Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


መሳፍንት 11 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ዮፍታሔ

1 ገለዓዳዊውም ዮፍታሔ ኃያል ጦረኛ ነበረ፤ አባቱ ገለዓድ ነበር፤ እናቱም ጋለሞታ ነበረች።

2 የገለዓድ ሚስትም ለገለዓድ ወንዶች ልጆች ወለደችለት፤ እነርሱም ባደጉ ጊዜ ዮፍታሔን፥ “ከሌላ ሴት ስለተወለድህ ከቤተሰባችን ምንም ዓይነት ውርስ አይገባህም” በማለት አሳደዱት።

3 ስለዚህም ዮፍታሔ ከወንድሞቹ ሸሽቶ መኖሪያውን ጦብ በተባለች ምድር አደረገ፤ እዚያም ወሮበሎች ተሰባስበው ተከተሉት።

4 ከጥቂት ጊዜ በኋላም አሞናውያን በእስራኤል ላይ ጦርነት ባደረጉ ጊዜ፥

5 የገለዓድ አለቆች ዮፍታሔን ለማምጣት ወደ ጦብ ምድር ሄዱ።

6 እነርሱም፥ “ከአሞናውያን ጋር መዋጋት እንችል ዘንድ መጥተህ ምራን” አሉት።

7 ዮፍታሔም፥ “ምነው ጠልታችሁኝ ከአባቴ ቤት አሳዳችሁኝ አልነበረምን? ታዲያ አሁን ችግር ሲገጥማችሁ ነው የምትፈልጉኝ?” አላቸው።

8 የገለዓድ አለቆችም፥ “እንግዲህ አሁን ወደ አንተ መጥተናል፤ አሞናውያንን እንድንወጋ በል ተነሥና አብረን እንሂድ፤ በገለዓድ በምንኖረው በሁላችንም ላይ አለቃ ትሆናለህ” አሉት።

9 ዮፍታሔም፥ “አሞናውያንን ለመውጋት ወደ አገሬ ብትመልሱኝና ጌታ በእጄ አሳልፎ ቢሰጣቸው በእርግጥ አለቃችሁ እሆናለሁ?” ሲል ጠየቃቸው።

10 የገለዓድ አለቆችም፥ “ጌታ ምስክራችን ነው፤ ያልከውንም በእርግጥ እናደርጋለን” አሉት።

11 ስለዚህ ዮፍታሔ ከገለዓድ አለቆች ጋር ሄደ፤ ሕዝቡም በላያቸው ላይ አለቃና አዛዥ አደረጉት፤ ዮፍታሔም የተናገረውን ቃል ሁሉ ምጽጳ ላይ በጌታ ፊት ደገመው።


የዮፍታሔ ከአሞናውያን ጋር መደራደር

12 ከዚያም ዮፍታሔ ወደ አሞናውያን ንጉሥ፥ “ከእኔ ጋር ምን ጠብ ቢኖርህ ነው መጥተህ አገሬን የወጋኸው?” በማለት መልእክተኞች ላከ።

13 የአሞናውያንም ንጉሥ ለዮፍታሔ መልእክተኞች፥ “ይህን ያደረግሁት እስራኤል ከግብጽ በወጣ ጊዜ በአርኖንና በያቦቅ ወንዞች መካከል ያለውንና እስከ ዮርዳኖስ ያለውን አገሬን ስለ ወሰዱብኝ ነው፤ አሁንም በሰላም መልሱልኝ” አላቸው።

14 ዮፍታሔም መልእክተኞቹን እንደገና ወደ አሞናውያን ንጉሥ ላካቸው፤

15 እንዲህም አላቸው፤ “ዮፍታሔ እንዲህ ይላል፤ እስራኤል የሞዓብንም ሆነ የአሞናውያንን ምድር አልወሰደም።

16 እስራኤል ከግብጽ በወጣ ጊዜ በምድረ በዳ አድርጎ ወደ ቀይ ባሕር ከዚያም ወደ ቃዴስ ሄደ።

17 እስራኤልም ወደ ኤዶም ንጉሥ፥ ‘በአገርህ እንዳልፍ እባክህ ፍቀድልኝ’ በማለት መልእክተኞችን ላከበት፤ የኤዶም ንጉሥ ግን አልሰማውም። ለሞዓብ ንጉሥም እንደዚሁ ላከበት፤ እርሱም አልተቀበለውም፤ ስለዚህ እስራኤል በቃዴስ ተቀመጠ።

18 “ቀጥሎም የኤዶምንና የሞዓብን ምድር በመዞር፥ በምድረ በዳው ተጉዞ ከሞዓብ በስተ ምሥራቅ በኩል በማለፍ ከአርኖን ማዶ ሰፈረ፤ የሞዓብም ድንበር አርኖን ስለ ነበር ወደ ሞዓብ ክልል አልገባም።

19 “ከዚያም እስራኤል በሐሴቦን ወዳለው ወደ አሞራውያን ንጉሥ ወደ ሴዎን መልእክተኞች ልኮ፥ ‘ወደ ገዛ ስፍራችን ለመሄድ በአገርህ እንዳልፍ ፍቀድልኝ’ አለው።

20 ሴዎን ግን በግዛቱ እንዲያልፍ ለመፍቀድ እስራኤልን አላመነውም፤ ሠራዊቱንም ሰብስቦ በያሃጽ ከሰፈረ በኋላ ከእስራኤል ጋር ተዋጋ።

21 “ከዚያም የእስራኤል አምላክ ጌታ ሴዎንንና ሕዝቡን ሁሉ በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤” አሸነፏቸውም፤ እስራኤልም በዚያ አገር የሚኖሩትን የአሞራውያንን ምድር በሙሉ ወረሰ፤

22 ከአርኖን እስከ ያቦቅ፥ ከምድረ በዳው እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ያለውን ምድር በሙሉ ወረሱ።

23 “እንግዲህ የእስራኤል አምላክ ጌታ አሞራውያንን ከሕዝቡ ከእስራኤል ፊት አሳዶ ካስወጣቸው፥ አንተ ለመውሰድ ምን መብት አለህ?

24 አምላክህ ካሞሽ የሰጠህን ይዞ ማቈየቱ ያንተ ፈንታ አይደለምን? እኛስ እንደዚሁ አምላካችን ጌታ የሰጠንን ሁሉ ርስት አድርገን ልንወርስ አይገባንምን?

25 አንተ ከሞዓብ ንጉሥ ከሴፎር ልጅ ከባላቅ ትበልጣለህን? ለመሆኑ እርሱ ከእስራኤል ጋር ተጣልቶአልን? ወይስ ተዋግቶአልን?

26 እስራኤልም በሐሴቦንና በመንደሮችዋ፥ በአሮዔርና በመንደሮችዋ፥ በአርኖንም አቅራቢያ ባሉት ከተሞች ሁሉ ሦስት መቶ ዓመት ተቀምጦ በነበረበት በዚያን ጊዜ ስለምን አልወሰዳችኋቸውም?

27 እኔ አልበደልሁህም፤ አንተ ግን በእኔ ላይ ዘምተህ በድለኸኛል፤ እንግዲህማ ፈራጅ የሆነው ጌታ በእስራኤላውያንና በአሞናውያን መካከል ዛሬ ይፍረድ።”

28 የአሞን ንጉሥ ግን ዮፍታሔ የላከውን መልእክት ከምንም አልቈጠረውም።


የዮፍታሔ መሐላና ድሉ

29 ከዚያም የጌታ መንፈስ በዮፍታሔ ላይ ወረደ፤ ተነሥቶም ገለዓድንና ምናሴን አቋርጦ ሄደ፤ ገለዓድ ባለችው በምጽጳ በኩል አድርጎም በአሞናውያን ላይ ዘመተባቸው።

30 ዮፍታሔም እንዲህ ሲል ለጌታ ተሳለ፤ “አሞናውያንን በእጄ አሳልፈህ ብትሰጠኝ፥

31 አሞናውያንን ድል አድርጌ በምመለስበት ጊዜ በመጀመሪያ ሊቀበለኝ ከቤቴ ደጅ የሚወጣው ማንኛውም ሰው ለጌታ ይሆናል፤ እኔም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አቀርበዋለሁ።”

32 ከዚያም ዮፍታሔ አሞናውያንን ለመውጋት ወጣ፤ ጌታ እነርሱን በእጁ አሳልፎ ሰጠው።

33 ከአሮዔር አንሥቶ እስከ ሚኒት አካባቢ ከዚያም አልፎ እስከ ክራሚም የሚገኙትን ሃያ ከተሞች ፈጽሞ አጠፋቸው፤ አሞናውያንም ለእስራኤል ተገዙ።

34 ዮፍታሔ ምጽጳ ወዳለው ቤቱ ተመለሰ፤ እነሆ፤ ልጁ አታሞ እየደለቀች በመዝፈን ልትቀበለው ወጣች፤ እርሷም አንዲት ልጁ ብቻ ነበረች፤ ከእርሷ በቀር ወንድም ሆነ ሴት ልጅ አልነበረውም።

35 ባያትም ጊዜ ልብሱን በመቅደድ፥ “ወይኔ ልጄ ጉድ አደረግሽኝ ጭንቅም ላይ ጣልሺኝ፤ ማስቀረት የማልችለውን ስእለት ለጌታ ተስያለሁና” ብሎ በኀዘን ጮኸ።

36 እርሷም እንዲህ አለች፤ “አባቴ ሆይ፤ መቼም አንዴ ለጌታ ቃል ገብተሃል፤ ጠላቶችህን አሞናውያንን አሁን ጌታ ተበቅሎልሃልና ቃል የገባኸውን ፈጽምብኝ።

37 ነገር ግን አንድ ነገር ብቻ እንድትፈቅድልኝ እለምንሃለሁ፤ ከእንግዲህ ባል ስለማላገባ ከባልንጀሮቼ ጋር ወደ ተራሮች ወጥቼ እየዞርሁ ሁለት ወር እንዳለቅስ አሰናብተኝ።”

38 እርሱም፥ “በይ ሂጂ” ብሎ ለሁለት ወር አሰናበታት፤ እርሷም ከእንግዲህ ባል ስለማታገባ ከልጃገረድ ጓደኞቿ ጋር ወደ ተራሮች ሄደው አለቀሱ።

39 ከሁለት ወር በኋላ ወደ አባቷ ተመለሰች፤ እርሱም የተሳለውን አደረገ፤ ድንግልም ነበረች። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህ በእስራኤል ልማድ ሆኖ፥

40 የእስራኤል ወጣት ሴቶች የገለዓዳዊውን የዮፍታሔን ልጅ በማሰብ በየዓመቱ እየወጡ የአራት ቀን ኀዘን ያደርጉላታል።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos