መሳፍንት 1 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የይሁዳ፥ የስምዖን፥ የካሌብ እና የቄናውያን መሥፈር 1 ኢያሱ ከሞተ በኋላ የእስራኤል ሕዝብ “ከነዓናውያንን ለመውጋት ማን በቅድሚያ ይወጣልናል?” ብለው ጌታን ጠየቁ። 2 ጌታም፥ “ይሁዳ በቅድሚያ ይውጣ፤ እነሆ ምድሪቱን በእጁ አሳልፌ ሰጥቻለሁ” አለ። 3 ይሁዳም ወንድሙን ስምዖንን፦ “ከነዓናውያንን ለመውጋት ድርሻዬ ወደ ሆነው ምድር አብረን እንውጣ፤ እኔም እንደዚሁ ድርሻህ ወደ ሆነው ምድር አብሬህ እወጣለሁ” አለው። ስለዚህም ከእርሱ ጋር ሄደ። 4 ከዚያ በኋላ ይሁዳ ሕዝብ ዘመተ፤ ጌታም ከነዓናውያንንና ፌርዛውያንን በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው፤ በቤዜቅም ዐሥር ሺህውን ድል ነሡ። 5 አዶኒቤዜቅንም በቤዜቅ አገኙትና ተዋጉት፤ ከነዓናውያንንና ፌርዛውያንን ድል አደረጉ። 6 አዶኒቤዜቅም ሸሸ፤ እነርሱ ግን አሳደው ያዙት፤ የእጆቹንና የእግሮቹንም አውራ ጣቶች ቈረጡ። 7 አዶኒቤዜቅም፥ “የእጃቸውና የእግራቸው አውራ ጣቶች የተቈረጡባቸው ሰባ ነገሥታት ከገበታዬ ሥር የወደቀ ፍርፋሪ ይለቃቅሙ ነበር፤ አሁን ግን እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ የፈጸምሁትን አመጣብኝ” አለ፤ እነርሱም ወደ ኢየሩሳሌም አመጡት፤ በዚያም ሞተ። 8 የይሁዳ ሰዎች ኢየሩሳሌምን ወግተው ያዟት፤ ከተማይቱንም በሰይፍ ስለት መተው፥ በእሳት አቃጠሏት። 9 ከዚያም በኋላ የይሁዳ ሰዎች በኰረብታማው አገር፥ በኔጌብና በቈላማው አገር የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ለመውጋት ወረዱ፤ 10 የይሁዳ ሰዎች በኬብሮን በሚኖሩ ከነዓናውያን ላይ ዘመቱ፤ ኬብሮን ቀደም ሲል ቂርያት-አርባዕ ተብላ ትጠራ ነበር፤ እነርሱም ሼሻይን፥ አሒማንንና ታልማይኖችን ድል አደረጉ። 11 ከዚያም ተነሥተው በዳቤር በሚኖሩት ሰዎች ላይ ዘመቱ፤ የዳቤር የቀድሞ ስም ቂርያት ሴፌር ነበር። 12 ካሌብም፥ “ቂርያት ሴፌርን ወግቶ ለሚይዛት ሰው ልጄን ዓክሳን እድርለታለሁ” አለ። 13 የካሌብም ትንሽ ወንድም የቄኔዝ ልጅ ዖትኒኤል ያዛት፥ ልጁንም ዓክሳን ዳረለት። 14 እርሷም ወደ ዖትኒኤል በመጣች ጊዜ፥ ከአባቷ የእርሻ መሬት እንዲጠይቅ መከረችው፤ ካሌብም እርሷ ከአህያዋ ላይ እንደወረደች “ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ?” ሲል ጠየቃት። 15 እርሷም “የሰጠኸኝ የኔጌብ መሬት በመሆኑ፥ የውሃ ምንጮችን እንድትሰጠኝ እለምንሃለሁ” አለችው፤ ካሌብም የላይኛውንና የታችኛውን ምንጮች ሰጣት። 16 የቄናዊው የሙሴ አማት ዘሮች ከይሁዳ ሰዎች ጋር በመሆን ከዘንባባዋ ከተማ ተነሥተው፥ ዓራድ አጠገብ በኔጌብ ውስጥ በይሁዳ ምድረ በዳ ካሉት ሕዝቦች ጋር አብረው ሄዱ፥ እዚያም ከሕዝቡ ጋር ተቀመጡ። 17 የይሁዳ ሰዎች ከወንድሞቻቸው ከስምዖን ልጆች ጋር ሆነው በጽፋት ከተማ በሚኖሩት ከነዓናውያን ላይ ዘመቱ፤ ከተማይቱንም ፈጽሞ ደመሰሷት፤ ስለዚህ ከተማይቱ ሖርማ ተብላ ተጠራች። 18 ደግሞም የይሁዳ ሰዎች ጋዛን ከነግዛቶቿ፥ አስቀሎን ከነግዛቶቿ፥ አቃሮን ከነግዛቶቿ ያዙ። 19 ጌታ ከይሁዳ ሰዎች ጋር ነበር፤ ስለዚህ ኰረብታማውን አገር ያዙ፤ ነገር ግን በረባዳማው ምድር የሚኖሩት ሰዎች ከብረት የተሠሩ ሠረገሎች ስለ ነበሯቸው ከዚያ አሳደው ሊያስወጧቸው አልቻሉም። 20 ሙሴም እንደ ተናገረው ኬብሮን ለካሌብ ተሰጠች፤ እርሱም ሦስቱን የዐናቅ ልጆች ከውስጧ አሳደደ። 21 ነገር ግን የብንያም ሰዎች በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያንን ከዚያ አላስወጧቸውም፤ ስለዚህ ኢያቡሳውያን እስከ ዛሬ ድረስ ከብንያማውያን ጋር በዚያ አብረው ይኖራሉ። የቤቴል መያዝ 22 የዮሴፍ ወገን ደግሞ ቤቴልን ሊወጉ ወጡ፤ ጌታም ከእነርሱ ጋር ነበር። 23 እነርሱም ቀደም ሲል ሎዛ ትባል ወደነበረችው ወደ ቤቴል ሰላዮችን በላኩ ጊዜ፥ 24 ሰላዮቹም አንድ ሰው ከከተማይቱ ሲወጣ አይተው፤ “የከተማይቱን መግቢያ አሳየን፤ እኛም ምሕረት እናደርግልሃለን” አሉት። 25 እርሱም አሳያቸው፤ እነርሱም ከሰውየውና ከቤተሰቡ በስተቀር የከተማይቱን ሕዝብ በሰይፍ ስለት ፈጁ። 26 ሰውየውም ወደ ኬጢያውያን ምድር ሄዶ ከተማ ሠራ፤ ስሟንም ሎዛ ብሎ ጠራት፤ እስከ ዛሬም የምትጠራው በዚሁ ስም ነው። የሰሜን ነገዶች 27 የምናሴ ነገድ ግን በቤትሳን፥ በታዕናክ፥ በዶር፥ በይብለዓም፥ በመጊዶንና በየአካባቢያቸው ያሉት መንደሮች ነዋሪውን ሕዝብ ስላላስወጡ፥ ከነዓናውያን ኑሮአቸውን በዚያው ለማድረግ ወሰኑ። 28 እስራኤላውያን በበረቱ ጊዜ ግን ከነዓናውያንን የጉልበት ሥራ እንዲሠሩ አስገደዷቸው እንጂ ፈጽሞ አላስወጧቸውም። 29 እንደዚሁም የኤፍሬም ወገኖች በጌዝር የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ማስወጣት አልቻሉም፤ ስለዚህ ከነዓናውያን በመካከላቸው እዚያው መኖርን ቀጠሉ። 30 ዛብሎንም እንደዚሁ በቂድሮንና በነህሎል የነበሩትን በመካከለቸው የቀሩትን ከነዓናውያንን አላስወጣም፤ ነገር ግን የጉልበት ሥራ እንዲሠሩ አስገደዳቸው። 31 አሴርም በዓኮ፥ በሲዶን፥ በአሕላብ፥ በአክዚብ፥ በሒልባ፥ በኣፌቅና በረአብ የሚኖሩትን ሕዝብ በምድሪቱ ካሉት ከነዓናውያን ጋር አብረው ኖሩ። 32 በዚያችም ምድር የተቀመጡትን ከነዓናውያንን አላወጡአቸውምና በመካከላቸው የአሴር ልጆች ተቀመጡ። 33 ንፍታሌምም በቤትሳሚስና በቤትዓናት የሚኖሩትን አላስወጣም፤ ስለዚህ የንፍታሌም ነገድ በምድሪቱ ከሚኖሩት ከነዓናውያን ጋር አብረው ኖሩ፤ ይሁን እንጂ በቤትሳሚስና በቤትዓናት የሚኖሩት ለእነርሱ የጉልበት ሥራ ተገደው ይሠሩ ነበር። 34 የዳን ነገድ በኰረብታማው ምድር ብቻ እንዲወሰን እንጂ ወደ ሜዳማው አገር እንዲወርድ አሞራውያን አልፈቀዱለትም። 35 አሞራውያን በሔሬስ ተራራና በኤሎን በሸዓልቢምም በመቀመጥ ጸኑ፥ ነገር ግን የዮሴፍ ቤት እጅ ከበደች፥ አስገበረቻቸውም። 36 የአሞራውያን ድንበር አቅራቢያም መተላለፊያ እስከ ሴላዕና ከዚያም የሚያልፍ ነበር። |