበረታ እህል ቅመስ፤ ከዚያም መሄድ ትችላለህ” አለው።

6 ስለዚህ ሁለቱ ለመብላትና ለመጠጣት አብረው ተቀመጡ። የልጂቷም አባት፥ “እባክህ ዛሬም እዚሁ አድረህ ተደሰት” አለው።

7 ሰውየው ለመሄድ ሲነሣም ዐማቱ እንዲያድር ለመነውና እዚያው አደረ።

8 በአምስተኛውም ቀን ጠዋት ሌዋዊው ለመሄድ ሲነሣ፥ የልጂቱ አባት “ሰውነትህን አበርታ፤ ጥላው እስኪበርድም ድረስ በዚሁ ቈይ” አለው፤ ስለዚህ ሁለቱም አብረው በሉ።

9 ሰውየውም ከቁባቱና ከአገልጋዩ ጋር ለመሄድ በተነሣ ጊዜ፥ የልጅቱ አባት ዐማቱ “እነሆ ጊዜው እየመሸ ነው፤ እዚሁ እደሩ፤ ቀኑ እየተገባደደ ነው፤ እዚሁ አድራችሁ ተደሰቱ፤ ነገ ጠዋት ማልዳችሁ በመነሣት መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ” አለው።

10 ሌዋዊው ግን በዚያች ሌሊት በዚያ ለማደር ስላልፈለገ ተነሥቶ የተጫኑትን ሁለቱን አህዮቹንና ቁባቱን ይዞ ኢየሩሳሌም ወደተባለችው ወደ የቡስ ሄደ።


የጊብዓ ሰዎች ወንጀል

11 ወደ የቡስ እንደ ቀረቡም ጊዜው እየመሸ ስለ ነበር አገልጋዩ ጌታውን፥ “እንግዲህ ወደዚህች ወደ የቡሳውያን ከተማ ጐራ ብለን እንደር” አለው።

12 ጌታውም፥ “አይሆንም፤ ሕዝቧ እስራኤላዊ ወዳልሆነ ወደ ባዕድ ከተማ አንገባም፤ ወደ ጊብዓ አልፈን እንሂድ” አለው።

13 ቀጥሎም፥ “በል ና፤ ወደ ጊብዓ ወይም ወደ ራማ ለመድረስ እንሞክርና ከዚያ በአንዱ ስፍራ እናድራለን” አለው።

14 ስለዚህም መንገዳቸውን ቀጠሉ፤ የብንያም ነገድ ወደ ሆነችው ወደ ጊብዓ እንደ ደረሱም ፀሓይ ጠለቀች።

15 ለማደርም ወደዚያው ጎራ አሉ፤ ሄደውም በከተማይቱ አደባባይ ተቀመጡ፤ ሆኖም በቤቱ ለማሳደር ማንም አልተቀበላቸውም ነበር።

16 በዚያች ምሽት ከኰረብታማው ከኤፍሬም አገር መጥቶ በጊብዓ የሚኖር አንድ መጻተኛ ሽማግሌ ከዕርሻ ሥራው መጣ፤ የዚያ አገር ሰዎች ግን ብንያማውያን ነበሩ።

17 ሽማግሌው ቀና ብሎ መንገደኛውን በከተማይቱ አደባባይ ላይ ባየው ጊዜ፥ “ከወዴት መጣህ? ወዴትስ ትሄዳለህ?” ሲል ጠየቀው።

18 ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኛ የመጣነው ከይሁዳ ቤተልሔም ርቆ ከሚገኘው ከኰረብታማው ከኤፍሬም አገር ነው፤ ከይሁዳ ቤተልሔም ነበርሁ፤ አሁን ወደ ጌታ ቤት እሄዳለሁ፤ ወደ ቤቱ የሚወስደኝ ሰው አላገኘሁም።

19 ለአህዮቻችን ገለባና ገፈራ አለን፤ እኛ ባሮችህ ለእኔም ሆነ ለገረድህ፥ አብሮን ላለውም ወጣት እንጀራና የወይን ጠጅ ይዘናል፤ ሌላ ምንም ነገር አያስፈልገንም።”

20 ሽማግሌውም፥ “ኑ ግቡ በቤቴም እደሩ፤ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አቀርባለሁ፤ በዐደ ባባይ ግን አትደሩ” አለው።

21 ስለዚህ ወደ ቤቱ አስገብቶት ለአህዮቹ ገፈራ ሰጣቸው፤ እንግዶቹም እግራቸውን ታጠቡ፤ በሉ፤ ጠጡም።

22 በግብዣው ላይ እየተደሰቱ ሳለ፥ ጥቂት የከተማይቱ ወስላቶች ቤቱን ከበቡ፤ በሩንም እየደበደቡ፥ “ዝሙት እንድንፈጽም በት ቤትህ የገባውን ሰው አውጣው” በማለት የቤቱ ባለቤት በሆነው ሽማግሌ ላይ ጮኹበት።

23 የቤቱም ባለቤት ወደ ውጭ ወጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “የለም ወዳጆቼ፤ እንዲህ አትሁኑ፤ ሰውየው እንግዳዬ ስለ ሆነ ይህን አሳፋሪ ድርጊት አትፈጽሙ።

24 እነሆ ድንግል የሆነች ልጄና የሰውየው ቊባት አሉ፤ እነርሱን አሁኑኑ ላውጣላችሁና አስነውሯቸው፤ ያሻችሁንም አድርጉባቸው፤ በዚህ ሰው ላይ ግን እንዲህ ያለውን አሳፋሪ ድርጊት አትፈጽሙበት።”

25 ሆኖም ሰዎቹ ሊሰሙት አልፈለጉም፤ ስለዚህ ሌዋዊው ቁባቱን ወደ ውጭ አወጣላቸው፤ ሰዎቹም አመነዘሩባት፤ ሌሊቱን ሙሉ ሲፈራረቁባት አድረው ጐሕ ሲቀድ ለቀቋት።

26 በነጋም ጊዜ ሴቲቱ ጌታዋ ወዳለበት ቤት ተመልሳ ሄደች። ደጃፉ ላይ ወድቃ ፀሓይ እስክትወጣ ድረስ እዚያው ተዘረረች።

27 ጌታዋ በጠዋት ተነሥቶ በሩን በመክፈት መንገዱን ለመቀጠል ሲወጣ፥ ቁባተ እጅዋን ከደጃፉ መድረክ ላይ እንደ ዘረጋች ከቤቱ በራፍ ላይ ተዘርራ ወድቃ አገኛት።

28 ሌዋዊውም፥ “በይ ተነሺና እንሂድ” አላት፤ ነገር ግን መልስ አልነበረም። ከዚያም በአህያው ላይ ከጫናት በኋላ ወደ ቤቱ ጉዞውን ቀጠለ።

29 ቤቱ እንደደረሰም ቢላዋ አንሥቶ ቁባቱን ዐሥራ ሁለት ቦታ በመቈራረጥ ወደ እስራኤል ምድር ሁሉ ሰደደ።

30 ያየም ሁሉ፥ “እስራኤላውያን ከግብጽ ከወጡ ጀምሮ እንዲህ ያለ ነገር ከቶ አልታየም፤ አልተደረገም፤ ምን ማድረግ እንዳለብንም በነገሩ አስቡበት፤ ተመካከሩ በት” ተባባሉ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos